ተጥሎ የተገኘውን ጨቅላ ጡት በማጥባት የታደጉት የድሬዳዋ ፖሊስ አባል

ረዳት ሳጅን ቤተልሔም ምትኩ በድሬዳዋ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ውስጥ ፖሊስ መሬት በሚባለው ፖሊስ ጣቢያ መርማሪ ናቸው።

ሰሞኑን ከተወለደ አንድ ወር የሆነውን እና ከድልድይ ስር ተጥሎ የተገኘውን ልጅ ጡታቸውን በማጥባት “ሕይወቱን መታደጋቸውን” የፖሊስ መምሪያው በማኅበራዊ ትስስር ገጹ ላይ አስፍሯል።

ክስተቱ ያጋጠመው ግንቦት 10/2015 ዓ.ም. በድሬዳዋ ከተማ 09 ቀበሌ ገራዳ በሚባል አካባቢ ባለ ድልድይ ስር የሕጻን ልጅ ለቅሶ የሰሙ ሰዎች ልጁን አንስተው ወደ ቤታቸው ወሰዱ።

የዚህን ሕጻን ልቅሶ ሰምተው ወደ ድልድዩ በማምራት ያነሱት የአካባቢው ነዋሪ የሆኑት ወ/ሮ ፋጡማ መሆናቸውን ፖሊስ በመግለጫው ላይ ጠቅሷል።

የፖሊስ መግለጫም አክሎ ወ/ሮ ፋጡማ ድልድዩ ጋር ሲደርሱ ባዩት ነገር ደንግጠው ነበር ብሏል።

ምክንያታቸው ደግሞ ከድልድዩ ስር ሲያለቅስ የነበረው ከተወለደ ከአንድ ወር ያልበለጠው በጨርቅ ተጠቅልሎ የተቀመጠ ጨቅላ መሆኑን መረዳታቸው ነው።

ከዚያም ወ/ሮ ፋጡማ ሕጻኑን ከተጣለበት አንስተው ወደ ቤት ይዘውት ሔዱ።

ነገር ግን ልጁ ሊጠባው የሚችለው ምንም ነገር ቤታቸው ውስጥ ስላልነበር ሕጻኑ ምግብ ሳይወስድ ማደሩን ለፖሊስ አስረድተዋል።

በማግስቱ ግንቦት 11/2015 ዓ.ም. እኚህ ነዋሪ ሕጻኑን ይዘው በአቅራቢያቸው ወደሚገኘው የፖሊስ ጣቢያ አመሩ።

ወ/ሮ ፋጡማ ሕጻኑን ይዘው ፖሊስ መምሪያው ሲደርሱ የፖሊስ መሬት ፖሊስ ጣቢያ መርማሪ የሆኑት ረዳት ሳጅን ቤተልሔም ምትኩ የዕለት ሥራቸው ላይ ነበሩ።

ረዳት ሳጅን ቤተልሔም ከቢቢሲ ጋር ባደረጉት ቆይታ ሕጻኑ ተጥሎ የተገኘ መሆኑን ከፋጡማ በሰሙ ጊዜ ስሜታቸው መረበሹን ተናግረዋል።

“ተጥሎ የተገኘ ልጅ ነው ባሉኝ ጊዜ ውስጤ ተረበሸ። ምግብም ሳያገኝ ስለቆየም ደካክሞ ነበር። የሚበላ ነገር እንዲሰጠው ስጠይቅ ይዛው የመጣችው ሴት ምንም እንደሌላት እና ሌሊትም ጡት ሳይጠባ ማደሩን ነገረችኝ” ብለዋል።

በዚህም ፖሊሷ የጨቅላውን ሕይወት ለመታደግ ወሰኑ።

“‘ይህ ሕጻን አይኔ እያየ ሕይወቱ ማለፍ የለባትም’ ብዬ፣ እናትነቴ ገፋፍቶኝ ጡቴን ማጥባት እንዳለብኝ አሰብኩ” ብለው እንዴት እንዳጠቡት አስረድተዋል።

ተጥሎ የተገኘው ልጅ ጡት ከጠባ በኋላ ነቃ ማለቱን ፖሊሷ ይናገራሉ።

ሕጻኑ አሁን በተሻለ ጤንነት ላይ እንደሚገኝ የድሬዳዋ ፖሊስ በፌስቡክ ገፁ ላይ ጠቅሷል።

ረዳት ሳጅን ቤተልሔም የሁለት ዓመት ሕጻን ልጅ እንዳላቸው እና ልጃቸውን ስለሚያጠቡ ተጥሎ የተገኘውን ልጅ ማጥባታቸውን ተናግረዋል።

የድሬዳዋ ፖሊስ ይህንን መረጃ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ካጋራ በኋላ ከተለያዩ ወገኖች ረዳት ሳጅን ቤተልሔም ለፈጸሙት ሰብአዊ ተግባር ሙገሳ እየተቸራቸው ነው።

የድሬዳዋ ፖሊስ ጉዳዩን አስመልክቶ በፌስቡክ ገፁ ላይ ባሰፈረው ሀሳብ ስር በርካታ የገፁ ተከታዮች የፖሊስ አባሏን ሰብዓዊነት አድንቀዋል።

“በኃላፊነት ስሜት የማገልገል ማሳያ ናት፣ የአንድን ሕጻን ሕይወት መታደግ ጀግንነት ነው፣ እንዲሁም እውቅና እና ሽልማት ይገባታል. . .” የሚሉ አስተያየቶች ተሰጥተዋል።