ዶናልድ ትራምፕ እና ሌሎች 18 ሰዎች የጆርጅያ ምርጫን ለማጭበርበር በመሞከር ተከሰሱ

የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በጆርጅያ ግዛት የተደረገውን የምርጫ ውጤት ለመቀልበስ አሲረዋል በሚል ክስ ተመስርቶባቸዋል።

ከእርሳቸው በተጨማሪ ሌሎች 18 ግለሰቦችም በዚሁ የክስ መዝገብ ተካተዋል።

ይህ ክስ በዚህ ዓመት ብቻ በዶናልድ ትራምፕ ላይ የተመሰረቱ ክሶችን ወደ አራት ከፍ አድርጓቸዋል።

ለቀጣዩ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ለመፋለም የተዘጋጁት ዶናልድ ትራምፕ ሁሉንም ክሶች እንደማይቀበሏቸው ገልጸዋል። በዚህ የክስ መዝገብ ከትራምፕ ጋር ከተከሰሱት ሰዎች መካከል የቀድሞው የትራምፕ ጠበቃ፣ የቀድሞው የዋይት ሃውስ ኃላፊ እና የቀድሞው የፍትህ ሚንስትር ይገኙበታል።

የተመሰረተባቸው ክስ “በማወቅ እና ሆን ብለው የምርጫ ውጤትን ለመቀልበስ በመተባበር” የሚል ነው ።

በዚህም ምክንያት ተከሳሾችን “የወንጀል ድርጅቶች” በማለት ክሱ የሰየማቸው ሲሆን፣ የሃሰት ጽሁፍ በማዘጋጀት፣ የምርጫ አስፈጻሚዎችን በግል በመደለል፣ በሐሰተኛ ሰነድ ዝግጅት፣ ታዛቢዎች ላይ ተጽዕኖ በማሳደር፣ ኮምፒውተርን በመሰለል እና ስርቆት የመሳሰሉ ክሶች ተካተውበታል።

ከእነዚህ ክሶች መካከልም ጥፋተኛ ሆኖ ለተገኘ ሰው እስከ 20 ዓመት የሚያስቀጡ የወንጀል ድርጊቶች ተካተውበታል። ይህ የቅጣት ድንጋጌ የተቀመጠው የምርጫ ተወዳዳሪዎች በማፊያዎች እና በሕገ ወጥ ቡድኖች ታግዘው የምርጫ ውጤትን እንዳይቀለብሱ ለመከላከል ነው።

የሪፐብሊካን ፓርቲ ቀዳሚ ዕጩ የሆኑት ዶናልድ ትራምፕ የተመሰረተባቸው ክስ ፖለቲካዊ እንድምታ ያለው ነው ብሏል።

ይህም የሆነው የ2024 የትራምፕን ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ቅስቀሳ ለማስተጓጎል መሆኑን የትራምፕ የሕግ ክፍል ገልጿል።

“ይህ ወገንተኛ በሆነው የዲሞክራቲክ ፓርቲ ዓቃቤ ሕግ የተቀነባበረው ክስ በአሜሪካውያን ዘንድ እምነት ከማሳጣቱም በላይ የሃሰት ክስ ለማዘጋጀት ያነሳሳቸውን ገፊ ምክንት ቁልጭ አድርጎ ያሳያል” ብሏል የትራምፕ የሕግ ክፍል ባወጣው መግለጫ።

ትራምፕ ቀደም ሲል በዋሽንግተን የነበረውን የምርጫ ውጤት ለመቀልበስ አሲረው ነበር በሚል ሌላ ክስ ተመስርቶባቸዋል።

ትራምፕ በ2021 የጆርጅያን አስተዳዳሪ ባይደንን ለማሸነፍ የሚያስችላቸውን 11 ሺህ 780 ድምጽ እንዲፈልግላቸው ሲጠይቁ በስልክ ተቀድተዋል።