የፌስቡክ ባለቤት ዛከርበርግ፤ ኢላን እንቧቀስ ያለው “የምሩን አይደለም” ሲል ወቀሰ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ኢላን መስክ እንቧቀስ ያለው “የምሩን አይደለም” ስለዚህ “ጉዳዩን ብንገታው ሳይሻል አይቀርም” ሲል ማርክ ዛከርበርግ ወቀሰ።
ትሬድስ የተሰኘው ማሕበራዊ ሚድያ ላይ ሐሳቡን የገለጠው የሜታ ባለቤት ከኢላን ጋር ለመቧቀስ “ቀነ ቀጠሮ” ቢይዝም መስክ ምክንያት እየደረደረ አስቸግሯል።
መስክ እሑድ ዕለት ኤክስ በተሰኘው ማሕበራዊ ሚድያው ሰኞ ቢሆን ለመቧቀስ ዝግጁ መሆኑን ጠቁሞ ነበር።
ቢሊየነሮቹ ባለፈው ሰኔ በቦክስ ይዋጣልን ማለታቸው የመገናኛ ብዙኃን መነጋገሪያ ሆኖ ነበር።
ነገር ግን ሁለቱም እርስ በርስ በነገር ከመጎሻሸም ውጭ ቀነ ቀጠሮ ለመያዝ መቸገራቸው ጉዳዩ ቀልድ ነው ወደሚል እሳቤ ወስዷል።
የቃላት ጦርነቱ በጣም የደራው ዛከርበርግ ትሬድስ የተባለ የኤክስ [የቀድሞው ትዊተር] ተቀናቃኝ ማሕበራዊ ሚድያ ይፋ አድርጎ በአንድ ሳምንት 100 ሚሊዮን ተጠቃሚዎች ሲያጋብስ ነው።
ነገር ግን የትሬድስ ተጠቃሚዎች ቁጥር አሽቆልቁሎ ኤክስ በ350 ሚሊዮን ተጠቃሚዎች በልጦ መሪውን ጨብጧል።
መስክ፤ “ትሬድስ የተባለውን ማሕበራዊ ሚድያ ለመሥራት ከትዊተር ኮርጇል” ሲል ፌስቡክን እከሳለሁ ቢልም ሜታ ግን ወቀሳውን አስተባብሏል።
ባለፈው ሳምንት ዛከርበርግ ቡጢው በፈረንጆቹ ነሐሴ 26 ይከናውን ሲል ቀን ቆርጦ ነበር።
ነገር ግን አርብ ዕለት የጣሊያኑ ባሕል ሚኒስትር ከኢላን መስክ ጋር ማውራታቸውን ገልጠው ሃገራቸውን ቡጢውን ለማሰናዳት መዘጋጀቷን አስታውቀዋል።
መስክ ቡጢው “ልክ እንደ ጥንታዊቷ ሮም ይሆናል” ብሎም ነበር።
ከዚያ በኋላ ነው የሜታ አለቃ ዛከርበርግ “ኢላን ቀን ሊቆርጥ አልቻለም፤ አንዴ ቀዶ ጥገና ያስፈልገኛል ይላል፤ አንድ ጊዜ ደግሞ እኔ ቤት ጓሮ የሙከራ ድብድብ እናድርግ ይላል” ሲል ያማረረው።
“ኢላን የምሩን ከሆነ ቀን ቆርጦ፤ ቦታ መርጦ ይንገረኝ። የት እንደምገኝ ያውቃል። ካልሆነ ግን ሁሉን እርግፍ አድርገን እንተወው። እኔ በቁም ነገር መቧቀስ ከሚፈልጉ ሰዎች ጋር ብወዳደር ይሻለኛል።”
ለዚህ ኤክስ ላይ ምላሽ የሰጠው ኢላን መስክ የሜታውን ባለቤት “ፈሪ” ብሎታል።
መስክ ከዛከርበርግ ጋር ያደረጉት ነው ብሎ በለጠፈው የመልዕክት ልውውጥ ላይ ከፈለግክ ወዳለህበት መጥቼ ሰኞ ዕለት መቧቀስ እንችላለን ማለቱ ይታያል።
የ52 ዓመቱ ኢላን መስክ እና የ39 ዓመቱ ማርክ ዛከርበርግ ከዓለማችን በቴክኖሎጂ አማካይነት የበለጠጉ ቢሊዮነሮች መካከል ቁንጮዎቹ ናቸው።
ባለፈው ሰኔ መስክ በቀድሞው ትዊተር ላይ “በፍርግርግ በታጠር መቧቀሻ ውስጥ ይለይልን” ማለቱን ተከትሎ ነው የቡጢው ሐሳብ የደራው።
ቀጥሎ ዛከርበርግ “አድራሻውን ላክልኝ” ሲል ምላሽ ሰጠ።
የሜታው አለቃ ሚክስድ ማርሻል አርትስ በተሰኘው ስፖርት ሥልጠና የወሰደ ሲሆን በቅርቡ ደግሞ በጂዩ-ጂትሱ ውድድር ተሳትፏል።












