ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የዓለም ፍጻሜ ተቃርቧል በሚል በጾም ላይ የነበሩ 4 ኬንያውያን ሲሞቱ በርካቶች ሆስፒታል ገቡ
ኬንያ ውስጥ የዓለም ፍጻሜ ቀርቧል በማለት እየጾሙ ሲጠባበቁ ከነበሩ በርካታ ሰዎች መካከል አራቱ ሲሞቱ ብዙዎቹ ሆስፒታል ገቡ።
በኬንያ ምሥራቃዊ ክፍል ኪሊፊ በሚባለው የባሕር ዳርቻ ግዛት ውስጥ ነዋሪ የሆኑት እነዚህ ሰዎች እራሳቸውን ነጥለው የዓለም ፍጻሜን ሲጠባበቁ ነበር በፖሊስ የተገኙት።
ሰዎቹ ፓስተር ማኬንዚ ንቴንጌ የተባለ የሃይማኖት ሰባኪ የዓለም ፍጻሜ እውን ሊሆን በመቃረቡ እየጾሙ “የኢየሱስ ክርስቶስ መምጣትን እንዲጠብቁ” በተነገራቸው መሠረት ነው የተባሉትን ያደረጉት።
ፖሊስ እንዳለው ሐሙስ ዕለት በቡድን የተሰባሰቡትን ሰዎች የሰባኪውን ትዕዛዝ ከተቀበሉ በኋላ ለበርካታ ቀናት በቆዩበት ጫካ ውስጥ ነው የተገኙት።
በጾም ተዳክመው ጫካ ውስጥ ሕይወታቸው ካለፈው ሰዎች በተጨማሪ 11 ሰዎች በፖሊስ ተገኝተዋል፣ ከመካከላቸውም ስድስቱ በጣሙን ተጎድተው በአሳሳቢ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ባለሥልጣናት ተናግረዋል።
ሐሙስ ዕለት ከተገኙት ሰዎች በተጨማሪ ሌሎችም በጫካው ውስጥ እንዳሉ መረጃ የደረሰው ፖሊስ የቀሩትን ሰዎች ፈልጎ ለማግኘት ከአርብ ጠዋት ጀምሮ ፍለጋ እያካሄደ ነው።
በተጨማሪም በጫካው ውስጥ ትኩስ የመቃብር ስፍራዎች በማግኘቱ በዚህ ዙሪያ ምርመራ እንደሚያደርግ ተገልጿል።
በጫካው ውስጥ የቆዩት ሰዎቹ ‘ጉድ ኒውስ ኢንትርናሽናል ቸርች’ የተባለው ቤተክርስቲያን ምዕመናን ሲሆኑ የቤተክርስቲያኗ መሪ ፓስተር ማኬንዚ ንቴንጌ በፖሊስ ክትትል የሚደረግበት ግለሰብ ነው።
የአካባቢው የሃይማኖት ሰባኪ የሆነው ይህ ግለሰብ ከዚህ በፊትም ተከታዮቹን በፍጥነት ወደ መንግሥተ ሰማያት መግባት የሚፈልጉ ከሆነ በጾም እራሳቸውን በመጉዳት እንዲሞቱ ሲያበረታታቸው ነበር ተብሏል።
ፓስተር ማኬንዚ ንቴንጌ የቤተክርስቲያኗ አባል ከሆኑ ወላጆች ሁለት ልጆች ሞት ጋር በተያያዘ ክስ ቀርቦበት የነበረ ሲሆን፣ ጥፋተኛ አይደለሁም ብሎ በመከራከሩ ባለፈው ወር በፖሊስ ዋስ ከእስር መፈታቱም ተገልጿል።
በዚህ እና በሌሎች ምክንያቶች የተነሳ በፖሊስ የቅርብ ክትትል ይደረግበት የነበረ ሲሆን፣ አሁን ደግሞ ለአራት ሰዎች ሞት እና ለበርካቶች መጎዳት ምክንያት ሆኗል።
በጫካ ውስጥ ካጋጠመው ክስተት በኋላ ፓስተር ማኬንዚ ንቴንጌ በአሁኑ ወቅት የት እንዳለ አልታወቀም።
ለተፈጠረው ሁኔታ መረጃ ከደረሰው በኋላ “የተጠርጣሪውን ምግብ አቁመው በረሃን መሞት ኢየሱን ለማግኘት ያበቃል የሚለውን ስብከት አምነው የተቀበሉ የተቀበሉ የዋህ ምዕመናን” ሞተው እና ከባድ ጉዳት ደርሶባቸው እንዳገኘ ፖሊስ ገልጿል።
በተጨማሪም አስከ 31 የሚደርሱ ሰዎች የተቀበሩበት የጅምላ መቃብር ሊኖር እንደሚችል ማስጠንቀቂያ እንደደረሰው ፖሊስ ባወጣው መግለጫ አመልክቷል።
ከእንዲህ አይነት የእምነት ሰባኪያን ምክር ጋር በተያያዘ በሚፈጸሙ የጾም እና ሌሎች ትዕዛዞች ምክንያት ምዕመናን በተለያዩ አገራት መሞታቸው ተዘግቧል።
ከሳምንታት በፊት ሞዛምቢክ ውስጥ አንድ ፓስተር እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ አርባ ቀን እና ሌሊት እጾማለሁ ብሎ በመሞከሩ ክፉኛ ተጎድቶ ሆስፒታል ከገባ በኋላ ለሕልፈት መብቃቱ ይታወሳል።