ቫግነር አዲስ ቅጥር አቁሜ ትኩረቴን አፍሪካ እና ቤላሩስ ላይ አድርጊያለሁ አለ

የሩሲያው ቅጥረኛ ተዋጊ ቡድን ቫግነር መሪ የቭጌኒ ፕሪጎዢን ቡድኑ አሁን ላይ አዲስ ቅጥር አቁሞ ትኩረቱን አፍሪካ እና ቤላሩስ ላይ ማድረጉን አስታወቀ።

በቫግነር የቴሌግራም ገጽ ላይ በተለቀቀ የድምጽ ቅጂ የቡድኑ መሪ የቭጌኒ ፕሪጎዢን “ለሩሲያ ታላቅነት” ስላለው ቀጣይ ስትራቴጂ ውሳኔ እያሳለፈ ነው ብሏል።

ቡድኑ በቭላድሚር ፑቲን አስተዳደር ላይ የከሸፈ አመጽ ቀስቅሶ ከሞስኮ ጋር ወዳጅነቱ ከመዳከሙ በፊት፣ ቫግነር ሩሲያ በዩክሬን ላይ በከፈተችው ወረራ ላይ ከሞስኮ ጎን ተሰልፎ ከፍተኛ ተጋድሎ አድርጓል።

የቭጌኒ በዚህ የድምጽ ቅጂው ላይ “ከከፍተኛ የሥራ ኃላፊነቶች” በኋላ በርካታ የቫግነር ተዋጊዎች እረፍት ላይ ይገኛሉ ሲል ይደመጣል።

ቡድኑ “በአፍሪካ እና በቤላሩስ የልምምድ ማዕከላት ውስጥ ንቁ ሆኖ ይቀጥላል” ብሏል።

የቭጌኒ በጉዳዩ ላይ ዝርዝር መረጃ ባይሰጥም ቫግነር በበርካታ የአፍሪካ አገራት ተሰማርቶ የሚገኝ ሲሆን፣ ከከሸፈው አመጽ በኋላ በሺዎች የሚቆጠሩ የቡድኑ አባላት ቤላሩስ ውስጥ ባለ የጦር ካምፕ ሰፍረዋል።

በቅርቡ በመቶዎች የሚቆጠሩ የቫግነር ቅጠረኛ ቡደን ተዋጊዎች ወደ መካከለኛ አፍሪካ ሪፐብሊክ መግባታቸው ተሰምቷል።

የቡድኑ አባላት በመካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ በሚካሄደው ሕዝበ ውሳኔ የጥበቃ አገልግሎት ይሰጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ቡድኑ ከመካከላኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ በተጨማሪ በአፍሪካ ከ10 ባላነሱ አገራት ውስጥ ተሰማርቶ ይገኛል አልያም ተሰማርቶ ነበር።

ሊቢያ፣ ሞዛምቢክ፣ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እና ሱዳን ቫግነር ከተሰማራባቸው አገራት መካከል ተጠቃሽ ነው።

በቅርቡ መፈንቅለ መንግሥት በተደረገባቸው ቡርኪና ፋሶ እና ማሊ ቡድኑ እጁን ሳያስገባ እንደልቀረ የሚወጡ ሪፖርቶች ይጠቁማሉ።

ባለፈው ሳምንትም በኒጀር መፈንቅለ መንግሥት መፈጸሙን ቫግነር እንደ መልካም አጋጣሚ ተመልክቶታል።

ምዕራባውያን አገራት በሕዝብ የተመረጡትን ፕሬዝዳንት ከሥልጣን ያነሳው ወታደራዊ ቡድን ወዳጅነቱን ከሞስኮ ጋር ሊያደርግ ይችላል የሚል ስጋት አድሮባቸዋል።

የቫግነር መሪ የቭጌኒ ፕሪጎዢን “በኒጀር የሆነው ነገር የኒጀር ሕዝብ በቅኝ ገዢዎቻቸው ላይ ያደረጉት ትግል ነው። ...ዛሬ ነጻነታቸውን እያገኙ ነው” ስለማለታቸው ከቡድኑ ጋር ቅርበት ያለው የቴሌግራም ቻናል ገልጿል።

“በሰው ኃይል ረገድ ምንም አይነት ችግር እየገጠመን ስላልሆነ አዲስ ቅጥር ለማድረግ ዕቅድ የለንም።...ይሁን እንጂ እናት አገራችን ብሔራዊ ፍላጎት የሚያስጠብቅ አዲስ ኃይል ስትፈልግ ቅጥር ስለምንጀምር ከእኛ ጋር ግንኙነት ፈጥራችሁ ብትቆዩ ደስ ይለናል” ብሏል የቭጌኒ።

በቭላድሚር ፑቲን አስተዳደር ላይ አመጽ ቀስቅሶ ሩሲያን ለ24 ሰዓታት ትርምስ ውስጥ ከቷት የነበረው ቫግነር፣ አመጹ ከከሰመ በኋላ መሪው ወደ ቤላሩስ እንዲያመራ ተደርጎ ቡድኑ ደግሞ የከባድ መሳሪያ ትጥቅ እንዲፈታ ሆኗል።

ቡድኑ ትጥቅ እንዲፈታ ተደርጎ የቡድኑ ተዋጊዎች ክስ ሳይመሠረትባቸው የሩሲያን ጦር መቀላቀል፣ ወደ ቤላሩስ ማቅናት አልያም ትጥቅ ፈትተው ወደ ቀደመ ሕይወታቸው መመለስ እንደሚችሉ በፑቲን አስተዳደር አማራጭ ተሰጥቷቸው ነበር።