ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የህዋ ሕክምና ምርጥ ተማሪ ተብሎ የተሸለመው ኢትዮጵያዊው የቀድሞ አየር ኃይል አባል
ሰለሞን ጉርሙ ቤካ በኒው ዚላንድ፣ ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ኦታጎ የፒኤችዲ (ዶክትሬት) ተማሪ ነው።
የአቪዬሽን እና ስፔስ ሜድስን ወይም የበረራ እና ህዋ ሕክምና አጥኚ ነው።
ከሰሞኑ በዓለም አቀፉ የህዋ ሕክምና ማኅበር የዓመቱ ምርጥ የህዋ ሕክምና ተማሪ የሚል ሽልማት ተበርክቶለታል።
ከመላው ዓለም በበረራ እና ህዋ ሕክምና ዘርፍ ያሉ ተማሪዎች ተወዳድረው፣ ጥሩ ውጤት ያመጡ ወይም ጥሩ ጥናት እና ምርምር ያበረከቱ የሚሸለሙበት ዓመታዊ መሰናዶ ነው።
“ሽልማቱን ማግኘት ደስ ይላል። በተለይ አገራችን ዘርፉ በደንብ ያላደገባት እንደመሆኗ፣ የዚህ አገር ተወላጅ ሆኖ በዚህ ዘርፍ እየተማሩ ማሸነፍ በጣም ትልቅ ኩራት ይሰጣል” ይላል ሰለሞን።
የበረራ እና የህዋና ሕክምና (Aerospace Medicine) በኢትዮጵያ እምብዛም የሚስተዋል ሙያ አይደለም።
አንድ የሕክምና ሳይንስ ዘርፍ ሲሆን፣ ትኩረቱን በረራ እና ህዋ ላይ ያደርጋል።
በሕክምና ውስጥ ያሉ ባለሙያዎች በተለየ ሁኔታ ከበረራ እና ህዋ ጋር የተያያዘ ሥልጠና ወስደው የሚቀላቀሉት ዘርፍ ነው።
የህዋ ሕክምናን ስንመለከት፣ ጤናማ ሰውነት ያላቸው ሰዎች ጤናማ ወዳልሆነው ወይም እንግዳ ወደሆነው የህዋ ከባቢ አየር ሲሄዱ እንዴት ደኅንነቱ በተጠበቀ መልኩ ሥራቸውን አከናውነው በጤና ይመለሳሉ የሚለውን ያጠናል።
የበረራ ሕክምናን ስንመለከት ደግሞ፣ ተጓዦችን ጨምሮ በአውሮፕላን የሚሳፈሩ ሰዎች ከበረራ በፊት፣ በበረራ ወቅት እና ከበረራ በኋላ የሚኖራቸውን የጤና ሁኔታ ይዳስሳል።
የህዋ ሕክምና
የጠፈር ተመራማሪዎች ወደ ህዋ ከመላካቸው አስቀድሞ ሙሉ የጤና ምርመራ ያደርጋሉ። ከህዋ ሲመለሱም እንዲሁ።
“ለምሳሌ ሆስፒታል ውስጥ ሊታከም የሚመጣው የታመመ ሰው ነው። በህዋ ሕክምና ግን ጤነኛ ሆኖ ወደ ጠፈር የተጓዘ ሰው ነው የሚመጣው። ጤናማ ሆኖ ቢጓዝም የህዋ ከባቢ አየር ሙቀት በጣም የበዛበት፣ ግፊት የበዛበት፣ ለተለያየ ጨረራ እና ድምጾች የሚያጋልጥ፣ የኦክስጅን እጥረትን ጨምሮ ሌሎችም መሰናክሎች የሚገጥሙበት ነው” ይላል ሰለሞን መደበኛ በሚባለው እና በህዋ ሕክምና መካከል ያለውን ልዩነት ሲያስረዳ።
ለጤና እክል የሚዳርጉ ነገሮች ወዳሉበት ህዋ የሚጓዙ ባለሙያዎች እንዴት መሰናክሎቹን መወጣት ይችላሉ ከሚለው አንስቶ ሕመም ገጥሟቸው ወደ ምድር ከተመለሱ በኋላ ሕክምናው የሚሰጥበትም ነው።
ሕክምና ከመስጠት ጎን ለጎን የተለያዩ የሕክምና ልኬቶች እና ሕጎች ማውጣትም ኃላፊነታቸው እንደሆነ ሰለሞን ይናገራል። ይህም የመመዘኛ መስፈርት ማውጣት እና ማሻሻልን ይጨምራል።
አብራሪ መሆን የሚችሉት እነማን ናቸው የሚለውን መዝኖ ከመምረጥ አንስቶ፣ ለበረራ አስተናጋጆች የመጀመሪያ ሕክምና እርዳታ እና ሌሎች ክህሎቶችንም ማሠልጠን የባለሙያዎቹ ኃላፊነት ነው።
“ከአንድ የሰዓት ክበብ (Time Zone) ወደ ሌላው ሲሄዱ ምን ሊገጥማቸው ይችላል የሚለውም በዚህ ውስጥ ይካተታል። ቅድመ በረራ እና ድኅረ በረራ ምዘና ደግሞ ሌላው ነገር ነው” ይላል።
የጠፈር ተመራማሪዎች ወደ ህዋ እንዲላኩ ከመወሰኑ በፊት በአካል እንዲሁም በሥነ ልቦና ብቁ መሆናቸው ይመዘናል።
በዚህ ውስጥ የማስታወስ ችሎታ፣ ትኩረት የመስጠት ችሎታ፣ የአመራር ብቃት፣ የመግባባት ብቃት እና ሌሎችም ክህሎቶች ጉዞ እንዲያደርጉ ከመፈቀዱ በፊት እንደሚፈተሹ ይናገራል።
ህዋ ላይ ምን ሕመም ይገጥማል?
የተለመዱ ከሚባሉ ሕመሞች አንደኛው ከአእምሮ ጋር የተገናኘ እንደሆነ ሰለሞን ይናገራል።
ይህ የሚፈጠረው ህዋ ላይ በሚገጥም የብቸኝነት ስሜት ሲሆን፣ ድካም ሌላው በተደጋጋሚ የሚገጥም ሕመም ነው።
“ድካም ስንል የሚገጥመው የአእምሮ እና አካላዊም ድካም ነው። መራብ አለ፣ መጠማት አለ፣ ያልተለመደ የሥራ ሰዓት አለ፣ እንቅልፍ ማጣት አለ” ሲል ያብራራል።
ከተለመደው የቀን እና ሌሊት ዑደት ውጪ ሲሆኑ የሚገጥም እንቅልፍ ማጣትም ተያይዞ ይጠቀሳል።
ሌላው ከዕይታ ጋር በተያያዘ የሚገጥም ሕመም ነው። በጠፈር ያለው ጨረራ (Radiation) ዐይንን ጨምሮ በተቀረው ሰውነት ላይም የጎንዮሽ ጉዳት እንደሚያስከትል ባለሙያው ይገልጻል።
እነዚህ ሕመሞች እንዳይገጥሙ የጠፈር ባለሙያዎች ወደ ህዋ ይዘዋቸው የሚሄዱ መሣሪያዎች አሉ።
ከህዋ ሲመለሱ ደግሞ በአፋጣኝ ምርመራ እና ሕክምና ይደረግላቸዋል።
“አብዛኞቹ የሚገጥሟቸው እክሎች የከፉ ባይሆኑም፣ አንዳንዴ ለረዥም ጊዜ የሚዘልቅ ሕመም ሊገጥማቸውም ይችላል” ይላል ባለሙያው።
ከህዋ ጋር በተያያዘ ናሳ ወይም ደግሞ ከበረራ ሕክምና ጋር በተያየዘ የተለያዩ የአቪዬሽን ተቋሞች ለጠፈር ባለሙያዎች ሕክምና የሚሰጡባቸው ተቋሞች መደበኛ ሕክምና ከሚሰጥባቸው የተለዩ እንደሆኑም ያክላል።
የልጅነት ሕልም
ሰለሞን ተወልዶ ያደረገው በምዕራብ ሸዋ ዞን፣ ከሆለታ ከተማ 15 ኪሎ ሜትር በሚርቅ የገጠር ቀበሌ ነው።
የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ደጃዝማች ከበደ ብዙነሽ ነው የጨረሰው።
“ወደ በረራ እና ህዋ ሕክምና እገባለሁ የሚል ሕልም አልነረበኝም። እንኳን ወደ ሙያው እገባለሁ ልል መኖሩንም አላውቅም። ገጠር ሆነን የተሻለ ሙያ ብለን የምናውቀው መምህርነትን ስለሆነ ብዙዎቻችን ሕልማችን ያ ነበር። ከዚያ በኋላ ሌላ ነገር ስናይ ነው ሌላ ነገር የምንመኘው” ሲል ያስታውሳል።
አያይዞም “. . .ወደዚህ ሙያ ከመግባቴ በፊት በኢትዮጵያ አየር ኃይል የድንገተኛ ቀዶ ሕክምና ባለሙያ ነበርኩ። ስለዚህ በበረራው ዘርፍ ውስጥ ነበርኩ። እዚያው ሳለሁ ሙያውን ለማዳበር ፈለግኩ። ከዚያ ነው ነጻ የትምህርት ዕድሉን ያገኘሁት” ይላል።
ሙያው በኢትዮጵያ እምብዛም የተለመደ ባይሆንም ለበረራው ዘርፍ እና ለሕክምና ከነበረው ቅርበት ተነስቶ ወደዚህ ሙያ እንደተሳበ ይናገራል።
የመጀመሪያ እና ሁለተኛ ዲግሪውን ያገኘው ከጎንደር እና ከወሎ ዩኒቨርስቲዎች ነው።
“ሁሉም ሰው የለመደው እና የሚያውቀው ሙያ ውስጥ ነው የሚገባው። ያኔ ዩኒቨርስቲ ስንገባ የምንመርጠውን ትምህርት ሁሉ አናውቅም፤ የሰዎችን ምክር አንጠይቅም ነበር” ሲል ያስታውሳል።
የህዋ ዘርፍ ተፈላጊ ከሆኑ ሙያዎች አንዱ እየሆነ መጥቷል። ጠፈርን ለቱሪስቶች ክፍት የማድረግ ጅማሮዎችም አሉ። በዚህ ጊዜ በህዋ ሕክምና ዘርፍ ውስጥ መሆኑ የሚያስደስተውም ለዚህ ነው።
“በተለይም በአገራችን በደንብ ያላደገ ሙያ ውስጥ መገኘቴ በጣም ነው የሚያኮራኝ። ለወደፊት ተስፋ የሚሰጥ ሙያ ውስጥ መሆን ያኮራል። በሙሉ አቅሜ ለአገሬ የተቻለኝን አደርጋለሁ።”
ሰለሞን በአየር ኃይል
እአአ በ2009 ከዩኒቨርስቲ ከተመረቀ በኋላ ነው ወደ ኢትዮጵያ አየር ኃይል የገባው። በድንገተኛ ቀዶ ሕክምና እና በበረራ ምዘና ዘርፍ ይሠራ እንደነበር ይናገራል።
“አገሬን ማገልገል እፈልጋለሁ” የሚለው ሰለሞን፣ የዶክትሬት ጥናቱን ሲያጠናቅቅም ወደ አገር ቤት መመለስ እንደሚፈልግ ይገልጻል።
በኢትዮጵያ በህዋ ዘርፍ ያለውን ጅማሮ “ምዕራባውያን ከደረሱበት ደረጃ ላይ ባንደርስም ጥሩ ነው...ባለፈው ሮኬት ተኩሰናል” ሲል ነው የሚገልጸው።
በሌላ በኩል የኢትዮጵያ አየር ኃይል እና የኢትዮጵያ አየር መንገድን እንደ ማሳያ በመውሰድ፣ የአቪዬሽን ዘርፉ ከአፍሪካ ትልቅ ደረጃ መድረሱን ጠቅሷል።
በህዋ ዘርፍ ወደተሻለ ደረጃ ለመድረስ “ቀጣዩን ትውልድ፣ ሕዝቤን፣ አገሬን ማገልገል ነው የምፈልገው” ይላል።
አሁን ላይ ብዙ ታዳጊዎች ወደ ህዋ ሳይንስ የመግባት ፍላጎት እንዳላቸው ይናገራሉ። በተለይም ጥሩ ውጤት የሚያስመዘግቡ ተማሪዎች ወደ ህዋ ሳይንስ ሲያዘነብሉ ማየት ሰለሞንን ያስደስተዋል።
የህዋ ሕክምና የህዋ ሳይንስ አንድ ዘርፍ እንደመሆኑ “የኢትዮጵያን ኤሮስፔስ ከአፍሪካ አንደኛ፣ ከዓለምም የተሻለው እንዲሆን ለማስቻል” የራሱን ጥረት እንደሚያደርግ ይናገራል።
ሰለሞን ከዚህ ቀደም በሪፍት ቫሊ ዩኒቨርስቲ መምህር ነበር። በተለያዩ የሕብረተሰብ ጤና ነክ ዘርፎች ላይ ሠርቷል። የኢትዮጵያ የድንገተኛ ቀዶ ሕክምና ባለሙያዎች ማኅበርንም መርቷል።
የዓለም ድንገተኛ ቀዶ ሕክምና ባለሙያዎች ማኅበር የቦርድ አመራሮች አባል ነው። በኦታጎ ዩኒቨርስቲ የድኅረ ምረቃ ተማሪዎች ማኅበር ዋና አመራር ኮሚቴ እንዲሁም የበረራ እና የህዋ ሕክምና ማኅበር አባልም ነው።
እአአ በ2021 የዓለም አቀፍ በረራ እና የህዋ ሕክምና አካዳሚ የሦስተኛ ዲግሪ የትምህርት ዕድል ሲያገኝ፤ በ2022 በኒው ዚላንድ የፒኤችዲ ትምህርት ጀምሯል።
የጥናት ጽሑፉ፣ ወደ ህዋ የሚጓዙ ጠፈርተኞችን ደኅንነት ለመጠበቅ ከአእምሮ ጤና ምዘና መንገዶች ጋር የተያያዘ ነው።