የሩሲያ ፍርድ ቤት የአይኤስ ታጣቂ ሚስቶችን ታሪክ የሚያሳየውን ትያትር አዘጋጆች በእሥር ቀጣ

ሩሲያዊያቷ ደራሲ እና የትያትር አዘጋጅ “ሽብርተኝነትን ለማስተባበል በመሞከር” ወንጀል ጥፋተኛ ሆነው ተገኝተዋል ሲል የሞስኮው ወታደራዊ ችሎት ፈርዷል።

አዘጋጇ የቭጌኒያ ቤርኮቪች እና ደራሲ ስቬትላና ፔትሪቹክ፤ ዘ ብሬቭ ፋልከን ፊኒስት የተሰኘውን ትያትር በመሥራታቸው የስድስት ዓመት እሥራት ተፈርዶባቸዋል።

በከፊል እውነተኛ ታሪክ ላይ ተመሥርቶ የተሠራው ይህ ትያትር በሶሪያ የእርስ በርስ ጦርነት ወቅት ወደሥፍራው አምርተው የኢስላሚክ ስቴት ታጣቂ ቡድን አባላትን ያገቡ ሩሲያዊያን ሴቶችን ሕይወት የሚዳስስ ነው።

የሁለቱ ሴቶች ጠበቃዎች የችሎቱን ውሳኔ በመቃወም ይግባኝ እንደሚጠይቁ አሳውቀዋል።

በዝግ ችሎት የተካሄደውን የፍርድ ሂደት የሀገሪቱ የጥበብ ሰዎች ሐሳባቸውን በነፃነት እንዳይገልፁ የሚያደርግ ነው ሲሉ ተችዎች ነቅፈውታል።

ሴቶቹ የተፈረደባቸውን የስድስት ዓመት እሥር ጨርሰው ሲወጡ ለተጨማሪ ሶስት ዓመታት “ድረ-ገፅ እንዳያስተዳድሩ” የሚል ቅጣትም ተጥሎባቸዋል።

የሩሲያው ዜና ወኪል አርቢሲ እንደዘገበው በአውሮፓውያኑ ከ2023 ጀምሮ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር የቆዩት ሁለቱ ሴቶች ቅጣታቸውን ለማጠናቀቅ ወደ እሥር ቤት ይላካሉ።

አቃቤ ሕግ እንዳለው ሴቶች ለአይኤስ ተዋጊዎች አዎንታዊ አመለካከት እንዲኖራቸው ሆኗል።

አልፎም አቃቤ ሕግ የካቴሪና ዴኒሶቫ ትያትሩ “ለሽብርተኝነት አመክንዮ ለመስጠት ይሞክራል” ሲሉ ተከራክረዋል ይላል የአርቢሲ ዘገባ።

ችሎቱ ባለፈው ግንቦት መጀመሪያ ሲጀመር የ39 ዓመቷ የቭጌኒያ እና የ44 ዓመቷ ስቭትላና ትያትሩን የሠሩት ሽብርተኝነት ስለሚቃወሙ እንደሆነ ተናግረው ነበር።

የቭጌኒያ ቲያትሩ የተሠራው “ሽብርተኝነት ለማስወገድ” እንደሆነ ተናግራ “ሽብርተኞች አወግዛለሁ፤ እጠየፋለሁ” ብላ ነበር።

“እኔ ይህ ሥራ ከኔ ጋር ያለው ግንኙነት ምን እንደሆነ አላውቅም. . . ስለፅንፈኛ ኢስላምም ሆነ ስለሌላው ያለኝን አመለካከት አጋርቼ አላውቅም” ብላለች ይላል የአርቢሲ ዘገባ።

ደራሲዋና እና አዘጋጇ ችሎቱ ተጀምሮ እስኪያልቅ ድረስ ጥፋተኛ አለመሆናቸውን ሲናገሩ ነው የቆዩት።

ችሎቱ ሁለቱን ሴቶች በእሥር ከቀጣ በኋላ አስተያየት የሰጡት ጠበቃ ክሴኒያ ካርፒንስካያ ፍርዱን “ሕጋዊ ያልሆነ” እና “ፍትሕ የጎደለው” ሲሉ የተቹ ሲሆን ምንም እንኳ “ቅንጣት ተስፋ” ብቻ ቢኖረውም ይግባኝ እንደሚጠይቁ አሳውቀዋል።

“እኔ እንድታውቁ የምፈልገው እኒህ ሴቶች ጥፋተኛ አለመሆናቸውን ነው” ይላሉ ጠበቃዋ።

የየቭጌኒያ ደጋፊዎች ቅጣቱ የተጣለባት ሩሲያ በዩክሬን የምታካሂደውን ጦርነት ተቃውሞ በተደጋጋሚ ግጥም ስለፃፈች ነው ይላሉ።

ሩሲያ በአውሮፓውያኑ 2022 በዩክሬን መጠነ ሰፊ ወረራ ማካሄድ ከጀመረች በኋላ የሀገሪቱ የጥበብ ማሕበረሰብ ከክሬምሊን ከፍተኛ ጫና እየደረሰበት ይገኛል።

በርካታ ትልቅ ስም ያላቸው ሩሲያዊያን አርቲስቶች፣ ፀሐፊዎች እና ጋዜጠኞች ሁለቱን ሴቶች ደግፈው ሐሳባቸውን እየሰጡ ይገኛሉ።

በ2020 ለዕይታ የበቃው ትያትር ጎልደን ማስክ ትያትር አዋርድስ የተሰኘውን ሽልማት ሁለት ጊዜ ማሸነፍ ችሏል።

በቅርብ ወራት ኢስላማዊ ታጣቂዎች በሞስኮው እና ዳጌስታን የበርካቶችን ሕይወት የቀጠፈ ጥቃት ፈፅመዋል። ክሬምሊን በሁለቱም ጥቃቶች የዩክሬን እጅ አለበት ስትል ትወቅሳለች።