የትግራይ ቤተ ክህነት 10 ኤጲስ ቆጶሳትን ሊሾም መሆኑ ተገለጸ

የትግራይ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ጠቅላይ ቤተ ክህነት ሥራ አስፈጻሚዎች በክልሉ እና በውጭ አገራት ለሚገኙ ሃገረ ስብከቶች 10 ኤጲስ ቆጶሳትን ለመሾም መወሰናቸውን አስታወቁ።

መንበረ ሰላማ ከሳቴ ብርሃን ጠቅላይ ቤተ ክህነት ማክሰኞ ግንቦት 15/ 2015 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ የሚሾሙት ኤጲስ ቆጰሳትን ስፍራዎችን ጠቅሷል።

በዚህም መሠረት በትግራይ ክልል በደቡብ ምዕራብ፣ በምዕራብ እና በደቡብ ትግራይ ሃገረ ስብከቶች እንዲሁም በውጭ አገራት በሰሜን አሜሪካ፣ በአውሮፓ፣ በአውስትራሊያ፣ በካናዳ እና በመካከለኛው ምሥራቅ አገራት እንደሆነ ተገልጿል።

የመንበረ ሰላማ ከሳቴ ብርሃን ጠቅላይ ቤተ ክህነት ለሁለት ቀናት ግንቦት 14 እና 15 ያደረገውንም ጉባኤ ተከትሎ እዚህ ውሳኔ ላይ መድረሱንም ነው መግለጫው ያተተው።

በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚገኙ ምዕመናን “ሙሉ መንፈሳዊ አገልግሎት” ለማግኘትም ካላቸው ፍላጎት የተነሳ ኤጲስ ቆጶሳት እንዲሾሙላቸው በተደጋጋሚ ጥያቄ መቅረቡን መግለጫው ጠቅሶ ውሳኔውም ያንን መሠረት አድርጓል ብሏል።

ሹመት የተቀበሉት ኤጲስ ቆጶሳት በቅርቡ ሥራቸውን እንደሚጀምሩም መግለጫው አክሏል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ሲኖዶስ በአሁኑ ሹመት ላይ የሰጠው መግለጫ ባይኖርም ከዚህ ቀደም የትግራይ ቤተ ክህነት በአሜሪካ፣ በአውሮፓ፣ በካናዳ እና በአውስትራሊያ በሚገኙ ሃገረ ስብከቶች ለሚገኙ ምዕመናን ኤጲስ ቆጶሳት መሾሙን ባስታወቀበት ወቅት ተቃውሞ መግለጫ ማውጣቱ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ሲኖዶስ በትግራይ ቤተ ክህነት ላይ የቤተ ክርስቲያኗን ጸንቶ የቆየ ተቋማዊ አንድነት እና ነባር መዋቅራዊ አደረጃጀትን በሚንድ መልኩ “መንበረ ሰላማ የትግራይ ጠቅላይ ቤተ ክህነት” ጽ/ቤት የሚል አዲስ መዋቅር ማቋቋሙ ሕገወጥ ነው ብሎ ነበር።

ሲኖዶሱ ከዚህ በተጨማሪም የቤተ ክርስቲኗን ቀኖናዊ እና አስተዳደራዊ አሠራርን በጣሰ ሁኔታ በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ሊቃነ ጳጳሳት ተመድበው በሚሠሩባቸው የውጭ ዓለማት አህጉረ ስብከት ላይ ሊቃነ ጳጳሳት ከቀኖና ውጪ ራሳቸውን በራሳቸው መመደባቸው እንዳሳዘነውም ገልጿል።

የትግራይ ቤተ ክህነት እና የቅዱስ ሲኖዶስ ግንኙነት መሻከር

በትግራይ ቤተ ክህነት እና በኢትዮጵያ ሲኖዶስ መካከል ግንኙነት መሻከር የጀመረው ከሁለት ዓመት በፊት በትግራይ የተቀሰቀሰውን ጦርነት ተከትሎ ነው።

የትግራይ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የእምነት አባቶች ከኢትዮጵያ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ወጥተው የትግራይ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ለመመሥረት መወሰናቸውን ማስታወቃቸው ይታወሳል።

የትግራይ ሃይማኖት አባቶች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሲኖዶስን ለፌደራሉ መንግሥት በመወገን የሚከሷት ሲሆን፣ ንጹሃን እና ካህናት ሲገደሉ፣ የዕምነት ተቋማት ላይ ውድመት ሲደርስ፣ ቅርሶች ሲዘረፉ ሲኖዶሱ ዝምታን መርጧል ብለዋል።

በፕሪቶሪያ የተደረሰውን ስምምነት ተከትሎም በቤተ ክህነት መካከል የተፈጠረውን ሁኔታ በዕርቅ ለመፍታት ቢሞከርም ፍሬ አላፈራም።

የትግራይ ቤተ ክህነት ሹመት ይፋ የሆነው ሰኞ ግንቦት 14/ 2015 የተጠናቀቀውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ርክበ ካህናትን አስመልክቶ በዛሬው ዕለትም ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ መግለጫ እንደሚሰጡ ከሚጠበቅበት አንድ ቀን ቀደም ብሎ ነው።

በዚህ ጉባዔ ላይ አቡነ ማትያስ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉ ሲሆን በዚህም “በትግራይና በኦሮሚያ ያጋጠሙን ፈተናዎች ከቤተ ክህነት አልፈው የሕዝብም ጭምር እየሆኑ ስለመጡ የሕዝቡን ጥያቄ በትክክል በማዳመጥ ሃይማኖቱን እና ቀኖናውን በጠበቀ መልኩ በጥበብና በፍቅር ጥያቄያቸውን አክብረን መቀበል ያሻል” ብለው ነበር።

በጉባኤው በሁለተኛው ቀንም በትግራይ እና ኦሮሚያ አህጉረ ስብከቶች የነበሩትን ችግሮች መነሻ በማድረግ ውይይት መደረጉ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን አስታውቃለች።

በዚህም መሠረት በትግራይ ክልል የተፈጠረውን ችግር ለመፍታት የትግራይ አባቶች እና አባላቱን በአካል የሚያነጋግሩ የእምነቱ አባቶች ተመርጠው ኃላፊነት መሰጠቱን እንዲሁም ተቋርጦ የነበረው በጀት እንዲለቀቅ ውሳኔ ላይ መደረሱ ተገልጿል።

ቅዱስ ሲኖዶሱ በዚህ ውሳኔው ችግር ላለባቸው እና አስፈላጊ በሆኑባቸው አህጉረ ስብከቶች ዘጠኝ አዳዲስ ኤጲስ ቆጶሳት በዕጩነት ቀርበው በመጪው ሐምሌ 9/2015 ዓ.ም. ይሾማሉ ተብሏል።

ከእነዚህ ከሚታጩት ዘጠኝ ኤጲስ ቆጶሳት መካከል ሰባቱ በኦሮሚያ እንዲሁም ሁለቱ በደቡብ ኢትዮጵያ ለሚገኙ አህጉረ ስብከቶች የሚመደቡ መሆናቸው ተገልጿል።

ባለፈው የካቲት ወር አቡነ ሳዊሮስን ጨምሮ ሦስት ጳጳሳት ከቤተ ክርስቲያኗ እውቅና ውጪ 25 ኤጲስ ቆጶሳትን በመሾማቸው ውዝግብ እና ከባድ ቀውስ ተከስቶ የነበረ ሲሆን፣ በዚህም ሳቢያ በተለያዩ አካባቢዎች በፈጠሩ ችግሮች የሰዎች ሕይወት ጠፍቷል።