በወርቅ ማዕድን ጉድጓድ በገዛ ባልደረቦቻቸው ታግተው የነበሩ ሠራተኞች ተለቀቁ

ሠራተኞቹ የታገቱት በሌላ ሠራተኛ ማኅበር ሠራተኞች ነው

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ሠራተኞቹ የታገቱት በሌላ ሠራተኛ ማኅበር ሠራተኞች ነው

በደቡብ አፍሪካ በወርቅ ማውጫ ጉድጓድ በባልደረቦቻቸው ለቀናት ታግተው የነበሩ ወርቅ ቆፋሪዎች ተለቀቁ።

የወርቅ ማዕድን አውጪዎቹ ላለፉት ሦስት ቀናት በመጥፋታቸው በደቡብ አፍሪካ ጉዳዩ አነጋጋሪ ሆኖ ነበር።

አጋቾቹ ልዩ ልዩ ከቁፋሮ ጋር የተያያዙ መሣሪያዎችን በመያዝ ታጋቾቹን አስፈራርተዋል ተብሏል።

ጎልድዋን በሚባለው የማዕድን ቁፋሮ ማዕከል ነው ክስተቱ የተፈጠረው።

ከእገታው አምልጠን ነው የወጣነው ካሉት መካከል አንዱ ‘ሕይወቴን ለማዳን ነው ማምለጥ የቻልኩት’ ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል።

ነገሩ ይበልጥ አነጋጋሪ ያደረገው አጋቾቹ የታጋቾች የገዛ ባልደረቦቻቸው መሆናቸው ነው።

እገታው ሊፈጸምባቸው የቻለውም የሠራተኛ ማኅበር ምሥረታ ላይ አለመግባባት በማጋጠሙ ነው።

የብሔራዊ ማዕድን አውጪዎች ማኅበር አጋቾቹን ‘አደገኛ ቦዘኔዎች’ ሲል አውግዟቸዋል።

አጋቾቹ ናቸው የሚባሉት ደግሞ የዚህ ሠራተኛ ማኅበር ተቀናቃኝ የሆነው የደቡብ አፍሪካ የማዕድን እና ኮንስትራክሽ ሠራተኞች ማኅበር አባላት ናቸው።

ከጆሐንስበርግ በቅርብ ርቀት በሚገኝ ግዙፍ የወርቅ ማዕድን ማውጫ ጉድጓድ ውስጥ የተፈጸመው እገታ ላለፉት ሦስት ቀናት ቤተሰቦችን ሲያስጨንቅ ነበር የሰነበተው።

ሠራተኞችን አግቷል ተብሎ ወቀሳ የደረሰበት የሠራተኛ ማኅበር በበኩሉ ድርጊቱን አለመፈጸሙንና ታገትን ያሉትም በገዛ ፈቃዳቸው አመጽ ላይ እንደነበሩ ተናግሯል።

ከጉድጓዱ ከሦስት ቀናት በኋላ አምልጠን ወጣን ያሉ ቆፋሪዎች ለቢቢሲ ሲናገሩ ነገሩ ለሕይወታቸው ጭምር አስጊ እንደነበር አብራርተዋል።

“ሮጬ ነው ያመለጥኩት። ሕይወቴን ለማዳን ሌላ ምንም አማራጭ አልነበረኝም” ይላል አንድ ታጋች ለቢቢሲ።

ሌላ የ32 ዓመት ታጋች ደግሞ አጋቾቹ ጥቃት ይፈጽሙ እንደነበር ተናግሯል።

“ለሕይወቴ ስለሰጋሁ በዝምታ ታዘዝኳቸው። በመጀመርያ ቀን ምግብ ነበር፤ በ2ኛው ቀን ከመጀመርያ ቀን የተረፈውን ምግብ ተቋደስን” ብሏል ለቢቢሲ።

ቀጥሎ በነበሩት ቀናት የሚላስ የሚቀመስ በመጥፋቱ በውሃ ብቻ ነፍሳቸውን እንዳተረፉ አንድ በጎልድዋን ለ10 ዓመት የሠራ ታጋች ተናግሯል።

በሁለቱ የሠራተኞች ማኅበር መካከል አለመግባባቱ የተፈጠረው ሠራተኞችን በማገት የተጠረጠረው ማኅበር ሕጋዊ እውቅና ስለሌለው ነው።

ሕጋዊ እውቅና ለማግኘት ያደረጋቸው ሙከራዎችም አልተሳኩለትም።

የማዕድን ቆፋሪ ሠራተኞች ቤተሰቦች ለቀናት ወደ ሥፍራው በመሄድ በድንኩን ውስጥ ውለው እያደሩ የታጋቾችን መለቀቅ በትእግስት ሲጠብቁ ነበር።

ባለቤቷ ከሰኞ ጀምሮ ወደ ቤት አለመመለሱን የተናገረች አንዲት ሴት “ነገሩ ረብሾኛል፤ ባለቤቴ መቼ እንደሚመለስ አላውቅም። ማዕድን ማውጫ ጉድጓድ ውስጥ ሰኞ የገባ አልተመለሰም” ብላለች።

“ባለቤቴ ሠርቶ በሚያመጣው ገንዘብ ነው የምንኖረው፤ ቤት ስመለስ ልጆቼ አባታችን የታል ይሉኛል፤ ምን ብዬ እንደምመልስ አላውቅም” ትላለች ሌላ ሴት።

የፖሊስ ሕዝብ ግንኙነት ብሬንዳ ሙዲሪ ከጉድጓዱ የወጡ ማዕድን ቆፋሪዎችን ውስጥ ስላለው ሁኔታ መረጃ እየጠየቅናቸው ነው ብለዋል።

“እስከአሁን ያነጋገርናቸው ታጋቾች እንደነገሩን ተይዘው የነበረው ከፈቃዳቸው ውጭ እንደነበረ ነው። አጋቾቹ 15 እንደሚደርሱ ነው የነገሩን። አጋቾቹ የትኛውን ማኅበር እንደሚወክሉ ግን አልነገሩንም” ብለዋል የፖሊስ ቃል አቀባይ ብሬንዳ።

የደቡብ አፍሪካ ማዕድን ቆፋሪ ሠራተኞች ማኅበር የተመሠረተው በፈረንጆቹ 1982 ሲሆን መሥራቹ የዛሬው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ ናቸው። በደቡብ አፍሪካ ትልቁ የማዕድን ሠራተኞች ማኀበር ነው።