የዩክሬን ጦርነት፡ የሞስኮው ግዙፍ ሕንፃ ድጋሚ በድሮን ተመታ

በሩሲያ መዲና ሞስኮ የሚገኝ ግዙፍ ሕንፃ ድጋሚ በድሮን መመታቱን የከተማዋ ከንቲባ ሰርጌይ ሶብያኒን ገለጹ።

አክለው ሌሎች በርካታ ድሮኖች ጥቃት ከማድረሳቸው በፊት ተመትተው ወድቀዋል ብለዋል።

“ነገር ግን አንድ ድሮን ወደ ሞስክቫ ሲቲ ኮምፕሌክስ ሄዳ” እሑድ ዕለት የተመታውን ሕንፃ ድጋሚ ማጥቃቷን ተናግረዋል።

ለመንገድ ደረቱን የሰጠው የሕንፃው 21ኛ ፎቅ ጉዳት ደርሶበታል ያሉት ከንቲባው በሰው ላይ ምንም ዓይነት ጉዳት እንዳልደረሰ ጠቁመዋል።

የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር ለጥቃቱ ዩክሬንን የኮነነ ሲሆን ኪየቭ እንደተለመደው አስተያየት ከመስጠት ተቆጥባለች።

ከንቲባው በሰጡት አጭር መግለጫ “የሕንፃው መስታወት ክፍል 150 ስኩዌር ሜትር ከጥቅም ውጭ ሆኗል” ብለዋል።

ሶብያኒን የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች በሥፍራው ሥራቸውን እየከወኑ እንደነበርም ገልጸዋል።

በሌላ በኩል የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቱር ሁለት የዩክሬን ድሮኖች በሞስኮው ክልል በፀረ-በራሪ መሣሪያ ተመትተው መወድቃቸውን አሳውቋል።

ጨምሮ እንዳስታወቀው በሞስክቫ ሲቲ ኮምፕሌክስ ሰው በማይኖርበት አካባቢ ደግሞ አንድ ድሮን “በኤሌክትሮኒክ ጦርነት ጫና ከደረሰበት በኋላ” ወድቋል ይላል።

የሞስኮው ቭኑኩቮ አየር ማረፊያ ለአጭር ጊዜ ያክል ተዘግቶ እንደነበር የሩሲያ ዜና ወኪሎች ዘግበዋል።

በተለይ ከቅርብ ወራት ወዲህ በተደጋጋሚ ዩክሬን ክሬምሊንን ጨምሮ ሩሲያ ድንበር ውስጥ ጥቃት እያደረሰች ነው ስትል ሞስኮ ትወቅሳለች።

የፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን መኖሪያ የሆነው ክሬምሊን ባለፈው ግንቦት በዩክሬን ድሮን ጥቃት ደርሶበታል ስትል ሩሲያ መውቀሷ ይታወሳል።

ምንም እንኳ ዩክሬን ለሚደርሱት የድሮን ጥቃቶች ኃላፊነት ባትወስድም የዩክሬኑ ፕሬዝደንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ በሩሲያ ምድር የሚደርሱ ጥቃቶች “ሊወገዱ የማይችሉ፣ ተፈጥሯዊ እና ፍፁም ፍትሐዊ ናቸው” ብለዋል።

በሌሎች የዩክሬን ጦርነት ዜናዎች ሩሲያ ምሽቱን ባደረሰችው የድሮን ጥቃት በዩክሬን ሰሜን ምስራቃዊ ከተማ ኻርኪቭ የተማሪዎች ማደሪያዎች መጎዳታቸውን የከተማዋ ከንቲባ ገልጠዋል።

ሩሲያ፤ በማዕከላዊ ዩክሬን ክሪቭይ ሪህ ከተማ ባደረሰችው የሚሳዔል ጥቃት አንድኢት የ10 ዓመት ልጅን ጨምሮ ስድስት ሰዎች መገደላቸውን፤ 75 ደግሞ መቁሰላቸውን የከተማዋ ባለሥልጣናት ሰኞ ዕለት ተናግረዋል።

ሞስኮው የሾመቻቸው የዶኔትስክ ባለሥልጣናት ሰኞ ዕለት እንዳሳወቁት በምስቃዊቷ የዩክሬን ከተማ ኪየቭ ባደረሰችው ድብደባ ሶስት ሰዎች ተገድለዋል።

ሩሲያ ዩክሬንን የወረረችው በፈረንጆቹ የካቲት 2022 ነበር።