ጃፓን መደፈርን እንደገና መተርጎም ለምን አስፈለጋት?

ሜጉሚ ኦካኖ ከተደፈሩ ከቀናት በኋላ አጥቂያቸው ምንም ሳይነካ በነጻ እንደሚለቀቅ ያውቁ ነበር።

ዓለምን በሁለት ጾታ ብቻ የማይከፍሉት እና በወንድ ወይም በሴት እንዳይጠሩ የጠየቁት ሜጉሚ በዚህ ጽሑፍ እሳቸው እያልን እንጠቅሳቸዋለን።

ሜጉሚ ደፋሪያቸውን ያውቁታል።

የት እንደሚኖር እና አድራሻውንም መጠቆም ይችላሉ። ነገር ግን ጉዳዩ በፍርድ ቤትም ውሃ የማይቋጥር እንደሆነም ተረድተውታል።

ለዚህም ምክንያቱ የጃፓን ባለሥልጣናት በሜጉሚ ላይ የተከሰተውን ጉዳይ እንደ መድፈር አድርገው ሊቆጥሩት እንደማይችሉም ተረድተውታል።

ለዚያም ነው የዩኒቨርስቲ ተማሪ የሆኑት ሜጉሚ ጉዳዩን ለፖሊስ ሪፖርት ለማድረግ ያልወሰኑት።

“በዚህ መንገድ ፍትሕን ማግኘት እንደማልችል ተረዳሁ። ደፋሪዬም ነጻ እና ቀላል ሕይወት መኖር ጀመረ። ይህ ለእኔ ከፍተኛ ህመምን የፈጠረብኝ ጉዳይ ነበር” ይላሉ ሜጉሚ።

ነገር ግን አሁን የሜጉሚ ህመም ሰሚ የሚያገኝበት ጊዜ ሊመጣም ይመስላል በጃፓን።

የጃፓን ፓርላማ የአገሪቱን የጾታ ጥቃት ሕግን ለማሻሻል በወጣው ረቂቅ ላይ እየተወያየ ይገኛል። ይህ ዓይነቱ ማሻሻያ በመቶ ዓመት (በክፍለ ዘመኑ) ለሁለተኛ ጊዜ ነው።

የማሻሻያ ሕጉ በርካታ ለውጦችን ቢሸፍንም ነገር ግን ዋኛው እና ቁልፍ የሆነው ሕግ አውጪዎች መደፈር ለሚለው የሚሰጡት ብያኔ/ትርጓሜ (አንድምታ) ነው።

በዚህም መሠረት ከዚህ ቀደም የነበረውን የግዳጅ ወሲብ (ግብረ ሥጋ ግንኙነት) ወደ ስምምነት የሌለው ወሲብ ወደሚለው ትርጉም ይቀይሩታል።

ማሻሻያው በወሲብ ላይ የሚደረስ ስምምነት ወይም የሚሰጥ ፈቃድ ጽንሰ ሃሳብ አሁንም ደካማ በሆነበት ማኅበረሰብ ውስጥም መደፈር የሚለውን በማስፋትም ሕጋዊ ማሰሪያ እንዲኖረው ያበጅለታል።

አሁን ያለው የጃፓን ሕግ መደፈርን በግዳጅ፣ በጥቃት ወይም በማስፈራራት እንዲሁም ንቃተ ህሊናውን ያጣ ሰው ወይም መቃወም የማይችሉ ሰዎች ላይ ወሲብ መፈጸም ነው ሲል ይገልጸዋል።

ይህ ከሌሎች በርካታ አገራት ሕግ ጋር የሚቃረን ነው። ሌሎች አገራት መደፈርን በተመለከተ የሚሰጡት ትርጓሜ ማንኛውም ያለ ስምምነት የተፈጸመ ወሲባዊ ድርጊት በሚል ነው።

የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች እንደሚሉት፣ ይህ ጃፓን ለመደፈር የሰጠችው ጠባብ ትርጉም ዐቃቤ ሕጎች እና ዳኞች በበለጠ አጥብበው እንዲተረጉሙ አድርጓቸዋል። ይህም ለፍትህ የማይቻለውን ከፍተኛ ደረጃ በማስቀመጥ እንዲሁም ከጥቃት የተረፉ ግለሰቦች ሪፖርት እንዳያርጉ የጥርጣሬ ባህል እንዲፈጠር አድርጓል ይላሉ።

ለምሳኔ በአውሮፓውያኑ 2014 በቶኪዮ የክስ መዝገብ ላይ የሰፈረውን እንመልከት። አንድ ግለሰብ የ15 ዓመት ታዳጊን ከግድግዳ ጋር በማጣጋት እሷ እየተቃወመች ወሲብ ፈጽሞባታል።

ነገር ግን ግለሰቡ ከዚህ የመድፈር ወንጀል ነጻ እንዲሆን ተደርጓል። ለዚህም የተሰጠው ምክንያት ታዳጊዋ ራሷን ለመከላከል “እጅግ አስቸጋሪ” አልነበረም የሚል ነው።

ታዳጊዋ የታየችውም እንደ ትልቅ ሰው ነው። ምክንያቱም በጃፓን ለወሲብ ፈቃድ የመስጠት እድሜ 13 ሲሆን፣ ከዓለማችን የበለጸጉ አገራት መካከል ዝቅተኛውም ነው።

“የፍርድ ሂደቶች እና ውሳኔዎች ይለያያሉ። አንዳንድ ተከሳሾች ምንም እንኳን ስምምነት የሌለው ወሲብ ቢፈጽሙም ‘የጥቃት ወይም የማስፈራራቱን’ ሂደት ስላላሟሉ በፍርድ ቤት ክስ አልተመሰረተባቸውም” በማለት ከወሲባዊ ጥቃት የተረፉ ግለሰቦች ቡድን የሆነው ስፕሪንግ የተሰኘ ተቋም ቃለ አቀባይ ዩ ታዶኮሮ ትናገራለች።

ለዚህም ነው ሜጉሚ አብሯቸው በሚማር የዩኒቨርስቲ ተማሪ የደረሰባቸውን ጥቃት ለፖሊስ ሪፖርት ያላደረጉት።

ሁለቱም አብረው ቴሌቪዥን እየተመለከቱ ባለበት ጊዜ ነበር ግለሰቡ ወሲባዊ ሙከራዎችን ያደረገው። ሜጉሚ እምቢ ቢሉም ግለሰቡ አላቆመም።

ታገሉ፤ መጨረሻ ላይም ሜጉሚ በጣም ሲዝሉ መታገላቸውን አቆሙ እናም ግለሰቡ ደፈራቸው። እንዲህ ዓይነት መደፈር ሕጉ ሽፋን እንደማይሰጠው ተሟጋቾች ይናገራሉ።

በተደፈሩ በተከታዮቹ ቀናት ውስጥ የሕግ ተማሪ የሆኑት ሜጉሚ የአገሪቱን የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ፈተሹ። እንዲሁም ከዚህ ቀደም የነበሩ ሪፖርቶችን መረመሩ።

እናም የተፈጸመባቸው ነገር ለእሳቸው መደፈር ቢሆንም፣ በፍርድ ቤት ዐይን ግን “የጥቃት እና የማስፈራራት” መስፈርቶችን እንደማያሟላ ተገነዘቡ።

እንዲሁም ከጥቃት የተረፉ ግለሰቦችን በማሸማቀቅ እና በመውቀስ “ለሁለተኛ ጊዜ” እንደተደፈሩ ያህል እንዲሰማቸው እንደተደረጉም ሜጉሚ ተሰምቷቸዋል።

በተለይም ፖሊስ፣ የሆስፒታል ሠራተኞች ወይም መርማሪዎች ከጥቃት ለተረፉ የሚያሳዩት ግድየለሽነት ይህ እንዲሰማቸው አድርጓቸዋል ይላሉ።

“ፍትሕ የማግኘት ተስፋዬም ስለመነመነ በምርመራው ውስጥ ማለፍ አልፈለኩም። ለዚያም ነው ወደ ፖሊስ ያልሄድኩት። ሪፖርቴ ተቀባይነት ይኑረው አይኑረው እርግጠኛ አልነበርኩም” ይላሉ።

ይልቁንም ወደ ዩኒቨርሲቲው የትንኮሳ የምክር ማዕከል አቀኑ። ማዕከሉም ምርመራ ካደረገ በኋላ በሜጉሚ ላይ የመድፈር ጥቃት እንደተፈጸመ ውሳኔ አስተላለፈ።

ቢቢሲ ማዕከሉን በጉዳዩ ላይ ለማነጋገር ቢጠይቅም “ምስጢራዊ” ነው በማለት ፈቃደኛ እንዳልሆነ አስታውቋል።

ምርመራው እስከሚጠናቀቅበት ጊዜ ድረስም አጥቂው ተመረቀ። ግለሰቡም ማስጠንቀቂያ ብቻ እንደተሰጠው እና ምንም እንዳልደረሰበት ሜጉሚ ይናገራሉ።

“ይህንን ግለሰብ በወንጀል ክስ በድርጊቱ እንዲጸጸት ማድረግ አለመቻሌ ቅር ያሰኘኛል” ይላሉ።

የለውጥ ጩኸት

ይህ የሜጉሚ ታሪክ ብቻ አይደለም - የበርካታ ጃፓናውያን እንጂ።

በጃፓን ውስጥ ከሚከሰቱ የመደፈር ጉዳዮች መካከል አንድ ሦስተኛው ብቻ ናቸው ክስ የሚያስመሰርቱት።

ይህም ከአጠቃላይ የወንጀል ክስ መጠን በጣም ያነሰም ነው። ለዚያም ነው ሕዝቡ ለውጥ እንዲመጣ ጩኸቱን እያሰማ ያለው።

በአውሮፓውያኑ 2019 አራት የወሲባዊ ጥቃት ተከሳሾች በአንድ ወር ውስጥ በነጻ መሰናበታቸው የጃፓን ሕዝብን አስቆጣ።

ፉኮካ በተባለ ስፍራ አንድ ግለሰብ በመጠጥ ራሷን ከሳተች ሴት ጋር የወሲብ ግንኙነት ፈጸመ። ይህ በሌሎች ቦታዎች እንደ መደፈር ሊቆጠር ይችላል።

ፍርድ ቤቱ ግለሰቧ ከሬስቶራንት ወጥታ መጠጥ ጠጥታ ስትሰክር የመጀመሪያ ጊዜዋ መሆኑን ሰምቷል።

በወቅቱ እንደ ወጡ ዘገባዎች ከሆነ ግለሰቡ በዝግጅቱ ላይ ወንዶች በቀላሉ ወሲብ የሚፈጽሙበት ቦታ ነው ብሎ እንዳሰበ እና ግለሰቧንም ሲወስድ የተመለከቱ ሰዎች አላስቆሙትም ተብሏል።

በተጨማሪም ሴትዮዋ ጥቃቱ በተፈጸመበት ጊዜ ዐይኗን ከፍታ “ድምጽ በማውጣቷም” እንደተስማማች ተገምቷል።

ሌላኛው ናጎያ በምትባል ግዛት አንድ አባት በአስራዎቹ ዕድሜ ውስጥ ከምትገኘው ሴት ልጁ ጋር ለበርካታ ዓመታት ወሲብ መፈጸሙን የሚመለከተው ጉዳይ ነው።

ፍርድ ቤቱ አባትየው ሴት ልጁን “ሙሉ በሙሉ በበላይነት ተቆጣጥሯታል” የሚለውም ላይ ጥርጣሬ ማሳደሩ ነው።

ለዚህም የተነሳው ጉዳይ ልጂቷ ቤተሰቦቿ የመረጡላትን ትምህርት ቤት ተቃውማ ሌላ ትምህርት ቤት መምረጧን በማንሳት ነው።

ነገር ግን የሥነ ልቦና ባለሙያ ታዳጊዋ አባቷን ለወሲብ መቃወም የማትችልበት የአዕምሮ ደረጃ ላይ እንደነበረች ምስክርነት ሰጥተዋል።

ሕዝባዊ እምቢተኝነቱን ተከትሎ እነዚህን ሁለት ጉዳዮችን ጨምሮ ነጻ የወጡ አራት ወሲባዊ ጥቃቶች በድጋሚ ክስ ተመስርቶ አጥቂዎቹ ጥፋተኛ ሆነው ተገኝተዋል።

ከጾታዊ ጥቃት ለተረፉ ሰዎች አጋርነትንም ለማሳየት ‘ፍላወር ዴሞ’ በመባል የሚታወቅ አገር አቀፍ ዘመቻም በጃፓን የተሟጋቾች ተጀምሯል።

ተሟጋቾቹ ከፍተኛ ተሰሚነት ያገኘው 'ሚቱ' የተባለው እንቅስቃሴ እንዲሁም የጃፓናዊቷ ጋዜጠኛ ሺዮሬ አስደናቂ ድል በጾታዊ ጥቃት ላይ ብሔራዊ ውይይት እንዲካሄድ በር በመክፈት የሕግ ማሻሻያውም እንዲመጣ የራሱን ሚና ተጫውቷል።

መደፈርን በአዲሱ ትርጉም እና ሕግ መሠረት ተጠቂዎች ፍቃደኛ አለመሆናቸውን ለመግለጽ፣ ለመናገር ወይም ለመፈጸም የሚከብዳቸውን ስምንት ሁኔታዎችን በግልጽ አስቀምጧል።

ይህም ተጠቂዎች አልኮል ወይም አደንዛዥ ዕጾች ተጠቅመው ከሆነ፣ የትኛውም ማስፈራሪያ እና ትንኮሳ ላይ ከሆኑ፣ የሚፈሩበት ወይም የሚሸማቀቁበት ሁኔታ ከተፈጠረ የሚል ተካቶበታል።

በተጨማሪም የሥልጣንን ያላግባባብ መጠቀም የሚያካትት ሲሆን፣ ተጠቂዎች ይህንን ካልፈጸሙ የሆነ ነገር እንደሚደርስባቸው የሚያስጨንቅ ወይም የሚሰጉበት ሁኔታ ከተፈጠረ ነው።

ለወሲብ የመስማሚያ ዕድሜም ወደ 16 ዓመት ያድጋልም ተብሏል።

ሆኖም አንዳንድ የመብት ተሟጋቾች በሕጉ ላይ አሻሚ ቃላቶች ስላሉ ሁኔታዎቹ የበለጠ ግልጽነት እና መብራራት እንዲኖራቸው ጠይቀዋል።

በተጨማሪም ዐቃቤ ሕግ ክሱን ለማረጋገጥ የበለጠ አዳጋች ያደርጉታል ብለው ይሰጋሉ።

ሌሎች ደግሞ ለአካለ መጠን ያልደረሱ ታዳጊዎች ተጨማሪ ጥበቃ ሊደረግላቸው እንደሚገባም አስተያየታቸውን እየሰጡ ነው።

የተለያዩ ጥያቄዎች እየተነሱ ቢሆንም ማሻሻያው ከጸደቀ ለውጥን ለረጅም ጊዙ ሲመኙ ለቆዩ በርካቶች ድል መቀናጀት ይሆናል።

“የዚህን ሕግ ርዕሱን እንኳን ከቀየሩ ውይይቱን በጃፓን እንደሚያጀምሩት ተስፋ እናደርጋለን። ለምሳሌም ያህል ስምምነት ምንድን ነው? ያለ ፍቃድ ስንል ምንድን ነው” በማለት በቶኪዮ ተቀማጭነቱን ያደረገው ሂውማን ራይትስ ናው ምክትል ፕሬዚዳንት ካዙኮ ኢቶ ይናገራሉ።

ነገር ግን ጊዜ ያለ አይመስልም። የጃፓን ፓርላማ አዲሱን ሕግ እስከ ሰኔ 14 ማጽደቅ ቢኖርበትም በአሁኑ ወቅት በኢሚግሬሽን ክርክር ተጠምዷል።

ያ ቀነ ገደብ አለፈ ማለት የጾታ ጥቃት ማሻሻያውን ስጋት ላይ ይጥለዋል። ተሟጋቾች ባለፈው ሳምንት ይህንን መዘግየት አስመልክቶ “ተቀባይነት የሌለው” ሲሉ ያወገዙ ሲሆን፣ የሕግ አውጪ አካላት በአስቸኳይ እርምጃ እንዲወስዱ ጠይቀዋል።

የወሲብ ጽንሰ ሃሳብን እንደገና መከለስ

ይህ ማሻሻያ በጃፓን ውስጥ ያለውን የተወሰነውን ችግር ብቻ ነው የሚፈታው ይላሉ የመብት ተሟጋቾች። ለለውጡ ጥሪ እያደረጉ ያሉ ተሟጋቾች ጉዳዩ ከፍርድ ቤት በላይም እንደሆነ ነው የሚናገሩት።

በጃፓን ውስጥ መደፈር ወይም ወሲባዊ ጥቃት የተሸፋፈነ እና እንደ ነውር የሚታይ ጉዳይ ነው። በቅርቡ ግን ጉዳዩ በአደባባይ መነጋገሪያ ሆኗል።

ከእነዚህም መካከል የሺዮሪ ኢቶ የፍርድ ቤት ፍልሚያ፣ የቀድሞ የመከላከያ ሠራዊት አባል እና የወሲብ ጥቃት ተጎጂ የሆነችው ሪና ጎኖይ መግለጫ፣ እንዲሁም የጆኒ ኪታጋዋ የማጋለጥ ጉዳይ ብሔራዊ ትኩረትን አግኝቷል።

ካዙኮ ኢቶ እንደሚሉት የችግሩ አንድ ካል ጃፓናውያን ለዘመናት “የተዛባ የወሲብ ሃሳብ እና ስምምነትን ይዘው” ማደጋቸው ነው።

በአንድ በኩል የወሲብ ትምህርት አብዛኛውን ጊዜ የሚሰጠው ግልጽ ባልሆነ መንገድ ሲሆን፣ በወሲብ ጊዜ መደረግ ያለበትን ስምምነትንም ሆነ ስለሚሰጥ ፈቃድ ምንም አይባልም።

ሆኖም በሌላ መልኩ ደግሞ የጃፓን ታዳጊዎች አንዲት ሴት ያለ ፈቃዷ ወሲብ ሲፈጸምባት ስትደሰት የሚያሳዩ የወሲብ ፊልሞችን በቀላሉ ማግኘት ይችላሉ።

ጃፓን ከወሲባዊ ጥቃት ለተረፉ ሰዎች ተጨማሪ የገንዘብ እና የሥነ-ልቦና ድጋፍ ልታደርግ ይገባል ሲሉ ጠበቃ እና የመብት ተሟጋቿ ሳኩራ ካሚታኒ ይናገራሉ።

ነገር ግን ተጠቂዎች ብቻ ሳይሆን አጥቂዎቹም እርዳታ ማግኘት አለባቸው ይላሉ።

“የወሲብ ወንጀሎች የመደገም ዕድላቸው በጣም ከፍተኛ ነው። ለዚያም ነው በመከላከል ላይ ማተኮር ያለብን። ያለበለዚህ በርካታ ተጠቂዎች ይኖሩናል” ይላሉ።

ነገር ግን አሁን ያለው መሠረታዊ ሥራ ማሻሻያዎቹ እንዲጸድቁ እና ተግባራዊ እንዲሆኑ እንዲሁም ተጠቂዎች ሪፖርት እንዲያደርጉ ማበረታት እንደሆነ ተሟጋቾች ይናገራሉ።