ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ዶናልድ ትራምፕ ወደ ፌስቡክና ኢንስታግራም እንዲመለሱ ሊፈቀድላቸው ነው
ዶናልድ ትራምፕ ላይ ለሁለት ዓመታት ተጥሎ የነበረው እገዳ መጠናቀቁን ተከትሎ የቀድሞው ፕሬዝደንት ወደ ፌስቡክና ኢንስታግራም ለመመለስ እንደሚፈቀድላቸው ሜታ አስታውቋል።
ግዙፉ የማኅበራዊ ሚዲያ ተቋም ትራምፕ ላይ የተጣለው እገዳ በመጪዎቹ ሳምንታት እንደሚያበቃ ገልጿል።
የሜታ ዓለም አቀፍአዊ ጉዳዮች ፕሬዝዳንት ኒክ ክሌግ በጽሑፍ ባስተላለፉት መልዕክት ሕዝቡ “ፖለቲከኞች የሚሉትን መስማት አለበት” ብለዋል።
የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት እንደ አውሮፓውያኑ በ2021 በካፒቶል ሂል ከተፈጠው ሁከት በኋላ ላልተወሰነ ጊዜ ከፌስቡክና ኢንስታግራም ታግደው ነበር።
ትራምፕ በካፒቶል ሂል ሁከት ላይ የተሳተፉ ሰዎችን በማኅበራዊ ሚዲያው ተጠቅመው በማመስገናቸው እርምጃው እንደተወሰደ ክሌግ አስታውሰዋል።
ጨምረውም እገዳው ባልተለመደ መልኩ፣ ባልተለመደ ሁኔታ የተወሰነ ነው ሲሉም አክለዋል።
በተደረገው ግምገማ የትራምፕ የፌስቡክ አካውንት አሁን ላይ ለዜጎች ደኅነነት አስጊ መሆኑ አብቅቷል ያሉት ኃላፊው ሆኖም የቀድሞ ፕሬዝዳንት ለፈጸሙት ጥሰት ቅጣት እንደሚጠብቃቸው ተናግረዋል።
በቀጣዩ ዓመት ለአሜሪካ ፕሬዝደንትነት ለሁለተኛ ዙር ለመወዳድር እየተዘጋጁ ያሉት ትራምፕ ወደ ፌስቡክ እንዲመለሱ ሪፐብሊካኖች ጫና ሲያደርጉ ቆይተዋል።
ዶናልድ ትራምፕ ራሳቸው በመሠረቱት ትሩዝ ሶሻል በተባለው ማኅበራዊ መድርክ ላይ ይህንን ውሳኔ ተከትሎ በሰጡት አስተያየት ፌስቡክ “የናንተ ተወዳጅ ፕሬዝዳንት የሆንኩትን እኔን ካገደ በኋላ ቢሊዮኖችን ከስሯል” ሲሉ ጽፈዋል።
“ይህ ዓይነቱ ነገር በሥልጠን ላይ ባለ ፕሬዝዳንት ወይም ይህ በማይገባው ማንኛውም ሰው ላይ ፈጽሞ መደግም የለበትም” ሲሉም አክለዋል።
ትራምፕ ወደ ፌስቡክ የመመለስ ዜና በተሰማ አጭር ጊዜ ውስጥ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ባለፈው ምርጫ እንዳደረጉት አሸናፊ ነኝ የሚሉ ዓይነት ሐሰተኛ መረጃዎችን ለማጋራት ማኅበራዊ ሚዲያውን በድጋሚ ሊጠቀሙ ይችላሉ በሚል ከዲሞክራቶችና አክቲቪስቶች ተቃውሞ ገጥሞታል።
የካሊፎርኒያ የዲሞክራቶች ተወካይ አዳም ሺፍ በትዊተር ገጹ “ትራምፕ ሁከትን ቀስቅሰዋል” ሲሉ የጻፉ ሲሆን “ትራምፕ ውሸትና ቅጥፈት እንዲያስተላልፉ ድጋሚ ዕድሉን መስጠት አደገኛ ነው” ብለዋል።
እንደ አውሮፓውያኑ በ2021 ጥር ወር ላይ ከተከሰተው በካፒቶል ሂል ከተፈጠረው ሁከት ጋር ተያይዞ የትዊተርን ደምቦች ጥሰዋል በሚል ከማኅበራዊ ትስስር ገጹ ታግደው ነበር።
ሆኖም ባለፈው ዓመት የትዊተር ባለቤት ኤሎን መስክ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ወደ ማኅበራዊ ገጹ እንደሚለሱ ድምጽ እንዲሰጥ አድርጓል።
በውጤቱም ድምጽ የሰጡ የትዊተር ተጠቃሚዎች በጠባብ ልዩነት የትራምፕን መመለስ የደፉት በመብለጣው ትራምፕ ወደ ትዊትር ተመልሰዋል።
“የምመለስበት ምክንያት የለኝም” በሚል ትራምፕ ግን ትዊተርን ዳግም መጠቀም አልጀመሩም።