በፍኖተ ሰላም በተፈጸመ ጥቃት ቢያንስ 25 ሰዎች ሲገደሉ ከ50 በላይ መቁሰላቸው ተገለጸ

በአማራ ክልል በምዕራብ ጎጃም ዞን ዋና ከተማ በሆነችው ፍኖተ ሰላም ከተማ ላይ በተፈጸመ ጥቃት ቢያንስ 25 ሰዎች ሲገደሉ፣ ከ50 በላይ የሚሆኑ ሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱን ነዋሪዎች እና የሆስፒታል ምንጮች ለቢቢሲ ተናገሩ።

እሁድ ነሐሴ 07/2015 ዓ.ም. ረፋድ ላይ በከተማዋ ማዕከላዊ ክፍል ላይ የተፈጸመው ጥቃትን በተመለከተ ቢቢሲ ያናገራቸው ነዋሪዎች አንዳንዶቹ የከባድ መሳሪያ ነው ሲሉ ሌሎች ደግሞ በሰው አልባ አውሮፕላን (ድሮን) የተፈጸመ ነው ብለዋል።

በበርካታ የአማራ ክልል ውስጥ በፋኖ ታጣቂዎች እና በመንግሥት ኃይሎች መካከል የሚካሄደው ግጭት ከዋና ዋና ከተሞች በመውጣት በሌሎች አካባቢዎች እየተካሄደ መሆኑን ነዋሪዎች ተናግረዋል።

በፍኖተ ሰላም ከተማ እሁድ እለት ረፋድ ላይ ያጋጠመው ሁኔታ በድሮን የተፈጸመ መሆኑን አንድ የከተማው ነዋሪ ለቢቢሲ ተናግሮ ኢላማ የተደረገውም በከተማዋ አደባባይ ላይ ቆሞ የነበረ ሲኖትራክ የተባለ የጭነት መኪና መሆኑን ገልጿል።

“በቦታው በሲኖትራክ ተጭነው ሲሄዱ የነበሩ ታጣቂዎች አደባባዩ አካባቢ ቆመው ነበር። ጥቃቱ እነርሱን ኢላማ ለማድረግ ነው። ነገር ግን ያ ሲኖትራክ ቦታውን ከለቀቀ ከ20 ደቂቃ በኋላ ነው ፍንዳታው የደረሰው። ከዚያም በአይሱዙ ላይ የነበሩ ሌሎች ወጣቶች እና በአካባቢው ይንቀሳቀሱ የነበሩ ሰዎች ላይ ጥቃቱ ተፈጸመው” ብሏል።

የምዕራብ ጎጃም ዞን መቀመጫ በሆነችው ፍኖተ ሰላም ከተማ ላይ የተፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ በርካታ ሰዎች መሞታቸውን እና ጉዳት እንደደረሰባቸው ነዋሪዎች ተናግረዋል።

ነገር ግን በጥቃቱ የሞቱ ሰዎችን ትክክለኛ ቁጥር ለማወቅ አስቸጋሪ ነው። ነዋሪዎች ቁጥሩን ከ25 እስከ 70 የሚያደርሱት ሲሆን፣ ቢቢሲ በከተማዋ ካለው ዋነኛ የመንግሥት ሆስፒል ባገኘው መረጃ መሠረት 26 ሰዎች በጥቃቱ መገደላቸውን ተረድቷል።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው እና ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈቀዱ የፍኖተ ሰላም ሆስፒታል ሐኪም ጉዳቱ የደረሰው እሁድ ዕለት ከ3፡30 እስከ 4፡00 ሰዓት ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ መሆኑን በመግለጽ፣ “የተከሰተው ፍንዳታ ነው። የፍንዳታውን ምንነትን ግን ማወቅ አልቻልንም” ብለዋል።

የሕክምና ባለሙያው የደረሰውን ጥቃት ተከትሎ ወደ ሆስፒታሉ በርካታ ሰዎች ጉዳት ደርሶባቸው መምጣታቸውን ይናገራሉ። “ታካሚዎች አሁንም እየመጡ ነው። እስካሁን ከ70 በላይ ተጎጂዎች ወደ ሆስፒታላችን መጥተዋል” ብለዋል።

በጥቃቱ ብዙ ሰዎች እንደተገደሉ የፍኖተ ሰላም ሆስፒታል ምንጮች የሚገምቱ ሲሆን፣ ነገር ግን ከዚሁ ጋር በተያያዘ በሆስፒታሉ የተመዘገቡት የሟቾች ቁጥር 26 መሆኑን ገልጸዋል።

የሆስፒታሉ ዶክተር ጨምረውም በጥቃቱ ሕይወታቸው ካለፈው ሰዎች መካከል 22 የሚሆኑት ጥቃቱ እንደተፈጸመ እዚያው በቦታው የሞቱ ሲሆን፣ ሌሎች አራት ሰዎች ደግሞ ለሕክምና ሆስፒታል ከደረሱ በኋላ ነው ሕይወታቸው ያለፈው።

ዶክተሩ ጨምረውም ጉዳት ለደረሰባቸው ሰዎች አስፈላጊ የሆኑ የግብአቶች እጥረት ስላለ አራቱን ሰዎች ለመርዳት ተቸግረው እንደነበር የሕክምና ባለሙያዎች ለቢቢሲ ገልጸዋል።

ጥቃቱ ከተከሰተ በኋላ የሞቱ እና ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ቤተሰቦች ተደናግጠው ወደየቤታቸው የተወሰዱ ሟቾች እና ቁስለኞች እንዳሉ መስማታቸውን ዶክተሩ ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅትም በጥቃቱ ምክንያት ጉዳት ደርሶባቸው በሆስፒታሉ በሕክምና ላይ የሚገኙ 55 ሰዎች እንዳሉ እና አስከ ሰኞ ረፋድ ድረስም ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች እየመጡ መሆናቸውን የሆስፒታሉ ምንጮች ለቢቢሲ ገልጸዋል።

ትናንት እሁድ ካጋጠመው ጥቃት ጋር በተያያዘ ጉዳት ደርሶባቸው በአጠቃላይ 81 ሰዎች ወደ ፍኖተ ሰላም ሆስፒታል የተወሰዱ ሲሆን፣ ከመካከላቸው 26 የሞቱ 55 የመቁሰል ጉዳት የደረሰባቸው መሆናቸውን የሆስፒታል ምንጮች ለቢቢሲ ገልጸዋል።

በዚህም ምክንያት ጉዳት ደርሶባቸው ቤታቸው የቀሩ ሰዎች ስላሉ እንዲሁም ሞተው ወደ ሆስፒታል ሳያመጡ የቀሩ እንዲሁም ወደ ሌላ የሕክምና ተቋም የሄዱ ሊኖሩ ስለሚችሉ፣ በጥቃቱ የሞቱ እና ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች አሃዝ ከዚህም በላይ ከፍ ሊል እንደሚችል ሐኪሙ ገልጸዋል።

ቢቢሲ ያነጋገረው አንድ የከተማዋ ነዋሪ ደግሞ “የእኔን አራት ጓደኞቼን ጨምሮ ከ40 በላይ ሰዎች ተገድለዋል፣ ሰዉ በድንጋጤ ሁሉም በየቤቱ ስለተቀመጠ መረጃ ባለመሰብሰቡ እንጂ የጉዳቱ መጠን ከዚህም በላይ ነው” ይላል።

በጥቃቱ ጉዳት ደርሶበት አሁን ሆስፒታል ውስጥ የሚገኝ አንድ ተማሪ ለቢቢሲ እንደተናገረው “እቃ ልገዛ በወጣሁበት አደባባዩ ላይ በተከሰተው ፍንዳታ ተመታሁ” ብሏል። ጨምሮም ከአደጋው በፊት “ተሽከርካሪ ላይ የሚጨፍሩ ወጣቶች እና ብዛት ያለው ሰው በስፍራው ይንቀሳቀስ እንደነበር” ያስታውሳል።

በፍንዳታው በዙሪያው በነበሩ ሰዎች ብዙ ሰው ላይ ጉዳት እንደደረሰ የሚገልጸው ተማሪ፣ “ብዙ ሕዝብ ነው የተጎዳው። ከእኔ ጎን ራሱ አምስት አስከሬን ተነስቷል” በማለት እሱም ጭንቅላቱ እና እግሩ አካባቢ ጉዳት ደርሶበት ሕክምና ላይ እንደሚገኝ ገልጿል።

በፍኖተ ሰላም ከተማ በተፈጸመው ጥቃት ጉዳት የደረሰባቸው "ከ15 ዓመት ጀምሮ እስከ 20ዎቹ የሚገመቱ" በአብዛኛው በወጣትነት የእድሜ ክልል የሚገኙ መሆናቸውን የፍኖተ ሰላም ሆስፒታል ምንጭ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ከመካከላቸውም “13 እና 14 ዓመት የሚሆናቸው ሁለት ልጆች አግኝተናል” ያሉት የሕክምና ባለሙያው፣ “አብዛኛዎቹ ከባድ ጉዳት" የደረሰባቸው ናቸው።

በዚህም በፍኖተ ሰላም ሆስፒታል ሕክምና እየተከታተሉ ያሉት ሰዎች ከባድ የአካላቸው ጉዳት፣ የዐይን መጥፋት፣ አጥንት መሰበረ እና ሌላም ከፍተኛ ሕክምናን የሚጠይቁ ናቸው ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት 55 ሕክምና የሚፈልጉ ተጎጂዎች በፍኖተ ሰላም ሆስፒታል የሚገኙ መሆናቸውን የጠቀሱት ዶክተሩ፣ ሆስፒታሉ ቀደም ሲልም የግብዓት እጥረት የነበረበት መሆኑን ጠቅሰው፣ አሁን ደግሞ መንገዶች በመዘጋጋታቸው ከፍተኛ የሆነ የአቅርቦት እጥረት ማጋጠሙን ተናግረዋል።

ቢቢሲ በፍኖተ ሰላም ከተማ ስለተፈጸመው ጥቃት ከከተማው አስተዳደር እና ከአማራ ክልል ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ያደረገው ጥረት አልተሳካም።

ከሐምሌ ወር መጨረሻ ጀምሮ በተለያዩ የአማራ ክልል አካባቢዎች በመንግሥት ኃይሎች እና ፋኖ ታጣቂዎች መካከል በተካሄዱ ግጭቶች ምክንያት በክልሉ ውስጥ አለመረጋጋት በመከሰቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መደንገጉ ይታወሳል።

ይህንንም ተከትሎ የፌደራሉ መንግሥት ሠራዊት በክልሉ ውስጥ ተሰማርቶ በርካታ ከተሞችን ከታጣቂዎቹ ነጻ ማድረጉን ባለፈው ሳምንት አሳውቋል።

በመንግሥት ኃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል በተካሄዱት ግጭቶች ምክንያት ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን የሆስፒታል ምንጮች እና ቤተሰቦች ለቢቢሲ ገልጸዋል።

በግጭቱ ውስጥ የከባድ መሳሪያ እና የአየር ጥቃቶች መከሰታቸውን ነዋሪዎች የገለጹ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንም በደብረ ብርሃን፣ በፍኖተ ሰላም እና በቡሬ ከተሞች ሰላማዊ ሰዎች እና በመኖሪያ ሕንጻዎች ላይ ጉዳት ያደረሱ የከባድ መሳሪያ እና የአየር ጥቃቶች ስለመፈጸማቸው ተዓማኒ ሪፖርቶች ደርሰውኛል ብሏል።