ዜሌንስኪ ከሞስኮው ድሮን ጥቃት በኋላ ጦርነቱ ወደ ሩሲያ እያቀና ነው አሉ

የዩክሬኑ ፕሬዝደንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ በሞስኮው ከደረሰው የድሮን ጥቃት በኋላ ጦርነቱ ወደ ሩሲያ እያቀና ነው ሲሉ አስጠነቀቁ።

ዜሌንስኪ እንዳሉት የሩሲያ ግዛቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች “ሊወገዱ የማይችሉ፣ ተፈጥሯዊ እና በጣም ፍትሐዊ ናቸው” ብለዋል።

የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር እንዳለው እሑድ ዕለት ዩክሬን ወደ ሞስኮው የላከቻቸው ድሮኖች ሲከሽፉ ሁለቱ ደግሞ ሕንፃ ላይ ጉዳት አድርሰዋል።

በከተማዋ ደቡብ ምዕራብ አቅጣጫ የሚገኘው ቭኖኮቮ አየር ማረፊያ ለተወሰነ ጊዜ ተዘግቶ ነበር።

እሑድ ጠዋት ለደረሰው የድሮን ጥቃት ሞስኮው ዩክሬንን ተጠያቂ አድርጋለች።

ከምዕራባዊቷ የዩክሬን ከተማ ኢቫኖ-ፍራንክቭስክ ሆነው እሑድ ዕለት በቪድዮ ንግግር ያሰሙት ፕሬዝደንት ዜሌንስኪ ዩክሬን እየጠነከረች ነው ብለዋል።

“የሩሲያ መንግሥት «ልዩ ወታደራዊ ኦፕሬሽን» ሲል የጠራው ጦርነት በጥቂት ሳምንታት ውስጥ ይጠናቀቃል ብሎ ቢያስብም እነሆ ዛሬ 522ኛ ቀኑን ይዟል።”

አክለው “ቀስ በቀስ ጦርነቱ ወደ ሩሲያ እያቀና ነው። ወደሃገሪቱ ታሪካዊ ማዕከላትና ወታደራዊ ካምፖች እየሄደ ነው። ይህ ሊወገድ የማይችል ተፈጥሯዊ እና በጣም ፍትሐዊ ነው” ብለዋል።

ከዚህ ቀደም ዩክሬን በሩሲያ ለሚደርሱ ጥቃቶች ኃላፊነት ከመውሰድ ትቆጠብ ነበር።

የዩክሬኑ ፕሬዝደንት በልበ ሙሉነት ያሰሙት ንግግር በሩሲያ ላይ ጫና ሊያሳድር እንደሚችል እሙን ነው።

መሰል የድሮን ጥቃቶች ደግሞ ዜሌንስኪ ለሩሲያ ሕዝብ ንግግር እንዲያደርጉ የሚያግዙ ናቸው። አብዛኛዎቹ ሩሲያዊያን የሞስኮው ወረራ ፍትሐዊና ትክክለኛ ነው ብለው ያምናሉ።

የቀድሞው የሩሲያ ፕሬዝደንት ዲምትሪ ሜድቬዴቭ እሑድ ዕለት እንዳሉት ዩክሬን መልሶ ማጥቃቱን የምትቀጥል ከሆነ፤ ሞስኮው የኒውክሌር ጦር መሣሪያ ልትጠቀም ይገባል።

የሩሲያ ደኅንነት ምክር ቤት ምክትል ሊቀ መንበር የሆኑት ሜድቬዴቭ በማሕበራዊ ሚድያ ገፃቸው እንደገለጡት፤ ዩክሬን “የኛን መሬት” ከወሰደች “ሌላ አማራጭ” የለንም ብለዋል።

ባለሥልጣናት በድሮን ጥቃቱ የሞተ ሰው የለም ሲሉ የሞስኮው ከንቲባ የሆኑት ሰርጌይ ሶብያኒን ደግሞ በድሮን የተመቱት ሁሉቱ ሕንፃዎች በጥቂት ተጎድተዋል ብለዋል።

ከሥፍራው የተገኙት ፎቶዎች እንደሚያሳዩት በጥቃቱ የተመቱት ሕንፃዎች በርካታ መስኮቶች ረግፈው ስብርባሪው መንገድ ላይ ተበትኖ ይታያል።

አንድ የዓይን እማኝ እሣትና ጭስ እንዳየች ለሮይተር የዜና ወኪል ተናግራለች።

በደቡብ ምዕራብ የሚገኘው የቭኑኮቮ አየር ማረፊያ ለተወሰነ ጊዜ አገልግሎት መስጠት አቁሞ የሚያርፉ አውሮፕላኖች ወደ ሌላ አየር ማረፊያ ተልከዋል።

ሩሲያ በኪይቭ ጦርነት ካወጀች ጀምሮ ከዩክሬን ድንበር 500 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው ሞስኮው የጥቃት ዒላማ የሆነችው በጣም ጥቂት ጊዜ ነው።

ነገር ግን ሩሲያ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ዩክሬን በተለይ በዋና ከተማዋ የድሮን ጥቃት ለማድረስ እየሞከረች ነው ስትል ትወቅሳለች።