ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በአማራ ክልል የሰሜን ሸዋ እና ኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞኖች እየሆነ ያለው ምንድን ነው?
በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ውስጥ በሚገኙ የአማራ እና የኦሮሞ ብሔረሰብ አባላት መኖሪያ በሆኑ ስፍራዎች ለቀናት በዘለቀ ግጭት ምክንያት በርካታ ሰዎች መሞታቸውን እና ከፍተኛ የንብረት ውድመት መከሰቱን የአካባቢው ነዋሪዎች ተናገሩ።
ከቅዳሜ ጥር 13/2015 ዓ.ም. ጀምሮ በተከሰተው ግጭት ወደ ተለያዩ የዞኑ አካባቢዎች ተስፋፍቶ፣ ማክሰኞ ዕለትም ከዚህ በፊት በተፈጸሙ ጥቃቶች ከባድ ውድመት የደረሰባት የአጣዬ ከተማን ጨምሮ በሌሎች ስፍራዎችም ጉዳት ማድረሱን ነዋሪዎች እና አንድ የአካባቢው ኃላፊ ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ግጭቱ የተከሰተው የአማራ ክልል ዞኖች በሆኑት የሰሜን ሸዋ የኤፍራታ እና ግድም ወረዳ እንዲሁም በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን የጅሌ ድሙጋ አዋሳኝ አካባቢዎች ሲሆን እስከ ሰኞ ምሽት ድረስ በአንዳንድ ስፍራዎች ቀውሱ መቀጠሉን ነዋሪዎች ተናግረዋል።
በተጨማሪም ግጭቱ ከተቀሰቀሰበት አካባቢ ባሻገር በአቅራቢያ ወዳሉት የገጠር ቀበሌዎች መስፋፋቱን እና በተለይም ሰንበቴ እና አጣዬ ውስጥም መከሰቱን ወደ አጎራባች አካባቢዎች የሸሹ ነዋሪዎች ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ይህ ግጭት በተከሰተባቸው ቦታዎች አቅራቢያ ባሉ አካባቢዎችም የፀጥታ ስጋት መከሰቱን አንዲት የሸዋ ሮቢት ከተማ ነዋሪ ለቢቢሲ ገልጻለች።
አንዳንድ የሸዋ ሮቢት ነዋሪዎች ግጭቱ ወደ ከተማዋ ሊስፋፋ ይችላል የሚል ስጋት ቢኖራቸውም፣ ከተማዋ ውስጥ ያለው እንቅስቃሴ ላይ ግን ያስከተለው ተጽእኖ የለም ስትል ታክላለች።
በከተማዋም ንግድ፣ ትራንስፖርት እና የተለያዩ አገልግሎት መስጫዎች የተለመደ ሥራቸውን እያከናወኑ መሆናቸውን አረጋግጣለች።
የሸዋ ሮቢት አስተዳደር በአጎራባች አካባቢዎች ካለው አለመረጋጋት ጋር ይሁን በሌላ ምክንያት ባይገልጽም ከሰኞ ጥር 15/2015 ዓ.ም. ጀምሮ “ለከተማዋ ሰላም እና ፀጥታ” ሲባል ማንኛውም የባጃጅ እና የሰው እንቅስቃሴ ከምሽቱ 12 ሰዓት ጀምሮ መከልከሉን አሳውቋል።
የፀጥታ ችግር መከሰቱን ተከትሎ ከአዲስ አበባ ተነስተው ከሸዋ ሮቢት ባሻገር ወደ ደሴ እንዲሁም ከደሴ ተነስተው ከከሚሴ ባሻገር ወደ አዲስ አበባ የሚደረጉ የትራንስፖርት እንቅስቃሴዎች ከተስተጓጎሉ ቀናት መቆጠራቸውን እኚሁ የሸዋ ሮቢት ከተማ ነዋሪ ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ከትራንስፖርት በተጨማሪም በአጣዬ እና በዙሪያዋ ባሉ አካባቢዎች የስልክ ኔትወርክ በመቋረጡ ከቤተሰብ ጋር መገናኘት መቸገራቸውን ነዋሪዋ ተናግረው፣ በከተማዋ ያለውን ችግር በመሸሽ በአቅራቢያ ወዳሉ የገጠር አካባቢዎች በርካታ ሰዎች መሸሻቸውን እንደሰማች ተናግራለች።
ችግሩን ለማረጋጋት የመከላከያ ኃይል ወደ አካባቢው እንዲሰማራ በቀረበው ጥያቄ መሠረት ከባድ ውድመት እና የሰው ሕይወት መጥፋት ወዳጋጠመባቸው አካባቢዎች ይሰማራሉ ብለው ነዋሪዎች እየጠበቁ ነው።
የግጭቱ መነሻ ምክንያት ምንድን ነው?
በአካባቢው ግጭት የተቀሰቀሰበትን ሰበብ በሚመለከት ከሁለቱ ዞኖች በኩል የተለያዩ ምክንያቶች እየተሰጡ ይገኛሉ።
አንድ የአካባቢው ኃላፊ “የአማራ ልዩ ኃይል እና የፌደራል ፖሊስ አባላት በታጣቂዎች መገደላቸው ነው” ሲሉ፣ የኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን አስተዳዳር ባለሥልጣን እና ነዋሪ ደግሞ “በልዩ ኃይሉ በተወሰደ እርምጃ ሰዎች በመገደላቸው ነው” ይላሉ።
ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የአካባቢው ኃላፊ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ለቀናት ዘልቆ በአስሮቹ ለሚቆጠሩ ሰዎች ሞት እና ለውድመት ምክንያት የሆነው ግጭት የተቀሰቀሰው ቅዳሜ ጥር 13/2015 ዓ.ም. መሆኑን ያስታውሳሉ።
ጨምረውም በዚያ ዕለት ታጣቂዎች በክልሉ የፀጥታ ኃይል አባላት ላይ በፈጸሙት ጥቃት 20 በላይ የክልሉ ልዩ ኃይል፣ አምስት የፌደራል ፖሊስ አባላት እና ለጊዜው ቁጥራቸው ያልታወቁ ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን ጠቅሰው፣ በተጨማሪም የጀውሃ ቀበሌ አስተዳዳሪ መገደላቸውን ተናግረዋል።
በአማራክልል የኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን አስተዳዳሪ የሆኑት አቶ አህመድ አልይ እና አንድ ነዋሪ ደግሞ “ሸኔ ብለው የጠረጠሯቸውን፣ ነገር ግን ቤት ውስጥ ተቀምጠው ጫት ሲቅሙ የነበሩ 7 ሰላማዊ ሰዎችን የአማራ ልዩ ኃይሎች መገደላቸው" ሰበብ መሆኑን ገልጸዋል።
“ተኩስ ከተሰማ በኋላም በሕዝቡ እና በልዩ ኃይል አባላት መካከል ችግር ተፈጥሯል” ያሉት አቶ አህመድ፣ ነገሩን ለማርገብ ጥረት እየተደረገ ባለበት ጊዜ ወደ ሌሎች አካባቢዎች ግጭቱ መዛመቱን ገልጸዋል።
ቢቢሲ የግጭቱን ትክክለኛ መንስዔ ከገለልተኛ ወገን ማረጋገጥ አልቻለም።
በአካባቢው ስለተከሰተው እና ስላለው ሁኔታ ተጨማሪ ማብራሪያ ከሰሜን ሸዋ አስተዳደር እንዲሁም ከአማራ ክልል ኮምዩኒኬሽን ለማግኘት ጥረት ቢያደርግም ለጊዜው አልተሳካለትም።
የመከላከያ መሰማራት
ባለፈው ቅዳሜ የተቀሰቀሰው ግጭት ማክሰኞ ጥር 16/2015 ዓ.ም. ወደ ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ አጣዬ ከተማ ተስፋፍቶ በተለይ ከሰዓት በኋላ ውድመት መድረሱን ዘገባዎች ሲወጡ ነበር።
በከተማዋ የስልክ አገልግሎት በመቋረጡ ቢቢሲ ከአካባቢው ባለሥልጣናት እና ከከተማዋ ነዋሪዎች ማረጋገጥ ባይችልም፣ 50 ኪሎ ሜትር ርቃ በምትገኘው አጣዬ ከተማ ቤተሰብ እንዳላቸው የገለጹ የሸዋ ሮቢት ነዋሪ፣ አጣዬ ውስጥ ከባድ ተኩስ እንዳለ እና ቤቶች እየተቃጠሉ መሆናቸውን እንደሰሙ ተናግረዋል።
የአማራ ክልል፣ የአካባቢዎቹ አስተዳደሮች እና የፀጥታ አካላት ለቀናት ስለዘለቀው አለመረጋጋት እስካሁን በይፋ የሰጡት መግለጫ የሌለ ሲሆን፤ ቢቢሲ እስከ ማክሰኞ ድረስ ከሚመለከታቸው ባለሥልጣናት ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ያደረገው ተደጋጋሚ ጥረት አልተሳካም።
ነገር ግን የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን አስተዳዳሪ አቶ አሕመድ አልይ፣ ማክሰኞ ከሰዓት በኋላ በአካባቢያው ያለውን ሁኔታ በተመለከተ አንጻራዊ መረጋጋት እንዳለ እና በአካባቢው ተኩስ መቆሙን ለቢቢሲ ገልጸዋል።
“ዛሬ [ማክሰኞ] ያለው ሁኔታ በአንጻራዊነት የተሻለ ነው። የአገር መከላከያ ሠራዊት ሰኞ ማታ ጅሌ ድሙጋ እንዲሁም በሰሜን ሸዋ አካባቢ ያሉ ቦታዎች ገብቶ አረጋግቷል። ብዙ ቦታዎች ግጭት ቆሟል። ተኩስ የለም።”
ጨምረውም በሁለት አካባቢዎች ችግር የነበረ መሆኑን ገልጸው፤ እነሱም ሁለቱ የዞኑ አመራሮች የአገር ሽማግሌዎች እና ሕዝቡ ባደረገው ርብርብ ለማረጋጋት መመኮሩን በመጥቀስ “ማክሰኞ ያለው ሁኔታ ከሰኞው የተሻለ ነው። ነገ ደግሞ ከዚህ በተሻለ እንደሚሻሻል ተስፋ አለን”ብለዋል።
በዚህ አራት ቀናትን ባስቆጠረው አለመረጋጋት ምክንያት የሞቱ እና የተጎዱ ሰዎችን ቁጥር ለማወቅ አስቸጋሪ መሆኑን ቢቢሲ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች የገለጹ ሲሆን፣ ነገር ግን በርካቶች የግጭቱ ሰለባ ሳይሆኑ እንዳልቀሩ ይገምታሉ።
በአካባቢዎቹ ባለፉት ዓመታት ተመሳሳይ አለመረጋጋቶች አጋጥሞ የሰው ሕይወት እና በንብረት ላይ ከባድ ጉዳት የደረሰ ሲሆን፣ አጣዬ ከተማም የአሁኑን ጨምሮ ቢያንስ ለሦስት ጊዜ የከፋ ጥቃቶችን አስተናግዳለች።
በእነዚህ ጥቃቶች የተነሳም የከተማዋ ነዋሪዎች ለሞት፣ ለአካል ጉዳት፣ ለመፈናቀል እንዲሁም ለንብረት ውድመት መዳረጋቸው አይዘነጋም።