የሦስት ሰዎች ዘረ መል ተዋህዶ በዩናይትድ ኪንግደም የመጀመሪያው ልጅ ተወለደ

ሕጻን ልጅ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የሦስት ሰዎች ዘረ መል ውህድ የሆነው ልጅ በዩናይትድ ኪንግደም ለመጀመሪያ ጊዜ ተወለደ።

የልጁ ዘረ መል በአብዛኛው የተወሰደው ከእናት እና ከአባቱ ሲሆን፣ ሦስተኛው እና 0.1% የሚሆነው ዘረ መል ከአንዲት ለጋሽ ሴት የተወሰደ ነው።

ይህ የሦስት ሰዎችን ዘረ መል የማደባለቅ ሙከራ የተደረገው ሕጻናትን ከከፋ ሕመም ለመከላከል በተደረገ ጥናት ሥር ነው።

በዚህ መንገድ አምስት ተጨማሪ ልጆች ቢወለዱም፣ ዝርዝር መረጃው ይፋ አልተደረገም።

የማይቶኮንድሪያ በሽታዎች (Mitochondria diseases) የሚባሉት የሕመም ዓይነቶች መድኃኒት የሌላቸው ሲሆኑ ሕጻናትን በተወለዱ በቀናት ውስጥ ለሕልፈት ይዳርጋሉ።

አንዳንድ ቤተቦች በተደጋጋሚ ልጆቻቸውን ያጡ ሲሆን፣ ዘረ መል ማደባለቅ ጥንዶች ጤናማ ልጅ እንዲኖራቸው ብቸኛ አማራጭ መሆኑን አጥኚዎች ገልጸዋል።

እነዚህ ሕመሞች በሰውነት ውስጥ ያለውን እያንዳንዱን ምግብ ወደ ኃይል የሚለውጥ አሠራር በማቃወስ ለአእምሮ ጉዳት፣ ለጡንቻ ሕመም፣ ለዐይነ ስውርነት እና ለልብ ድካም ያጋልጣሉ።

ሕመሞቹ ወደ ልጆች የሚተላለፉት ከእናት ብቻ ነው። ስለዚህም ማይቶኮንድሪያ የተባሉትን ሕዋሳት ጤናማ እንቁላል ካላቸው ለጋሽ ሴቶች ጋር በማግኘት ነው ሂደቱ የሚከናወነው።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

እነዚህ ሕዋሳት የራሳቸው ዘረ መል ያላቸው ስለሆኑ ከሌላ ሴት በተለገሰ ሕዋስ አማካይነት የሚወለዱ ልጆች ከእናት እና አባታቸው በተጨማሪ የለጋሿ ዘረ መል ይኖራቸዋል ማለት ነው።

በዚህም ከትውልድ ትውልድ በሚደረግ ሽግግር ቋሚ የዘረ መል ለውጥ ይኖራል።

ከለጋሾች የሚገኘው ዘረ መል የሚጠቅመው ጤናማ የሆነ ሕዋስ ለማግኘት ሲሆን፣ የልጆች መልክ ወይም ሌሎች ከቤተሰብ የሚወረሱ ባሕሪያት ላይ ተጽዕኖ አያሳድርም።

ይህ ሂደት መጀመሪያ የተዋወቀው እዚያው ዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) ኒውካስል ውስጥ ሲሆን፣ እአአ በ2015 ሂደቱን የሚቆጣጠር ሕግ ወጥቷል።

ሕጉ ቢወጣም ዩኬ ውስጥ ወዲያው ተግባራዊ አልሆነም። ለመጀመሪያ ጊዜ ከሦስት ሰዎች ዘረ መል ልጅ የተወለደው እአአ በ2016 አሜሪካ ውስጥ ከዮርዳኖሳውያን ቤተሰቦች ነው።

በዩኬ ከወሊድ ጋር የተያያዙ ሂደቶችን የሚቆጣጠረው ባለሥልጣን እንዳለው እአአ በ2023 ግንቦት ውስጥ “ከአምስት በታች ልጆች” በዚህ መንገድ ተወልደዋል።

ትክክለኛው ቁጥር የማይገለጸው የቤተሰቦችን ደኅንነት ለመጠበቅ እንደሆነም ተገልጿል።

ጋርዲያን ጋዜጣ መረጃ በግልጽ እንዲሰጥ ከጠየቀ በኋላ ነው ስለጉዳዩ ጥቂት ነገር የተባለው።

ፕሮግረስ ኤዱኬሽናል ትረስት የተባለው ተቋም ኃላፊ የሆነችው ሳራ ኖርክሮስ “በዩኬ ጥቂት ሕጻናት በዘረ መል ልገሳ ተወልደዋል የሚለው ዜና መሰማቱ የመጀመሪያው ደረጃ ነው። የሕዋስ ልገሳ ገና ጊዜ የሚወስና ጥንቃቄ የሚፈልግ ነው” ብላለች።

ኒውካስል ውስጥ ይህን ሂደት ያከናወነው ቡድን እስካሁን ምንም ስላላለ ምን ያህል ስኬታማ እንደሆኑ እርግጠኛ መሆን አይቻልም።

ፍራንሲስ ክሪክ በተባለ የጥናት ተቋም የሚሠሩት ፕሮፌሰር ሮቢን ሎቨልባጅ “ምን ያህል የሕዋስ ልገሳው ውጤታማ እንደሆነ ማወቅ ትልቅ ነገር ነው። ልጆቹ ከሕመም ነጻ ሆነዋል ወይስ ካደጉ በኋላ ለሕመም የመጋለጥ ዕድል ይኖራቸዋል? የሚለውን ማወቅም ያስፈልጋል” ብለዋል።

በመርኅ ደረጃ አንድ ሕዋስ ሕመም ይዞ ወደ ሰውነት ከገባ በኋላ በሽታ ያሰራጫል።

በዩኬ በዚህ መንገድ በዓመት እስከ 150 ልጆች ሊወለዱ እንደሚችሉ ይገመታል።