ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ጨረቃ ላይ ውሃ የሚፈልገው ዶ/ር ብርሃኑ ቡልቻ ማን ነው? ጨረቃስ ‘ሁለተኛ ቤታችን’ ትሆናለች?
እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ሐምሌ 20፣ 1969 የሰው ልጅ ለመጀመሪያ ጊዜ ጨረቃን ረገጠ።
አስትሮናት ኒል አርምስትሮንግ “ይህ ለሰው ልጆች ትልቅ እርምጃ ነው” ብሎ የአገሩ አሜሪካን ሰንደቅ ዓላማ ጨረቃ ላይ ተከለ።
ይህ በሆነ በ53ኛ ዓመቱ ኢትዮጵያዊው ዶ/ር ብርሃኑ ቡልቻ ጨረቃ ላይ ውሃ የሚፈልግ መሣሪያ ሠርቷል።
ዶ/ር ብርሃኑ የናሳ ሠራተኛ ነው።
በእሱ የሚመራ የጥናት ቡድን ጨረቃ ላይ ውሃ መኖር፣ አለመኖሩን የሚመረምር መሣሪያ መሥራቱን ናሳ አስታውቋል።
የሰው ልጅ ለመጀመሪያ ጊዜ ጨረቃን ከረገጠ ወዲህ ወደ ጨረቃ ሄደን አናውቅም።
በቀጣይ ሦስት ወይም አራት ዓመታት ግን ናሳ ዳግመኛ ወደ ጨረቃ ሰው ለመላክ አቅዷል።
በዚህ ጉዞ የመጀመሪያዋ ጥቁር ሴት ወደ ጨረቃ እንደምትወጣም ይጠበቃል።
ሰዎች ወደ ጨረቃ ከመሄዳቸው በፊት ናሳ የተለያዩ መሣሪያዎችን ወደ ጨረቃ ይልካል።
ከእነዚህ መሣሪያዎች አንዱ እንደሚሆን የሚጠበቀው ደግሞ የዶ/ር ብርሃኑ ውሃ አሳሽ መሣሪያ ነው።
ከአምስት ዓሥርታት በፊት የሰው ልጅ ጨረቃን የረገጠው በProject Apollo ነበር።
ዳግመኛ ወደ ጨረቃ ለመጓዝ ናሳ የጀመረው ፕሮጀክት ደግሞ Artemis ይባላል።
በነገራችን ላይ በግሪክ አፈ ታሪክ አርቲመስ የአፖሎ እህት ናት።
ጨረቃ ላይ ምን አለ?
ዶ/ር ብርሃኑ እንደሚለው፣ ከናሳ ትልቅ ሥራዎች አንዱ ሕዋ ላይ ያሉና በዐይን የማይታዩ አካላትን የሚቃኙ መሣሪያዎች ማሰናዳት ነው።
Remote Sensing ይባላሉ።
መሣሪያዎቹ ወይ ጨረቃን በሩቁ ይቃኛሉ፤ አልያም ጨረቃ ላይ አርፈው የናሳን ምርመር ያግዛሉ።
የጨረቃ ምርምር በ70ዎቹ ተጧጡፎ ነበር።
የቀዝቃዛው ጦርነት ተቀናቃኞቹ አሜሪካ እና የቀድሞዋ ሶቪየት ኅብረት መካከል ጠንካራ የሕዋ ፉክክር ነበር።
Space Race ይባላል።
አሁንም ፉክክሩ እንደቀጠለ ነው። አሜሪካ፣ ሩሲያ፣ ቻይና እና ሕንድ ውድድሩን ይመራሉ።
ናሳ፣ ጨረቃ ላይ ምን አለ? ለሰው ልጆች ሕይወት የሚያስፈልጉ ነገሮች ጨረቃ ላይ ይገኛሉ? የሚለውን ለማወቅ ጥናቱን ቀጥሏል።
የዚህ ጥናት አካል የሆነው ደግሞ ጨረቃ ላይ ውሃ ስለመኖሩ የሚፈትሸው መሣሪያ ነው።
የመሣሪያው ፈጣሪ ዶ/ር ብርሃኑ ይህንን መሣሪያ Game Changer [ማርሽ ቀያሪ] ሲል ያሞካሸዋል።
ለምን? ቢባል፣ አንደኛ መሣሪያው ትንሽ ነው። ትክክለኛነቱም ያስተማምናል።
ይህን መሰል መሣሪያዎች Spectrometer ተብለው ይጠራሉ።
“ሕዋ ላይ ያሉትን የተለያዩ ኬሚካሎች፣ ሞለኪውሎች፣ ጋዞች ወዘተ ያጠናል” ሲል ዶ/ር ብርሃኑ ያብራራል።
እነዚህ ኬሚካሎች ልክ እንደ ሰው ልጅ አሻራ ጥለው ያልፋሉ።
መሣሪያው የሚያጠናውም አሻራቸውን ነው።
“አሁን የተሠራው መሣሪያ ብዙ ጋዞች ማጥናት ይችላል። በዋነኛነት ግን ውሃን እንዲያይ ነው የተሠራው” ይላል ዶ/ር ብርሃኑ።
ጨረቃ ላይ ውሃ አለ?
የዶ/ር ብርሃኑ መሣሪያ ዋነኛ ሥራው ጨረቃ ላይ ውሃ መፈለግ ቢሆንም እዛ ጋር አይቆምም።
ውሃ አለ ከተባለ ከየት መጣ? መጠኑስ ምን ያህል ነው? የሚለውን ይፈትሻል።
ሥራው በዚህ አያልቅም።
“ውሃው የምድር Solar System [ሥርዓተ ፀሐይ] ሲፈጠር የመጣ ነው? ወይስ ከዚያ በኋላ ኮሜቶች ወይም በረዶ ያዘሉ ግዑዞች ወደ ጨረቃ ሄደው ውሃውን አጓጉዘው ነው? የሚለውንም ያጠናል” ሲል ዶ/ር ብርሃኑ ያስረዳል።
በሕዋ ሳይንስ፣ ጨረቃ ላይ ውሃ ሊኖር ይችላል የሚል መላ ምት አለ።
እርግጥ ግን አይደለም።
የዶ/ር ብርሃኑ መሣሪያ መላ ምቱን ያረጋግጣል ተብሎ ይጠበቃል።
“ጥናቶች እንደሚያሳዩት ውሃ የሚመስሉ ነገሮች ጨረቃ ላይ አሉ። ግን በተለያዩ የጨረቃ ቦታዎች ላይ ውሃ አለ የሚለውን በእርግጠኛነት ለመናገር ይከብዳል። የእኔ ቡድን የሚሠራው መሣሪያ ውሃን ከሌሎች ሀይድሮጅን ካላቸው ሞለኪውሎች በትክክል መለየት ይችላል።”
ዶ/ር ብርሃኑ የዚህ ጥናት ዋና ተመራማሪ ነው። የጥናትና ምርምር ቡድንም አለው።
ሐሳቡን የጠነሰሰው ተማሪ ሳለ ነው።
እውን እስከሚሆን 8 ዓመታት ወስዶበታል።
አሁንም ግን አልተገባደደም።
ገና የሚቀሩት ደረጃዎች እንዳሉ ይናገራል።
ወደ ጨረቃ እስከሚላክም ሁለት ዓመታት ገደማ ሊወስድ ይችላል።
የናሳን ምዘና አልፎ ነው ወደ ጨረቃ የሚጓዘው።
አፖሎ እና አርቲመስ
አርቲመስ የናሳ ግዙፍ ፕሮጀክት ነው።
አፖሎ ለጨረቃ ምርምር መሠረት ጥሏል።
አፖሎ ከጨረቃ አፈር ይዞ መመለሱ እንደ ምሳሌ ይጠቀሳል።
ከአፖሎ በኋላ የሰው ልጅ ጨረቃን ባይረግጥም፣ ጨረቃን እየዞሩ መረጃ የሚሰበስቡ መሣሪያዎች መላክ ተችሏል።
ጨረቃ ላይ “ውሃ መሰል” አካል እንዳለ የጠቆሙትም እነዚህ መሣሪያዎች ናቸው።
ከጥቆማ በዘለለ ጥልቅ ምርምር ማድረግ ስላልቻሉ ነው የዶ/ር ብርሃኑ መሣሪያ ያስፈለገው።
የአርቲመስ ፕሮጀክት የመጀመሪያ ደረጃ አርቲመስ 1 ይባላል።
ወደ ጨረቃ ምኅዋር (Orbit) ገብቶ፣ ለስድስት ቀናት ዞሮ ወደ መሬት ይመለሳል።
ናሳ አርቲመስ 1ን ባለፈው ነሐሴ ላይ ሊያመጥቅ ብሎ አልተሳካም።
በቅርቡ ዳግመኛ ሙከራ ይደረጋል።
ከአርቲመስ 1 ተከትሎ አርቲመስ 2 ይላካል።
በሦስተኛው ዙር በረራ ወደ ጨረቃ መሣሪያዎች ይላካሉ።
ከዛ ደግሞ ሰዎች ይጓዛሉ።
በሁለተኛው ዙር የሚላኩት ከዚህ በፊት ያልተሠሩ መሣሪያዎች ናቸው።
ዶ/ር ብርሃኑ መሣሪያው በዘህ ጉዞ እንዲካተት እየሠራ ይገኛል።
“የእኛ መሣሪያ ብቁ ሆኖ ከተገኘ በአርቲመስ 2 ወይም 3 ላይ ይሄዳል። አስትሮኖቶቹ ከመሄዳቸው በፊት እንዲላክ ወይም አስትሮኖቶቹ ይዘውት ሄደው ውሃ ያለበትን በዚህ መሣሪያ እንዲያፈላልጉ ይጠቅማል።”
መሣሪያው ሮቦት ላይ ይቀመጥና ጨረቃ ላይ ይንቀሳቀሳል።
ከአፖሎ ጀምሮ ጨረቃን እየዞረ የሚመራመረው መሣሪያ Lunar Rover ነው።
ዶ/ር ብርሃኑ መሣሪያውን ይዞ ጨረቃ ላይ ባይወጣም፣ በአስትሮኖቶች በኩል ጨረቃ ይደርሳል።
ጨረቃ ላይ ውሃ ቢኖር ምን ይጠቅማል?
ዶ/ር ብርሃኑ እንደሚለው፣ ጨረቃ ላይ ውሃ ከተገኘ የሰው ልጆች ‘ሁለተኛ ቤት’ ያገኛሉ ማለት ነው።
ዘመኑ የሕዋ ቱሪዝም ነው።
ጨረቃ ላይ ውሃ ተገኘ ማለት ለሽርሽር ወደ ጨረቃ እንሄዳለን ማለት ነው። አልፎም ጠቅልለን ጨረቃ ላይ ልንኖር እንችላለን።
የሰው ልጅ ሊጠቀምባቸው የሚችሉ ግብዓቶች (Resources) ጨረቃ ላይ የሚገኙበትም ዕድል አለ።
ሕዋ ጥናት ላይ እንደሚሠራ ሳይንቲስት ይህንን መሣሪያ “ትልቅ ስኬት” ሲል ተመራማሪው ይገልጸዋል።
በዋናነት አሜሪካ፣ ሩሲያ፣ ሕንድ እና ቻይና ጨረቃን ቀድሞ ለማጥናት፣ ግብዓቷን ለመጠቀም እንዲሁም የጉብኝትና የኑሮ መዳረሻ ለማድረግ እሽቅድምድም ላይ ናቸው።
አሜሪካ ዓለምን ቀድማ ጨረቃ ላይ ብትወጣም፣ ሕንድ እና ቻይና ባለፉት 15 ዓመታት መሣሪያዎች ወደ ጨረቃ ልከዋል።
ናሳ ተፎካካሪዎቹን ቀድሞ ጨረቃን የማሰስ ትልቅ ግብ አለው። ለዚህ ዒላማ መሳካት ደግሞ የዶ/ር ብርሃኑ መሣሪያ በእጅጉ ያግዛል።
ዶ/ር ብርሃኑ ማን ነው?
ተወልዶ ያደገው አዲስ አበባ ነው።
የመጀመሪያ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱንም አዲስ አበባ ተማረ።
ከዚያም ነጻ የትምህርት ዕድል አግኝቶ ወደ አሜሪካ አቀና።
የመጀመሪያ ዲግሪውን ፊዚክስ እና ምኅንድስና ተማረ።
ፊዚክስ ሲያጠና እምብዛም የማይታወቀው የሕዋ ሳይንስ ማረከው።
በተለይ ደግሞ አስትሮፊዚክስ።
ዩኒቨርስቲ ኦፍ ቨርጂንያ ሲገባ ለሕዋ የሚሆኑ መሣሪያዎችን ሐሳብ ማጎልበት ጀመረ።
“. . . ከልጅነቴ ጀምሮ የፈጠራ ሥራዎች ይስቡኛል። ችግርን መፍታት በጣም ደስ ይለኛል። እንዲያውም የቴክኖሎጂም ይሁን የማኅበረሰብ አገልግሎት ባለሙያ ችግር መፍታት አለበት ብዬ ነው የማስበው።”
ሁለተኛ ዲግሪ እየተማረ ሳለ፣ እንዴት ፀሐዮች ተወልደው፣ አድገው ይሞታሉ? የሚለውን የሚያጠኑ መሣሪያዎች ላይ መሳተፍ ጀመረ።
መጀመሪያ ቨርጂኒያ ኮመንዌልዝ ዩኒቨርስቲ ከዛ ደግሞ ዩኒቨርሰቲ ኦፍ ቨርጂኒያ ተምሯል።
ፒኤችዲውን ከሠራ በኋላ ኤምአይቲ ቆይቷል።
ከስድስት ዓመት በፊት ደግሞ ናሳ ገባ።
ስለ ሕዋ የማወቅ ጉጉት ያደረበት ልጅ ሳለ ነበር።
“. . . የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት የተማርኩት የክርስትና ትምህርት ቤት ነበር። በክርስትና ስለ ሕዋ በተደጋጋሚ ይወራል። የበለጠ የማወቅ ተነሳሽነትም የጫረብኝ ያ ነው. . .”
ሆኖም ግን ኢትዮጵያ ሳለ ናሳ እገባለሁ ብሎ አስቦ አያውቅም።
ዩኒቨርስቲ ሳለ ወደ ናሳ ሊወስዱት የሚችሉ ጥናቶች መሥራት ጀመረ። ጨረቃ ላይ ውሃ የሚፈልገው መሣሪያ የተጠነሰሰውም በዚህ ወቅት ነበር።
ናሳ ሲገባ፣ ስለ Solar System [ሥርዓተ ፀሐይ] እንዲሁም ጋላክሲዎች በማጥናት ብዙ ጊዜ አሳልፏል።
ዶ/ር ብርሃኑ በናሳ
አሜሪካ ነጻ የትምህርት ዕድል አግኝቶ ሲሄድ ብቻውን ነበር።
ከቤተሰብ ተነጥሎ ለብቻ መኖር ደግሞ ቀላል አልነበረም።
“. . . በጊዜው ከአዲስ አበባ ወጥቼ ሁሉ አላውቅም ነበር። አንድ ሰው ከቤተሰቡ ጋር ለረዥም ጊዜ ኖሮ፣ ተለይቷቸው ሳያውቅ፣ ድንገት ሰው አገር ሲገባ ፈተናው ብዙ ነው። ደጋፊ ቤተሰብ የለም። ያኔ እንደ አሁኑም ቶሎ ቶሎ መደዋወል አይቻልም። ‘ፌስታይም’ የለም። ያኔ ለአንድ ዓመት ተኩል አካባቢ ስልክም አልነበረኝም። ስለዚህ መንገድ ላይ በሕዝብ ስልክ በወር ወይም በሁለት ወር አንዴ ነበር የምደውለው። በጣም አስጨናቂ ነበር. . .”
እየተማረ እራሱን በገንዘብ ለመደገፍ መሥራት ነበረበት።
‘አንተ ቁጭ በልና አጥና’ ከሚል ቤተሰብ ወጥቶ የአሜሪካ የሩጫ ሕይወት ውስጥ መግባት ፈትኖታል።
ናሳ ለመግባት ያለው ፉክክር ቀላል አልነበረም።
የኖቤል አሸናፊዎችን ጨምሮ ምጡቅ ሳይንቲስቶች፣ መምህራን እና አጥኚዎች ናሳን መቀላቀል ይሻሉ።
ዶ/ር ብርሃኑ እንደሚለው፣ ናሳ አንድ ዘርፍ ላይ ጥልቅ ጥናት የሠራ ሙያተኛ ነው የሚፈልገው።
በተለይም ሁለተኛ እና ሦስተኛ ዲግሪ ሲሠራ ያደረገው ዝግጅት ናሳ እንዲገባ እንዳገዘው ይናገራል።
“. . . እግዚአብሔር አግዞኝ፣ የቤተሰቦቼን ምክር እንደ ስንቅ በአእምሮየዬ ይዤ፣ ፈተናዎች በማለፍ እዚህ ደርሻለሁ” ይላል።
“. . . በጣም ምርጥ ሐሳብ ያላቸው ሰዎች ናሳ ይመጣሉ። ናሳ ድግግሞሽ አይፈልግም። አንቺን የመሰለ ሌላ ሰው አይቀጠርም። ስለዚህ በተቀጠርሽበት ጉዳይ ልሂቅ መሆን አለብሽ። ለዓመታት ከሠሩ ፕሮፌሰሮች፣ ብዙ ጥናት ካሳተሙ ባለሙያዎች እና ፓተንት ካላቸው ባለሙያዎች መካከል መመረጥ ለኔ ትልቅ ዕድል ነው” ሲልም ያክላል።
ናሳ የገባበትን ቅጽበት “በሕይወቴ ልዩ ከሆኑ ቅጽበቶች ዋነኛው” ይለዋል።
አብረውት የሚሠሩ ባልደረቦቹ ከተመቻቸ የሕይወትና የትምህርት ዕድል መጥተው ሊሆን ቢችልም፣ የእሱ ታሪክ ከእነሱ የተለየ ነው።
በሙያቸው ትልቅ ደረጃ ከደረሱ ጎን መሥራት ብዙ አስተምሮታል።
እንደ ተቋም የናሳ ግብ የአሜሪካ የሕዋ ጥናትን ማሳደግ እንደመሆኑ፣ ይህ የጋራ ዓላማ ባለ ኖቤሉንም፣ ገና ናሳ የገባውንም እንደሚያስተሳስር ይናገራል።
“. . . እንደ አንድ ኢትዮጵያ እንደተማረ ኢትዮጵያዊ እራሴን እዚህ ቦታ አገኘዋለሁ ብዬ ስለማልጠብቅ እደሰታለሁ። የዓለም ትልልቅ ሰዎችን የያዘ እና ትልልቅ አስተዋጽኦ የሚያበረክት ተቋም አካል መሆኔ ትልቅ ኩራት ነው።”
መጀመሪያ አሜሪካ ሲሄድ አዘውትሮ አገር ቤት የመደወል ዕድል ስላልነበረው እናቱን አጥብቆ ይናፍቅ እንደነበር ያስታውሳል።
‘አርዓያዬ’ ከሚለው ታላቅ ወንድሙ ጋርም ቶሎ አይገናኝም ነበር።
የዓመታት ፈተናውን አልፎ የስኬት ታሪክ ካላቸው አንዱ በመሆኑ ዛሬ ቤተሰቦቹ ደስተኛ እንደሆኑ ሳይናገር አያልፍም።
“. . . ከኢትዮጵያ ስትወጪ የመጥፋትም ስኬታማ የመሆንም ዕድል አለሽ። እኔ ከተሳካላቸው አንዱ ሆኜ በማየታቸው ቤተሰቦቼ በጣም ደስተኛ ናቸው።”