አደገኛ የተባለው የኤምፖክስ ቫይረስ ዝርያ ለመጀመሪያ ጊዜ አፍሪካን ተሻግሮ ስዊድን ተገኘ

የስዊድን ባለሥልጣናት አደገኛ የተባለ የኤምፖክስ (የዝንጀሮ ፈንጣጣ) ዓይነት ያለበት ሰው ማግኘታቸውን ይፋ አደረጉ።

ይህ የኤምፖክስ አደገኛ የተባለው ዝርያ ከአፍሪካ ውጭ ሲታይ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።

የስዊድን ጤና ጥበቃ ኤጀንሲ እንዳለው ግለሰቡ በበሽታው የተያዘው አፍሪካ ውስጥ ቆይታ አድርጎ ከተመለሰ በኋላ ነው። ኤምፖክስ ክሌድ 1 የተሰኘው የበሽታው ዝርያ አፍሪካ ውስጥ እየተስፋፋ ነው።

የዓለም ጤና ድርጅት የኤምፖክስ ወረርሽኝ በአንዳንድ የአፍሪካ ሀገራት መታየቱን ተከትሎ ጉዳዩን አስቸኳይ የማኅብረሰብ ጤና ስጋት ነው ብሎ ካወጀ በኋላ ነው ስዊድን ውስጥ ዜናው የተሰማው።

ወረርሽኙ ለመጀመሪያ ጊዜ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ውስጥ በታየ ወቅት በበሽታው 450 ሰዎች የሞቱ ሲሆን ቀጥሎ ወደ ማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ ተስፋፍቷል።

የስዊድን ጤና ጥበቃ ኤጀንሲ ጊዜያዊ ኃላፊ ኦሊቪያ ዊግዜል፤ በበሽታው የተያዘው ግለሰብ ስቶክሆልም አካባቢ እንክብካቤ እየተደረገለት ነው፤ ይህ ማለት ግን በሽታው ስዊድን ውስጥ ሊስፋፋ አይችልም ማለት አይደለም ብለዋል።

“በበሽታው የተያዘው ግለሰብ አፍሪካ ውስጥ ነበር። ኤምፖክስ ክሌድ 1 አፍሪካ ውስጥ ተስፋፍቷል” ሲሉ በጋዜጣዊ መግለጫቸው ተናግረዋል።

ከዚህ ቀደም መንኪፖክስ ወይም የዝንጀሮ ፈንጣጣ ተብሎ ይጠራ የነበረው ኤምፖክስ በንክኪ የሚተላለፍ ነው። በወሲብ፣ በቆዳ ለቆዳ ንክኪ እንዲሁም በንግግር አሊያም ወደ ውጭ በምንተነፍስበት ወቅት ወደ ሌሎች ሰዎች ሊተላለፍ ይችላል።

በሽታው እንደ ጉንፋን ዓይነት ምልክት እንዲሁም ቆዳ ላይ የሚታይ ሽፍታ ሊያሳይ ይችላል። በሽታው ገዳይ ነው። ከ100 ሰዎች በአማካይ አራቱን ሊገድል ይችላል።

ኤምፖክስ ‘ትሮፒካል ሬይንፎሬስት’ በሚባሉት እንደ ምዕራባዊ እና ማዕከላዊ አፍሪካ ሀገራት በብዛት የሚታይ ሲሆን በየዓመቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ይያዛሉ።

ባለፈው ነሐሤ ይፋ የተደረገው ክሌድ 1ቢ የተባለው የበሽታው ዓይነት ከሌሎቹ ሲነፃፀር አደገኛ እና ገዳይ ነው።

ሁለት ዓይነት የክሌድ 1 ኤምፖክስ ወረርሽኝ ዓይነቶች አሉ። ስዊድን ውስጥ በበሽታው የተያዘው ግለሰብ ክሌድ 1ቢ የተባለው ነው የተገኘበት።

ኤምፖክስ ክሌድ 1ቢ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ለመጀመሪያ ጊዜ ከታየ በኋላ ቡሩንዲ፣ ኬንያ እና ሩዋንዳ ውስጥ መገኘቱ ተዘግቧል።

በአውሮፓውያኑ 2022 ክሌድ 2 የተባለው የኤምፖክስ ወረርሽኝ የኅብረተሰብ ጤና አደጋ ተብሎ ከታወጀ በኋላ በሽታው መካከለኛ መሆኑ ተነግሯል። በወቅቱ ስዊድን ውስጥ 300 ሰዎች በበሽታው መያዛቸው ተዘግቦ ነበር።

የዓለም ጤና ድርጅት እና የአውሮፓ ሕብረት ከስዊድን ጤና ባለሥልጣን ጋር አብረው እየሠሩ እንደሆነ አሳውቀዋል።

“በሚቀጥሉት ቀናት ክሌድ 1 በሌሎች የአውሮፓ ሀገራትም ሊታይ ስለሚችል” ሀገራት ልክ እንደ ስዊድን አፋጣኝ እርምጃ እንዲወስዱ እና በግልፀኝነት ይፋ እንዲያደርጉ ሕብረቱ አሳስቧል።

የፖክስ ቫይረስ አጥኚ የሆኑት ዶክተር ዮናስ አልባርናዝ በሽታው ከአፍሪካ ውጭ መታየቱ እጅግ አስጊ ነው “ምክንያቱም ምን ያክል እንደተስፋፋ አናውቅም” ማለት ነው ይላሉ።

የዓለም ጤና ድርጅት በሽታው ዓለም አቀፍ የጤና ቀውስ ተብሎ መታወጁን ተከትሎ በስፋት ለተጠቁ አካባቢዎች ድጋፍ ለማድረግ እርዳታ ይደረጋል የሚል ተስፋ አለው።

ክሌድ 1ቢ የተባለው የኤምፖክስ ወረርሽኝ አፍሪካ ውስጥ ገዳይ ቢሆንም አውሮፓ ውስጥ ካለው የተሻለ የጤና አገልግሎት አኳያ ስዊድን ውስጥ ገዳይ ሊሆን እንደማይችል ይጠበቃል።

የአውሮፓ ሕብረት የበሽታ ቁጥጥር እና መከላከል ማዕከል እንደገለጠው አንድ ሰው በቫይረሱ ከተያዘ በኋላ ባሉት ከ6-13 ቀናት ውስጥ ምልክት የሚያሳይ ሲሆን ትኩሳት፣ ራስምታት፣ የቆዳ ማሳከክ እና ጉሮሮ መከርከር እንዲሁም መገጣጠሚያ ላይ የሚስተዋል ሕመም ምልክቶቹ ናቸው።

ብዙውን ጊዜ በበሽታው የተያዙ ሰዎች መካከለኛ እና ዝቅተኛ የተባሉ ምልክቶች የሚያሳዩ ሲሆን ቀጥሎ ሙሉ በመሉ ይድናሉ። ነገር ግን የበሽታ መከላከል አቅማቸው የደከመ ሰዎች አደጋ ላይ ሊወድቁ ይችላሉ።

ምንም እንኳ በሽታው ከአፍሪካ ውጭ መገኘቱ ቢያስደነግጥም የጤና ባለሙያዎች ይህ ሊሆን እንደሚችል ጠርጥረው ነበር።