ሩሲያ በሶሪያ የጦር ሰፈር ያላትን መሣሪያ ማንቀሳቀስ ጀመረች

ሩሲያ ከሶሪያ ከፍተኛ መጠን ያለው ወታደራዊ መሣሪያ እያዘዋወረች ሲሆን ይህም ከአገሪቱ በከፊል ለመውጣት መዘጋጀቷን ያሳያል ሲሉ ተንታኞች ገልጸዋል።

የሳተላይት ምስሎች እንደሚያሳዩት ከሆነ በሩሲያ በምትቆጣጠረው ወደብ እና በምዕራብ ሶሪያ የአየር ኃይል ወታደራዊ ተሽከርካሪዎች መከማቸታቸውን ያሳያሉ።

ባለፉት ቀናትም የትራንስፖርት አውሮፕላኖች ወደ አገሪቱ ገብተው የወጡ ይመስላል።

ቢቢሲ ቬሪፋይ ወደ እነዚህ የጦር ሰፈር የሚሄዱ የሩሲያ ወታደራዊ መኪናዎች ረዣዥም ሰልፍ ይዘው የሚያሳዩ ቪዲዮዎችን ቦታ ለመለየት ችሏል።

ይህ ሩሲያ ኃይሏን ለመቀነስ ወይም ሙሉ ለሙሉ ለማስወጣት መዘጋጀቷን ያመለክታል ሲል የጦርነት ጥናት ተቋም ገልጿል።

መቀመጫውን በዋሽንግተን ያደረገው ተቋም አክሎም ወታደራዊ ተሽከርካሪዎችን ወደ ጦር ሰፈራቸው ማዛወር ሞስኮ ከአዲሱ መንግስት ጋር በደማስቆ እስክትደራደር የተወሰደ የጥንቃቄ እርምጃ ሊሆን ይችላል ብሏል።

በበሽር አል አሳድ የግዛት ዘመን ሩሲያ በሶሪያ ውስጥ ከፍተኛ ወታደራዊ ተሳትፎ የነበራት ሲሆን በ2011 የእርስ በእርስ ጦርነት ከተቀሰቀሰ በኋላም መሪው በሥልጣን ላይ እንዲቆዩ አግዛለች።

ሁለቱ ዋና ዋና የጦር ሰፈሮችም አሏት። በታርቱስ የሚገኘው ወደብ በ1970ዎቹ በሶቭየት ኅብረት የተቋቋመ እና ከዚያም በ2012 በሩሲያ የተስፋፋው እና ዘመናዊው እና ከ2015 ጀምሮ አገልግሎት ላይ የዋለው እና ህሜሚም የሚገኘው የአየር ማረፊያ አሳድን በመደገፍ በመላው ሶሪያ የአየር ጥቃት ለመሰንዘር ተጠቅማበታለች።

ሁለቱም ለሩሲያ ቁልፍ ስትራቴጂካዊ መሠረት ሆነዋል። ይህንን ተጠቅማ ወደ መካከለኛው ምሥራቅ፣ ሰሜን አፍሪካ እና የሜዲትራኒያን ባሕር በቀላሉ መድረስ ችላለች።

የአሳድ ውድቀት ግን ሩስያ በሶሪያ ስለሚኖራት የወደፊት ዕጣ ፈንታ ላይ ጥያቄ አስነስቷል። ሞስኮ ከአዲሱ አገዛዝ ጋር ለመደራደር እያሰበች ነው።

ሰኞ ዕለት የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ "የመጨረሻ ውሳኔ" አልተደረሰም። ሩሲያ "አሁን በሶሪያ ውስጥ ያለውን ሁኔታ ከሚቆጣጠሩት ኃይሎች ተወካዮች ጋር ተገናኝታለች" ብለዋል።

ቢቢሲ ቬሪፋይ የፕላኔት ላብስ የሳተላይት ምስሎችን በመጠቀም የህሜሚም የአየር ኃይል እንቅስቃሴን ሲከታተል ቆይቷል።

ወታደራዊ ማጓጓዣ አውሮፕላኖችን ያሳተፈ እና ያልተቋረጠ የእንቅስቃሴ ምልክቶች አሉ። ንብረቶችን ከሶሪያ ለማውጣት የሚያገለግሉ ሁለት ትላልቅ አንቶኖቭ ኤኤን-124 አውሮፕላኖች አርብ ዕለት በስፍራው ታይተዋል።

እስከ ማክሰኞ ድረስ ቢቆዩም ረቡዕ ጠዋት ላይ ሁለት ትላልቅ አውሮፕላኖች ወደ ጣቢያው ደርሰዋል።

በማክስር ቴክኖሎጅ የተነሱት ተጨማሪ ምስሎች እንዳሳዩት ደግሞ እሁድ ዕለት በአየር ኃይሉ በደርዘን የሚቆጠሩ ወታደራዊ ተሽከርካሪዎች ቆመው ከመታየታቸውም በላይ ሩሲያ ሠራሽ የሆነው ኢሊዩሺን አይኤል-76 ወታደራዊ ማመላለሻ አውሮፕላን በስፍራው ታይቷል።

ቢቢሲ ቬሪፋይ በአውሮፕላን መከታተያ ድረ-ገጽ በሆነው ፍላይትራዳር24 አማካኝነት አንዱን የሩሲያ አንቶኖቭ ኤኤን-124 ማክሰኞ ዕለት ተከታትሏል።

በይፋ የሚገኘው መከታተያው መረጃ እንደሚያሳየው አውሮፕላኑ በሩሲያ አየር ክልል አድርጎ በሶሪያ አቅጣጫ እየተጓዘ አሳይቷል።

ከዚያም ከሶሪያ የባሕር ጠረፍ በስተምዕራብ ከህሜሚም አየር ኃይል ሲደርስ የራዳር መከታተያው ጠፋ። በመቀጠልም ከስድስት ሰዓታት በኋላም ወደ ሰሜን ሲመለስ ይታያል።

የማኬንዚ ኢንተለጀንስ የስለላ ኃላፊ ዴቪድ ሄትኮት እንዳሉት ከሆነ የአሳድ መንግሥት በፍጥነት በመውደቁ ሩስያ ንብረቷን ለማውጣት የሚበቃ ዕቅድ ነበራት ተብሎ አይታሰብም።

በአየር ኃይሉ የሚደረገውን እንቅስቃሴ "ያልተለመደ" ሲሉ ገልጸው፤ ይህም ሩሲያ ጥቂት መሣሪያዎችን በጣብያው እያከማቸች እና አንዳንድ መሣሪያዎችን እና ወታደሮችን ከሶሪያ ለማስወጣት በዝግጅት ላይ እንደምትገኝ ጠቁመዋል።

የቀድሞ የባሕር ኃይል መኮንን እና የመከላከያ ተንታኝ የሆነው ታይፉን ኦዝበርክ በበኩሉ ምስሉ "ሩሲያ ከሶሪያ የምትወጣበትን የመጀመሪያ ምልክቶችን ያሳያል" በማለት ተስማምተዋል።

"የአይኤል-76 አውሮፕላኖች መገኘት፤ የሩሲያ መርከቦች በታርቱስ ውስጥ አለመኖራቸው እና የተደራጁ ተሽከርካሪዎች እና መሣሪያዎች ቅድመ ዝግጅት ይህንን መደምደሚያ ያጠናክራሉ" ብለዋል።

ቢቢሲ ቬሪፋይ ባለፈው ሳምንት የሩስያ የጦር መርከቦች ታርቱስ ወደብን እንዴት ጥለው እንደወጡ ዘግቧል። ለጊዜው በዓለም አቀፍ ውሃ ላይ እንደሚገኙ ተንታኞች ጠቁመዋል።

እነዚያ መርከቦች በቦታቸው ባይመለሱም ግን ባለፉት ጥቂት ቀናት ከ 100 በላይ ወታደራዊ ተሽከርካሪዎች ወደ ጣቢያው መግባታቸውን የሳተላይት ምስሎች ያሳያሉ።

ሄትኮት እንደተናገሩት ከሆነ ተሽከርካሪዎቹ ለመልቀቅ እየተዘጋጁ ያሉ ሊሆን ቢችልም የመጫኛ ክሬኖች ባለመኖራቸው ይህ በፍጥነት ሊሆን የማይችል ነገር ነው።

የቅርብ ጊዜ ምስሎች በእንቅስቃሴ ላይ ያሉ ግዙፍ የሩሲያ ተሽከርካሪዎች ሰልፍ ይዘው አሳይተዋል። በዚህም በመላ አገሪቱ ካሉ ሌሎች የሩሲያ ማዕከሎች እንዲዘዋወሩ ስለመደረጉ ፍንች ሰጥቷል።

ቢቢሲ ቬሪፋይ ቪዲዮዎቹን በመርመር ወደ ሰሜን አቅጣጫ ወደሚገኙት የጦር ሰፈሮች እየሄዱ እንደሆነ ለመለየት ችሏል።

በኤክስ ላይ የታተመው የ80 ሰከንድ ቪዲዮ ከሆምስ በስተደቡብ 30 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኙትን የሩሲያ ተሽከርካሪዎች ረዥም ሰልፍ ይዘው ያሳያል።

በሌላ ቪዲዮ ደግሞ ከደማስቆ 70 ኪሜ ርቀት ላይ በሚገኘው በተመሳሳይ አውራ ጎዳና ላይ የሩሲያ ተሽከርካሪዎችን ሰልፍ አሳይቷል።

"ሩሲያ አሁን ደማስቆ ከመውደቋ በፊት በመላ አገሪቱ ወደ መቶ የሚጠጉ ጣብያዎች ላይ ተሰማርተው የነበሩትን የጦር ክፍሎችን እና ወታደራዊ ቁሳቁሶችን እያስወጣች ነው" ሲሉ በመካከለኛው ምሥራቅ የሶሪያ ፕሮግራም ተመራማሪው አንቶን ማርዳሶቭ ተናግረዋል።