ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ለሳምንታት ኃይል በመቋረጡ የአሶሳ ሆስፒታል አገልግሎት የማቆም ስጋት ተደቅኖበታል
ከሁለት ሳምንታት በላይ የኤሌክትሪክ ኃይል በተቋረጠበት የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ዋና ከተማ አሶሳ የሚገኘው የአሶሳ አጠቃላይ ሆስፒታል የሚሰጠው አገልግሎት በኃይል አለመኖር ምክንያት የሚሰጠው አገልግሎት ሊቆም እንደሚችል አስታወቀ።
በአሶሳ ከተማ እና በአካባቢው የኃይል መቋረጥ የተከሰተው አጎራባች በሆነው የኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን በሚገኝ የኃይል ተሸካሚ ምሰሶ ላይ “በታጣቂዎች” በደረሰ ጉዳት እንደሆነ የአሶሳ ዞን አስታውቋል።
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ዋና ከተማ እንዲሁም በዙሪያው ባሉ ወረዳዎች እና የገጠር ቀበሌዎች የኤሌክትሪክ ኃይል የተቋረጠው ከሦስት ሳምንታት በፊት ሰኔ 9/2016 ዓ.ም. እንደሆነ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታውቆ ነበር።
በአሁኑ ሰዓት በዞኑ ውስጥ የሚገኙ ዘጠኝ ወረዳዎች እንዲሁም የአሶሳ እና የባምባሲ ከተማ አስተዳደሮች የኤሌክትሪክ ኃይል እያገኙ አለመሆኑን የአሶሳ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ እድሪስ መሐመድ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በዚህም ምክንያት የጤና ተቋማትን ጨምሮ በተለይ በከተሞቹ ውስጥ የሚገኙ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት መስተጓጎል እንደገጠማቸው አስረድተዋል።
ከእነዚህ ተቋማት መካከል በየቀኑ ከ400 እስከ 500 ታካሚዎችን የሚያስተናግደው የአሶሳ አጠቃላይ ሆስፒታል ይገኝበታል።
በአሶሳ ከተማ የሚገኘው ይህ ሆስፒታል በዞኑ ወረዳዎች ከሚገኙ 22 ጤና ጣቢያዎች እንዲሁም በካማሺ ዞን እና በአጎራባች የኦሮሚያ ክልል አካባቢዎች ከሚገኙ ሆስፒታሎች ታካሚዎችን እንደሚቀበል የሆስፒታሉ ምክትል ሚዲካል ዳይሬክተር ዶ/ር አብዮት ደረሶ ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ከዚህ ባሻገር ከታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት እና በክልሉ ውስጥ ከሚገኙ አምስት የስደተኛ መጠለያ ጣቢያዎች ታካሚዎችን እንደሚያስተናግድም ጠቅሰዋል።
ሆስፒታሉ ከሚሰጠው አገልግሎት አንጻር 24 ሰዓት ሙሉ የማይቋረጥ ኃይል ማግኘት እንደሚኖርበት የሚያስረዱት ዶ/ር አብዮት፤ ባለፉት ሳምንታት የኤሌክትሪክ ኃይል መቋረጡ በተቋሙ ላይ “ከፍተኛ ጫና” ፈጥሯል።
እንደ ምክትል ሜዲካል ዳይሬክተሩ ገለጻ ኃይል ከተቋረጠ ጊዜ አንስቶ ሆስፒታሉ በምትክነት አገልግሎት ለሚሰጠው ጄኔሬተር በየቀኑ ከ180 እስከ 200 ሊትር ነዳጅ ይጠቀማል።
ነገር ግን አገልግሎት ላይ የሚውሉት ሁለት ጄኔሬተሮችም ቢሆኑ በአንድ ጊዜ ሆስፒታሉ ሙሉ በሙሉ ኃይል እንዲያገኝ የማያስችሉ ባለመሆናቸው “የተወሰኑ የሥራ ክፍሎች” ያለ ኃይል እንዲቆዩ እንደሚደረግ ጠቅሰዋል።
“ኦፕሬሽን ክፍል እና ሙሉ ጊቢው ላይ ኃይል ስንፈልግ [ሁለቱን ጄኔሬተሮች] እያቀያየርን ነው የምንጠቀመው። እርሱም ቢሆን እንደምንፈልገው የጨቅላ ሕጻናት ማቆያ ማሽኖችን ማስነሳት የሚችል አይደለም” ሲሉ ሆስፒታሉ ያለበትን ሁኔታ ገልጸዋል።
ያለ ጊዜያቸው የሚወለዱ ሕጻናትን ለማቆየት የሚውለው ማሽን ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል የሚጠይቅ መሆኑን የሚያነሱት ዶ/ር አብዮት፤ ሆስፒታሉ አነስተኛ የሆነውን ጄኔሬተር በሚጠቀምበት ወቅት ማሽኖቹ መነሳት እንደማይችሉ አስረድተዋል።
ምክትል ሜዲካል ዳይሬክተሩ፤ በዚህ ማሽን ውስጥ የሚቆዩ ሕጻናት ያልተቋረጠ ኦክስጅን ማግኘት እንዳለባቸው ገልጸው፤ መቋረጥ ካጋጠመ በሕጻናቱ ላይ “ሞት ሊያስከትል የሚችልበት ዕድል” እንዳለም አመልክተዋል።
“የተወሰኑ የሥራ ክፍሎችን የኃይል አቅርቦት አጥፍተን [ጄኔሬተሩ] ሲነሳልን [የኤሌክትሪክ ኃይሉን] ወደ የጨቅላ ሕጻናት ማቆያ ማሽኑ ላይ እናደርጋለን። ኦፕሬሽን ክፍል እና ሌሎች የሥራ ዘርፎች ላይ ኃይሉ ሲፈለግ ደግሞ ማሽኑን ለማቋረጥ የምንገደድበት ሁኔታ ይኖራል” ሲሉ ሆስፒታሉ ተግባራዊ እያደረገ ያለውን አሠራር አስረድተዋል።
ሆስፒታሉ በዚህ መልኩ ለተለያዩ አገልግሎቶች ኃይል እያፈራረቀ እስካሁን ቢቆይም ለጄኔሬተሩ የሚውለው ነዳጅ ወጪ ከሆስፒታሉ አቅም በላይ እንደሆነ ምክትል ሜዲካል ዳይሬክተሩ ገልጸዋል። ሆስፒታሉ ይህንን ስጋቱን ባለፈው ሳምንት ሰኞ ሰኔ 24/2024 ዓ.ም. ለክልሉ ጤና ቢሮ እና ለአሶሳ ከተማ አስተዳደር በጻፈው ደብዳቤ ላይ ገልጾ ነበር።
ሆስፒታሉ 2016 ዓ.ም. የበጀት ዓመትን “በበጀት እጥረት” ማሳለፉን የሚገልጸው ደብዳቤው፤ በኃይል መቋረጥ ምክንያት ተቋሙ ለሚጠቀመው እና በየቀኑ ለሚያስፈልገው ከ200 ሊትር በላይ ነዳጅ “የበጀት እጥረት እና የነዳጅ በማደያ ባለመኖሩ” ለማግኘት እየተቸገረ መሆኑን ያስረዳል።
ተቋሙ በደብዳቤው፤ “የድንገተኛ፣ የቀዶ ጥገና፣ ሁሉም ዕለታዊ የሆስፒታሉ አገልግሎቶች በመብራት የሚሠሩ በመሆናቸው፤ ሆስፒታሉ አጠቃላይ ሥራ ወደ ማቆም ደረጃ የደረሰ ስለሆነ በተቻለ መጠን መፍትሔ እንዲፈለግ እንጠይቃለን” ሲል ጥያቄ አቅርቧል።
ይህንን ጥያቄ ተከትሎ በከተማዋ ውስጥ ከሚገኙ የመንግሥት ተቋማት ሆስፒታሉ ነዳጅ “በውሰት” እንዲያገኝ እየተደረገ መሆኑን ዶ/ር አብዮት ተናግረዋል።
“ነዳጅ ከተለያዩ መሥሪያ ቤቶች እና ባለሀብቶች በልመና የምናመጣው ማታ በአንቡላንስ እየዞርን ነው። አስተማማኝ የነዳጅ ክምችት በሌለበት መብራት ለረጅም ጊዜ ሲቋረጥ፣ እንደገናም የበጀት እጥረት ሲጨመርበት የአገልግሎት መቋረጥ ሊኖር ይችላል የሚል ከፍተኛ ስጋት አለን” ብለዋል።
ሁኔታው በዚህ ከቀጠለ “የድንገተኛ ህክምና አገልግሎት ጭምር ሊቋረጥ የሚችልበት አዝማሚያ” መኖሩን አክለዋል።
የአሶሳ አጠቃላይ ሆስፒታል አገልግሎትን ስጋት ውስጥ የከተተው የኤሌክትሪክ ኃይል መቋረጥ የተከሰተው “ከአሶሳ መንዲ የተዘረጋ ባለ 132 ኪሎ ቮልት የከፍተኛ ኃይል ማስተላለፊያ መስመር ተሸካሚ የብረት ምሰሶ በመውደቁ” እንደሆነ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ከሦስት ሳምንት በፊት አስታውቆ ነበር።
በኦሮሚያ ክልል በምዕራብ ወለጋ ዞን መነሲቡ ወረዳ የሚገኘው ይህ ምሰሶ የወደቀው “በመፈታታቱ” የተነሳ እንደሆነ ተገልጾ ነበር። በምሰሶው ላይ ስርቆት እንዳልተፈጸመም አክሏል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በፌስቡክ ገጹ ከዚህ መረጃ ጋር የለጠፋቸው ምሥሎች ማያያዣዎቹ (ብሎን) ተፈትተው የወደቀ ምሰሶን ያሳያሉ።
የወደቀውን የኃይል ተሸካሚ ምሰሶ ለመጠገን የቴክኒክ ቡድን ቦታው ላይ መገኘቱን የጠቀሰው የኤሌክትሪክ ኃይል መረጃ፤ ይሁንና ቡድኑ “ምሶሶውን በነበረበት ሁኔታ መልሶ ለማቆም ረዘም ያሉ ሳምንታት እንደሚወስድ ሪፖርት” ማድረጉን ገልጿል።
የአሶሳ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ እድሪስ፤ ይህ የኃይል ተሸካሚ ምሰሶ “የተቆረጡት በኦሮሚያ ክልል በኩል የሚንቀሳቀሰው የሸኔ አባላት” እንደሆኑ መረጃ እንደደረሳቸው ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በአሶሳ እና አካባቢው አገልግሎት መቋረጡን ባስታወቀ ማግስት “በአሶሳ እና አካባቢው የተቋረጠውን ኃይል መልሶ እንደተገናኘ” ገልጿል። “አካባቢው ኃይል እንዲያገኝ የተደረገው በባለሙያዎች የቀረበውን ቴክኒካዊ የአማራጭ መፍትሔ በመተግበር” እንደሆነም አስታውቋል።
ይሁንና የተገናኘው የኤሌክትሪክ ኃይል ከሁለት ቀናት በኋላ መልሶ መቋረጡን የአሶሳ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ እድሪስ ገልጸዋል።
ይህንኑ የሚያረጋግጡት ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው አንድ ምንጭ ጥገና የተደረገለት መሠረተ ልማት ላይ በድጋሚ “ሰው ሰራሽ ጉዳት” እንደደረሰ ገልጸዋል።