በሎስ አንጀለሱ የሰደድ እሳት ምክንያት አከራዮች የቤት ኪራይ እየጨመሩ መሆኑ ተነገረ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በሎስ አንጀለሱ የሰደድ እሳት ምክንያት አከራዮች በህገወጥ መንገድ የመኖሪያ ቤት ኪራይ ላይ ከፍተኛ ጭማሬ ማድረጋቸው ተነገረ።
ሰደድ እሳቱን ተከትሎ አንዳንዶች ከዚህ ቀደም ይጠየቅበት ከነበረው የቤት ኪራይ በሺዎች በመጨመር እንደተጠየቁ ቅንጡ ቤቶችን በመሸጥ የሚታወቀው እና በኔትፍሊክስ አንድ ተከታታይ ሾው ያለው ጄሰን ኦፐንሃይም ይናገራል።
የካሊፎርኒያ ግዛት እንዲህ አይነት ፍትሃዊ ያልሆኑ የዋጋ ጭማሬን ህገወጥ ብታደርግም በርካቶች የሰደድ እሳቱን አጋጣሚ በማድረግ ህጉን እየተላለፉ ይገኛሉ ብሏል።
የሎስ አንጀለስ ባለስልጣናት ቀውሱን ምክንያት በማድረግ የሰደድ እሳቱ ተጎጂዎችን የሚያጭበረብሩ ወይም የሚጎዱ ማንኛውም አካላት በህግ ተጠያቂ እንደሚሆኑ አስጠንቅቀዋል።
በሎስ አንጀለስ ሰደድ እሳት ምክንያት በሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች ቤታቸውን አጥተዋል። በርካታ የተፈናቀሉ ተጎጂዎች የማይቀመስ የቤት ኪራይ እና የሆቴል ክፍያ እየተጠየቅን ነው ብለዋል።
ኦፐንሃይም በሎስ አንጀለስ በጣም ውድና ቅንጡ ቤቶችን በመሸጥ የሚታወቀው ድርጅቱ በአሁኑ ወቅት አገልግሎቱን በነጻ እየሰጠ እንደሆነ እና ቤታቸውን ያጡ በርካቶች ጥሪዎችን እየተቀበለ እንደሆነ ተናግሯል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አንድ ደንበኛው የሰደድ እሳቱ ከመከሰቱ በፊት አንድ ቤት ለመከራየት በወር 13 ሺህ ዶላር ተጠይቆ የነበረ ቢሆንም ከእሳቱ በኋላ ዋጋው ንሯል ብሏል።
"ደንበኛዬ በወር 20 ሺህ ዶላርና የስድስት ወራቱን በአንድ ጊዜ ለመክፈል ቢጠይቅም አከራዩ 23 ሺህ ዶላር ካልከፈልክ ብለውታል" ይላል።
"በካሊፎርኒያ እንዲህ አይነት ጭማሬዎችን የሚከለከሉ ህግጋት ቢጠቀሙም ችላ እየተባሉ ነው። በእነዚህ ሁኔታዎች ለመጠቀም ጊዜው አሁን አይደለም" ሲልም ለቢቢሲ ተናግሯል።
የ47 ዓመቱ የሪል ስቴት ድርጅት ባለቤት የሰደድ እሳቱ ቀውስ "ሁሉም ላይ ተጽእኖ አድርሷል" ብሏል።
"በርካቶች በእሳቱ ጭስ ቀኑን ሙሉ እንባ እያነቡ ነው። ይህ ብቻ አይደለም በርካቶች የደረሰባቸው እጦት የሚያስለቅስ ነው" ሲል አስረድቷል።
የካሊፎርኒያ ባለስልጣናት የንግድ ተቋማት ከቀውሱ በፊት ከነበረው 10 በመቶ በበለጠ በህገወጥ መንገድ ጭማሬ እንዳያደርጉ አስጠንቅቀዋል።
የካሊፎርኒያ ግዛት አቃቤ ህግ ሮብ ቦንታ የቤት አከራዮች በህገወጥ መንገድ ጭማሬ እያደረጉ እንደሆነ ከቀናት በፊት ተናግረው ነበር።
"ይህንን ጭማሬ ማድረግ አትችሉም። ተግባሩ በአንድ ዓመት እስር እና በገንዘብ የሚያስቀጣ ወንጀል ነው" ብለዋል።
"ይህ የካሊፎርኒያ ህግ ነው። የተቀመጠው በዚህ አሳዛኝ ክስተት የተጎዱ ሰለባዎች ጥበቃ እና ከለላ ለመስጠት ነው" ሲሉ ጠቅላይ አቃቤ ህጉ አጽንኦት ሰጥተዋል።
ለኪራይ የሚውሉ መኖሪያ ቤቶችን እና ህንጻዎችን ዝርዝር በድረገጽ በሚያወጣው ዚሎው መሰረት በሎስ አንጀለስ የመኖሪያ ቤት አማካኝ ወርሃዊ የኪራይ ዋጋ 2,800 ዶላር ነው።












