የኬንያ ፕሬዚዳንት የምርጫ አስፈጻሚዎችን አገዱ

የኬንያው ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ ነሐሴ የተካሄደውን ምርጫና አሸናፊ ያደረጋቸውን ውጤት ያልተቀበሉ አራት የምርጫ ኮሚሽነሮችን ከስራ አገዱ።

ፕሬዚዳንት ሩቶ ዛሬ አርብ እንዳስታወቁት ፍርድ ቤት አራቱን ባለስልጣናት ህግ በመጣስ፣ በከባድ ስነ ምግባር ጉድለትና በብቃት ማነስ እንደሚመረምራቸውና ከስልጣናቸውም እንደሚባረሩ ገልጸዋል።

ነገር ግን የተቃዋሚ ፓርቲው አመራርና ለአምስት ጊዜ በምርጫ የተወዳደሩት ራይላ ኦዲንጋ ውሳኔውን አውግዘው በመጪው 2027 ምርጫንም መንግሥት ለማጭበርበር ያለመ ነው ብለዋል።

“አራቱ ኮሚሽነሮች እንዲባረሩ የተደረጉት ሩቶና አስተዳደራቸው የምርጫ ኮሚሽኑን እንደ አዲስ ለማዋቀርና በራሳቸው ሹመኞች ለመሙላት ነው። ሩቶ በ2022 እያቀደ ያለው በ2027 ምርጫ ለማጭበርበር ነው” ብለዋል ኦዲንጋ

ፕሬዚዳንት ሩቶ የፍርድ ቤቱን ውሳኔ ያስታወቁት ነሐሴ በተደረገው ምርጫ ኮሚሽነሮቹ ባሳዩት ባህርይ ምክንያት እንዲታገዱ በብሔራዊ ምክር ቤቱ የቀረበውን ሃሳብ ተከትሎ ነው።

ዊሊያም ሩቶ ተፎካካሪያቸውን ራይላ ኦዲንጋን 50.5 በመቶ ድምጽ በማግኘት ማሸነፋቸው ይታወሳል።

ነገር ግን የምርጫ ቦርድ ምክትል ሊቀ መንበሩን ጨምሮ ከሰባት ኮሚሽነሮች ውስጥ አራቱ የምርጫው አኃዝ የተሳሳተ እና ውጤቱም “ግልጽ ያልሆነ” ብለውታል።