አሜሪካ የተሰረቁ 250 ውድ ጥንታዊ ቁሳቁሶችን ለጣሊያን መለሰች

የጣሊያን ጥንታዊ ቁሳቁሶች

የፎቶው ባለመብት, ITALIAN MINISTRY OF CULTURE

ዩናይትድ ስቴትስ ተሰርቀው የመጡ መሆናቸው በፖሊስ የተረጋገጡ ከ250 በላይ ጥንታዊ ቁሳቁሶችን ለጣሊያን መለሰች።

የጣሊያን ፖሊስ የጥበብ ክፍል በ1990ዎቹ ተሰርቀው ለአሜሪካ ሙዚየሞችና ለግል ሰብሳቢዎች የተሸጡ ቁሳቁሶችን አግኝተዋል።

ከእነኚህ ውድ ቁሳቁሶች መካከል ከሸክላ የተሠሩ ዕቃዎች፣ ስዕሎችና ቅርፃቅርፆች ይገኙበታል።

አሜሪካ ለጣሊያን ከመለሰቻቸው ቁሶች መካከል የተወሰኑቱ 3 ሺህ ዕድሜ ያላቸው ናቸው።

250 በላይ የሆኑት ጥንታዊ ቁሳቁሶች ዋጋቸው ሲሰላ ከ10 ሚሊዮን ዩሮ በላይ ያወጣሉ።

እጅግ ጥንታዊ የሆነው ቁስ ከቪላኖቫ ሥልጣኔ [ከክርስቶስ ልደት በፊት ከ1000-750] የተገኘ ሲሆን ከኢትሩስካን ሥልጣኔ፣ ከማግና ግራኤሺያ እና ከኢምፔሪያል ሮም ዘመነ መንግሥት የተገኙ ቁሳቁሶችም ተካተውበታል።

አብዛኛዎቹ ሰው ሠራሽ ቁሶች በ1990ዎቹ ተሰርቀው አሜሪካ ለሚገኙ ሙዚየሞች የተቸበቸቡ ናቸው።

ከእነዚህ መካከል በቴክሳስ ግዛት ሂዩስተን በሚገኘው ሜኒል ኮሌክሽን ለተባለ ሙዚየም የተሸጠው ብዙዎችን አስገርሟል።

የጣሊያን ባሕል ሚኒስቴር አንዳንድ ጥንታዊ ቁሳቁሶች በሜኒል ኮሌክሽን ተሰቅለው ታይተዋል ቢልም የሙዚየሙ ቃል-አቀባይ ግን ይህ ሐሰት ነው፤ እኛ የተሰረቁ የጣሊያን ቁሶችን ለዕይታ አቅርበን አናውቅም ብለዋል።

ቃል-አቀባዩ እንደሚሉት ሙዚየሙ ጥንታዊ የጣሊያን ቁሶችን እንዲገዛ ጥያቄ ቢቀርብለትም፤ ሙዚየሙ ጉዳዩን ወደ ጣሊያን የባሕል ሚኒስቴር መርቷል።

ሚኒስቴሩ እንደሚለው እኒህን የጣሊያን ጥንታዊ ቁሶች ይዞ የነበረ ግለሰብ ፖሊስ የተሰረቁ መሆናቸውን ባወቀ ጊዜ “በፍጥነት” መልሷል።

አብዛኛዎቹ ቁሶች በሕገ-ወጥ መንገድ ከጥንታዊ ቁሳቁስ መቆፈሪያ ሥፍራዎች ተፈልፍለው የወጡ ናቸው።

የጣሊያን ባሕል ሚኒስቴር አክሎ እንደገለጠው ከተመለሱት ቁሶች 145 ያክል የሚሆኑት በሕገ-ወጥ መንገድ የተገኙ ጥንታዊ ዕቃዎች አሻሻጭ ከሆነው እንግሊዛዊ ሮቢን ሳይምስ የተገኙ መሆናቸው ተረጋግጧል።

ጣሊያን ለዘመናት በሕገ-ወጥ መንገድ አሊያም በስርቆት ለሙዚየሞችና ለግለሰቦች የተሸጡ ጥንታዊ ንብረቶችን ስታፈላልግ ቆይታለች።

በፈረንጆቹ መስከረም 2022 የአሜሪካዋ ኒው ዮርክ ከተማ 19 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጡ የጥበብ ሥራዎችን ለጣሊያን መልሳለች።

ከክርስቶስ ልደት በፊት የነበረ 3 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ የአቴና ጣዖት የተሰኘችው ሐውልት አናት ይገኝበታል።