ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አውስትራሊያዊው ባለ ሃብት ሥራ አጥነት በእጥፍ ሊጨምር ይገባል ማለቱ ቁጣ አስነሳ
ከአውስትራሊያ ሃብታሞች አንዱ ቲም ጉነር የሥራ አጦች ቁጥር ሊጨምር ይገባል ሲል ያደረገው ንግግር ቁጣ አስነስቷል።
ሥራ ያላቸው ‘ትቢተኛ’ ሰዎች ምን ያህል ዕድለኛ እንደሆኑ እንዲረዱ ሲባል ሥራ አጥነት በእጥፍ ሊጨምር ይገባል ማለቱ ነው በርካቶችን ያስቆጣው።
“ምጣኔ ሃብቱ ታሞ ማየት አለብን” ብሏል ባለ ሃብቱ ቲም።
ቀድሞ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማዘውተሪያ ባለቤትና አሁን የሪልስቴት ባለቤት የሆነው ቲም፣ ከዚህ በፊት ወጣቶች አላግባብ ወጭ ስለሚያወጡ የቤት ባለቤት መሆን አይችሉም ብሎ ነበር።
አስተያየቱን ከ23 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ተመልክተው ተችተውታል።
የ41 ዓመቱ ባለሃብት እንዳለው በኮሮናቫይረስ ምክንያት የሠራተኞች አመለካከት እና የሥራ ሥነ ምግባር ተበላሽቷል።
የቤት ሠሪዎች ጉባኤ ላይ ባደረገው ንግግር ምሳሌ የሰጠው የግንባታ ባለሙያዎችን ነው።
የታየው የአመለካከት ለውጥ የግንባታ ዘርፉን እንደጎዳውና በአገሪቱ የቤት እጥረት እስዳስከተለ ገልጿል።
አሁን በአውስትራሊያ ያለው 3.7% ሥራ አጥነት ወደ 40-50% ከፍ ማለት አለበትም ብሏል። ይህ ከሆነ “በሥራ ዘርፉ ያሉ ትዕቢተኞች” ይቀንሳሉ ብሏል።
በባለ ሃብቱ ንግግር መሠረት ከ200,000 በላይ ሰዎች ሥራ አጥ ይሆናሉ።
“ሠራተኞች የእነሱ መኖር ለቀጣሪዎች ታላቅ ዕድል እንደሆነ ይሰማቸው ጀምሯል። ሠራተኞች የሚሠሩት ለቀጣሪዎቻቸው እንደሆነ ልናስታውሳቸው ይገባል” ብሏል።
ይህን ንግግር ያደረገው የአውስትራሊያ ተቋማት በቅጥር ሁኔታና ከቤት መሥራትን በተመለከተ ውዝግብ ውስጥ ባሉበት ወቅት ነው።
ለቀጣሪዎች ከሚገባው በላይ አለመሥራት (quiet quitting) እንዲሁም የተሻለ የሥራ ሕይወትና ደመወዝ ያለው ሥራ መምረጥ (lazy-girl jobs) የብዙዎችን ትኩረት የሳቡ አዲስ እሳቤዎች ናቸው።
የቲምን ንግግር የአገሪቱ የሕዝብ ተወካዮችም ኮንነዋል። የሌበር የሕዝብ ተወካዩ ጀሮሜ ላክሴል “ፊልም ላይ የሚታይ ክፉ ገጸ ባህሪ የሚለው ነገር ነው የተናገረው” ብለዋል።
የሊበራል ሕዝብ እንደራሴ ኪት ዋላሀን ደግሞ “ከእውነታው እጅግ የራቀ ንግግር” ብለውታል።
“ሥራ አጥነት የቁጥር ጉዳይ አይደለም። ሰዎችን ቤት አልባ የሚያደርግና እርዳታ ጠባቂ የሚያደርግ ነው” ሲሉም አክለዋል።
አሜሪካዊቷ አሌክሳንድሪያ ኦካሲዮ-ኮርቴዝም “የመሥሪያ ቤት ኃላፊዎች ደመወዛቸውን አሳድገው ሠራተኞቻቸው የሚከፈላቸው እያነሰ መጥቷል” ብላለች።
የቲምን ንግግር የደገፉም አሉ። ባለ ሃብቱ ወደ 598 ሚሊዮን ዶላር ገደማ እንደሚያንቀሳቅስ ይገመታል።
አያቱና የቀድሞ አለቃው በሰጡት ብድር እንዴት ንግዱን ስኬታማ እንዳደረገ ከዚህ ቀደም ተናግሯል።