ቁመትን በቀዶ ህክምና በ8 ሴንቲ ሜትር ለማስረዘም የተከፈለ ከባድ መስዋዕትነት

ማስጠንቀቂያ፦ ይህ ጽሁፍ አንባቢዎችን ሊረብሹ የሚችሉ የህክምና ዝርዝሮችን ይዟል።

የ49 ዓመቷ እሌይን ፋኦ በሁለቱም እግሮቿ ታፋ ላይ ያሉ ጠባሳዎች ጎልተው ይታያሉ።

እነዚህ ጠባሳዎች ቁመቷን ለማስረዘም በሚል እግር የማስረዘም ቀዶ ህክምና ያመጣቸው መዘዞች ናቸው።

ቁመቴን ያስረዝመዋል ብላ ያሰበችው ቀዶ ህክምና በአሰቃቂ ሁኔታ ሕይወቷን በሰቆቃ እንዲሞላ አድርጎታል።

እሌይን ከአውሮፓውያኑ 2016 ጀምሮ አምስት ያህል ቀዶ ህክምና አድርጋለች። ሦስት የአጥንት ንቅለ ተከላ አድርጋለች እንዲሁም ሕይወቷን በሙሉ ያጠራቀመችው ጥሪቷንም ለዚሁ አውላለች።

ቀዶ ህክምናው ባልታሰበ ሁኔታ በአሰቃቂ መልኩ መሄዱን ተከትሎም ዶክተሯን ከሳ ፍርድ ቤት ብትመላለስም ሂደቱ ማንም ተጠያቂ ባልነበት ሁኔታ ተቋጭቷል።

በዓመታት ውስጥ የከፉ ሁኔታዎች የገጠሟት ሲሆን፣ በአንድ ወቅት በአጥንቷ ውስጥ ማያያዣ ተብሎ የገባው ሚስማር ተሰብሯል።

እግሯ ከውስጥ በማይጠፋ እሳት እየተጠበሰ እንደሆነ ያህል ለማያቋርጥ ህመም እና ስቃይ ተዳርጋ ነበር።

“ጉዞዬ በውጣ ውረድ የተሞላ እና በእሳት የተፈተነ ነው፤ ነገር ግን ተርፌ እዚህ ደርሻለሁ” ትላለች እሌይን።

ቀዶ ህክምናውን ያከናወኑት ዶክተር እሷ የምታቀርብባቸውን የሙያ ቸልተኝነት ክስ የሚክዱ ሲሆን፣ ይህ ችግር የተፈጠረው በቀዶ ህክምናው አሉታዊ ጎኖች እንዲሁም ራሷ በፈጠረቻቸው ምክንያቶች ነው ይላሉ።

ስለ ቀዶ ህክምናው አሉታዊ ጎኖች ቀድሞ ማስጠንቀቂያ ተነግሯት ነበር ሲሉም ይገልጻሉ።

እሌይን አጠር ያለ ቁመቷን ሁልጊዜም ትጠላው ነበር።

“በ12 ዓመቴ ከብዙ ታዳጊዎች ረዘም ያልኩ ነበርኩ። ሆኖም በ14 ዓመቴ ከሁሉም አጭር ሆንኩኝ። ዋናው ትኩረቴ ቁመቴ ሆነ፤ ጭራሽ አባዜ ሆነብኝ። ረዥም መሆን ማለት የተሻለ፣ የበለጠ ቆንጆ ነው አልኩኝ። ረዣዥም ሰዎች በሕይወት ላይ የበለጠ ዕድል እንደሚከፈትላቸው ይሰማኝ ጀመር” ስትል ታስረዳለች።

በዚህ በልጅነት እድሜዋ የተጀመረው ረዥም የመሆን አባዜ ትልቅ ስትሆንም በከፍተኛ ሁኔታ ጨመረ።

እሌይን የራስን አካላዊ ገጽታ የመጥላት ወይም በራስ ላይ ጉድለት አለብኝ ብሎ የማመን ‘ዲስሞርፊያ’ የተባለ ችግር እንዳለባት ታምናለች።

ዲስሞርፊያ የአዕምሮ ጤና እክል ሲሆን፣ የሚያደርሰው ተጽእኖ አስከፊ ሊሆን ይችላል።

በዚህም መካከል እሌይን በ25 ዓመቷ ሰዎች የእግራቸውን አጥንት ለማስረዘም ቀዶ ህክምና ስለሚያደርግ አንድ የቻይና ክሊኒክን የተመለከተ ጽሑፍ አነበበች።

በጽሑፉ ላይ በመካከከለኛው ክፍለ ዘመን ቀዶ ህክምና ሲደረግ እንደነበረው ዓይነት ጥንታዊ የእግር መደገፊያዎች እንዲሁም ምን ያህል የከፋ ኢንፌክሽን እንደሚያመጣ ዝርዝር ይዘቶች አሉት።

ጽሑፉ ረዘም ያለ በከባድ ስቃይ የሚከናወን የቀዶ ህክምና ክንውንን ፍንትው አድርጎ ቢያሳይም የኢሌንን ቀልብ ሰቅዞ ያዘው።

“በርካቶች ለምን ብለው ጥያቄ ሊያነሱ ይችላሉ። ነገር ግን አካልህን ስትጠላ በጣም የከፋ ስሜት ለምን እንደሚሰማህ ምክንያታዊ ማብራሪያ የለውም” ትላለች።

ከአስራ ስድስት ዓመታት በኋላ እሌይን ለንደን ውስጥ ይህንን የእግር ማስረዘም ቀዶ ህክምና የሚያከናውን የግል ክሊኒክ አገኘች።

ይህንን የቀዶ ህክምና የሚያከናውኑት የአጥንት ሐኪሙ እና የራሳቸውን የእግር ማራዘሚያ መሳሪያ በመፍጠር ስመ ጥር የሆኑት ጂን ማርክ ጉይቸት ናቸው። መሳሪያቸውም የጉይቸት ሚስማር ይሰኛል።

ለንደን ቀዶ ህክምናውን አድርጋ በቤቷ ማገገም መቻሏ ለእሌይን እፎይታ ፈጠረላት። ዶክተር ጉይቸት በቀዶ ህክምናው ሊያጋጥሙ ስለሚችሉ አሉታዊ ጎኖች “የነርቭ ጉዳቶች፣ የደም መርጋት፣ አጥንቶች እንደገና የማይጋጠሙበት” ሁኔታንም ግልጽ አድርገው እንደነገሯት ታስረዳለች።

“ነገር ግን የራሴን ጥናቶች አካሄድኩኝ እንዲሁም በጣም ውድ የሚባል ዶክተር ጋር በመሄዴም ጥሩ የሚባል ህክምና እንደማገኝ ጠብቄ ነበር” ትላለች።

እሌይን ቁመቷ 1.57 ሜትር ሲሆን፣ በዚህም ቀዶ ህክምና 8 ሴንቲ ሜትር በመጨመር 1.65 የመድረስ ህልም ነበራት።

ከስምንት ዓመታት በፊት ሐምሌ አጋማሸ ላይ 50 ሺህ ፓውንድ (7 ሚሊዮን ብር ገደማ) በማውጣት ቁመቷን የማስረዘም ቀዶ ህክምና አደረገች።

እግር የማስረዘም ቀዶ ህክምናዎች በአንጻራዊ ሁኔታ ያልተለመዱ ቢሆኑም፣ ነገር ግን በዓለም ዙሪያ ባሉ የግል ክሊኒኮች ይከናወናሉ። ወጪውም ከ15 ሺህ እስከ 150 ሺህ ፓውንድ ሊደርስ ይችላል።

“ቀዶ ህክምናውን ካከናወንኩ በኋላ ስነቃ በጣም ተደሰትኩኝ ምክንያቱም ምንም የህመም ስሜት አልነበረኝም። ከዘጠና ደቂቃ በኋላ ግን ጀመረ። ስሜቱ እግሬን በእሳት የመጠበስ ያህል ነበር። ውስጤ ይነድ ጀመር። ሌሊቱን እንደጮህኩ ነጋ” ትላለች።

ቀዶ ህክምናው የእግር አጥንቶች ለሁለት ተሰብረው በመካከላቸው የብረት ዘንግ የሚገባበት ሂደት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ህመሙ የሚጠበቅ ነው።

በሁለቱ አጥንቶች መካከል የሚገቡት የብረት ዘንጎች ቀስ በቀስ እንዲራዘሙ ይደረጋል። በዚህም በሁለቱ አጥንቶች መካከል ያለውን ርቀት በማፈራቀቅ ቁመት እንዲጨምር ያደርጋሉ። ለሁለት እንዲሰበሩ የተደረጉት አጥንቶች ቀስ በቀስ ድነውም በመካከላቸው ያለው ክፍተት ተሞልቶ ወጥ ይሆናል።

የቀዶ ህክምናው ሂደት ከባድ እና ውስብስብ እንዲሁም ረጅም ጊዜን የሚፈጅ ነው።

“የማራዘሙ ሂደት ሁለት ወይም ሦስት ወር ገደማ የሚወስድ ሲሆን፣ በተወሰነ መልኩ ለማገገም ከዚህ እጥፍ የሚሆን ጊዜ ይፈጃል። ለአብዛኛዎቹ ቢያንስ አንድ ዓመት ከሕይወታቸው መቀነስ አለባቸው” በማለት የብሪታንያ የአጥንት ቀዶ ህክምና ማኅበር የቀድሞ የምክር ቤት አባል ፕሮፌሰር ሐሚሽ ሲምፕሰን ያስጠነቅቃሉ።

የእሌይን ቀዶ ህክምና ከተጠናቀቀ በኋላ እግሯ የመራዘሙ ሂደት ተጀመረ። በየዕለቱም ምቾት የማይሰጡ ለምሳሌ እግሮቿን በማሽከርከር የገቡት የብረት ዘንጎች የሚራዘሙበትን ሂደት መሥራት አለባት።

በዚህም መንገድ ነው የገቡት የብረት ዘንጎች ተራዝመው እግሮቿን የሚያሳድጉት። ነገር ግን ከሁለት ሳምንታት በኋላ ያልጠበቀችው ቀውስ ገጠማት።

“በግራ እግሬ ላይ ከፍተኛ ህመም ይሰማኝ ነበር። ከዚያም በአንዲት ምሽት አልጋዬ ላይ እየተገላበጥኩ የሆነ ኮሽ ኮሽ የሚል ድምጽ ከእግሬ በኩል ከሰማሁ በኋላ የከፋ ህመም ተከተለ” ትላለች።

እሌይን ክሊኒኩ ሄዳ የስካን ምርመራ ተደረገላት። በግራ እግሯ ላይ ያለው አያያዥ ሚስማር ጭኑዋ ላይ ያለው አጥንት ውስጥ ተሰብሯል።

ፊመር የተሰኘው ይህ የጭን አጥንት በሰውነታችን ውስጥ ከሚገኘው ጠንካራው አጥንት ነው።

ሁኔታው በጣም ቢያስደነግጣትም ዶክተሩ ጉይቸት እንዳረጋጓት ትናገራለች። “አሁን ማድረግ ያለብሽ መጨነቁን ማቆም ነው። እስኪድን ድረስ እንጠብቅ እና አንዴ ከዳነ በኋላ ሂደቱን እንደገና እንጀምራለን አለኝ” ስትል ለቢቢሲ አስረድታለች።

የግራ እግሯን ለማከም ሌላ የቀዶ ህክምና ቀጠሮ ከያዙ በኋላ የቀኝ እግሯን የማራዘም ሂደት ቀጠለ። ተጨማሪ ቀዶ ህክምናው በሺዎች የሚቆጠሩ ፓውንድ እንደሚያስወጣት ቢነገራትም ሁሉ ነገር ተጠናቆ ቁመቷ የሚረዝመበት ላይ ከደረሰች ለመክፈል ደስተኛ ነበረች።

ከወራት በኋላ የቀኝ እግሯ በታሰበው መልኩ 7 ሴንቲ ሜትር ረዘመ። ነገር ግን ሁሉ ነገር አልጋ በአልጋ አልሆነም። በቀኝ እና በግራ እግሯ መካከል ያለው የርዝማኔ ልዩነት ችግር ይፈጥርባት ጀመር።

ይባስ ብሎ የጀርባ አከርካሪ አጥንቷ እንዲጣመም እና የማያቋርጥ ህመም ፈጠረባት።

ከስድስት ሳምንታት በኋላ በተደረገው ስካን የቀኝ እግሯ ላይ መጋጠም የነበረባቸው ሁለቱ አጥንቶች ላይ አስደንጋጭ በሆነ መልኩ ችግር እንዳለ አሳየ።

ኢሌይን ዶክተር ጉይቸት እርዳታ እንዲያደርግላት የጠየቀች ሲሆን፣ እሳቸውም ሚላን ውስጥ በሚሠሩበት ክሊኒክ ሌላ ቀዶ ህክምና ለማድረግ ቀጠሮ ያዙላት።

በአውሮፓውያኑ 2017 ሚያዝያ ወር ላይ የግራ እግሯን የማራዘም ሂደት እንደገና ተጀመረ። በተመሳሳይም በግራ እግሯ ላይ ያለውን አጥንቶች ተጋጥመው በወጥነት እንዲያድጉ ለማድረግም የአጥንት መቅኒ (ቦን ማሮው) በመርፌ ተወጋች።

ቀዶ ህክምናውን ካደረገች በኋላ ኢሌይን ስትነቃ የሰማችው የበለጠ መርዶ ነበር።

“ዶክተር ጉይቸት ሚስማሩን በማውጣት ላይ እያለ እንደተሰበረ ነገረኝ። እናም ከሌላ ታካሚ ሌላ ሚስማር ወስደው ማስገባት እንደተቻለ እና የበለጠ ገንዘብ ያስወጣሻል ተባልኩ” ስትል ታስረዳለች።

ከሦስት ቀናት በኋላ መንቀሳቀስ ቢሳናትም ወደ ቤቷ መሄድ ስለፈለገች ወደ ለንደን ተመለሰች።

ለንደን ከተመለሰች በኋላ ከዶክተሯ ጋር ያላት ግንኙነት እየተፈራቀቀ እንዲሁም በኋላ ላይ እንደተቋረጠ እንደተሰማት ታስረዳለች።

የት ሄዳ እርዳታ መጠየቅ እንደምትችል ግራ የገባት ኢሌይን ከጥቂት ወራት በኋላ በብሪታንያ የጤና አገልግሎት ውስጥ ልዩ የአጥንት ሐኪም አማከረች።

የህክምና ባለሙያው መጀመሪያ የነገራት ነገር ቢኖር “የመዳን ጉዞው አጭር አይሆንም” የሚል ነበር።

“ሙሉ በሙሉ ለመዳን ቢያንስ ለአምስት ዓመታት ህክምና ራሴን ማዘጋጀት ነበረብኝ” ስትል ታስረዳለች።

ከስምንት ዓመታት በፊት የመጀመሪያ ቀዶ ህክምናዋን ያደረገችው እሌይን በአሁኑም ወቅት ከደረሰባት አዕምሯዊ እና አካላዊ ጠባሳ እያገገመች እንደሆነ ታስረዳለች።

አሁንም ቢሆን እንቅስቃሴዋ ላይ ችግሮች ያሉባት ሲሆን፣ የደረሰባት አሰቃቂ መከራም የአእምሮ ጤናዋ ላይ እክል መፍጠሩንም ገልጻለች።

“ለሦስት ዓመታት ያህል እአአ ከ2017 - 2020 ድረስ ከዓለም ተደብቄ ነበርኩ። የወንድ ጓደኛ አልነበረኝም፣ ብቻዬን ነበርኩ፣ ሥራ አጥ፣ ገንዘብ የሌለው እንዲሁም አካል ጉዳተኛ ነበርኩ” ትላለች።

እሌይን በዶክተሩ ላይ ያቀረበችው ክስ ከአራት ዓመታት የፍርድ ሂደት ትግል በኋላ ዘንድሮ ሐምሌ ወር ተቋጭቷል። ዶክተር ጉይቸት የተወሰነውን ገንዘብ ለመክፈል የተስማሙ ሲሆን፣ ለደረሰው ነገር ግን ጥፋተኛ መሆናቸውን አላመኑም።

ዶክተር ጉይቸትን ወክለው የቀረቡት ጠበቃቸው ደንበኛቸው የሙያ ቸልተኝነት እንዳላሳዩ ገልጸዋል “የአጥንት ስብራት እና የመዳኑ ሂደቱ የዘገየው ከህክምናው በፊት ህመምተኛዋ ማስጠንቀቂያ ከተሰጣት የቀዶ ህክምናው አሉታዊ ውስብስብ ችግሮች ምክንያት ነው።

“ከዚህም በተጨማሪ በቀኝ እግሯ በኩል ያለው የአጥንት እድገት ውስንነት የመጣው እሌይን ግልጽ ያላደረገችውን የፀረ-ድብርት መድኃኒት መጠቀሟ፤ እንዲሁም ሆን ብላ በቀኝ እግሯ ላይ ያለውን ሚስማር ስምምነት ላይ ከተደረሰበት በላይ በማራዘሟ ነው” ብለዋል።

ጠበቃው በተጨማሪም እሌይን የዶክተሩን ምክር ባለመስማት የማገገሚያ እና የፊዚዮ ቴራፒ ክትትሏን ችላ ብላለች ሲሉ ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል።

እሌይን ጠበቃው የሚሏቸውን ጉዳዮች አትቀበልም። ትወስዳቸው የነበሩ የፀረ-ድብርት መድኃኒቶች ችግሯን እንዳላወሳሰበው እና ዶክተሩ ለዚህ ቀዶ ህክምና ስህተት ተጠያቂ ናቸው ትላለች።

“በሕይወቴ ምርጥ የሚባሉ ዓመታትን አጥቻለሁ። አንዳንዶች ይጸጽትሻል ወይ? ብለው ይጠይቁኛል። በዚህ ሁሉ መከራ ውስጥ እንደምታልፊ ብታውቂ ኖሮ ይህንን ቀዶ ህክምና ታደርጊ ነበር ወይ ብሎ አንድ ሰው ጠየቀኝ። መልሴ ፍጹም በጭራሽ ነው” ስትል ገልጻለች።