እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ 40 ቀናት ለመጾም የሞከረው ሞዛምቢካዊ ፓስተር ሕይወቱ አለፈ

ፍራንሲስ ባራጃህ የተባለው ፓስተር ኢየሱስ ክርስቶስ በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ለ40 ቀናት በመጾም ያደረገውን ምሳሌ ለመድገም ባደረገው ሙከራ ነው ለሕልፈት የተዳረገው።

ፓስተሩ በሞዛምቢክ ማዕከላዊ ግዛት ማኒሺያ ውስጥ የምትገኘው ሳንታ ትሪንዳድ ወንጌላዊት ቤተክርስቲያን መሥራች ሲሆን ከጾሙ ጋር በተያያዘ ሕይወቱ ማለፉ ረቡዕ ዕለት ተረጋግጧል።

ፓስተር ፍራንሲስ ባራጃህ በጾሙ ምክንያት ክፉኛ በተዳከመበት ጊዜ ወደ ሆስፒታል የተወሰደ ቢሆንም ሕይወቱን ለማትረፍ ሳይቻል መቅረቱ ተዘግቧል።

ፓስተሩ ጾሙን ለ40 ቀናት ለማድረግ አቅዶ የነበረ ቢሆንም፣ ከ25 ቀናት ጾም በኋላ ግን በከፍተኛ ሁኔታ ክብደቱ ቀንሶ ለመቆምም ሆነ ለመራመድ ከማይችልበት ደረጃ ላይ ደርሶ ነበር።

ይህም ሆኖ ግለሰቡ በጾሙ የቀጠለ ሲሆን፣ ከቀናት በኋላ ግን በዘመዶቹ እና በቤተክርስቲያኗ አባላት ውትወታ ወደ ሆስፒታል ተወስዷል።

በጾሙ ክፉኛ የተዳከመው የ39 ዓመቱ ፓስተር ከፍተኛ የደም ማነስ እና የሆድ እቃ ክፍሎቹ ሥራ ማቆም እንዳጋጠመው ሐኪሞች አረጋግጠዋል።

ሕይወቱን ለማትረፍም ደም እና ፈሳሽ ምግቦት ቢሰጠውም፣ በጾሙ ምክንያት ክፉኛ በመጎዳቱ የተነሳ ሐኪሞች ጤናውን ለመመለስ ያደረጉት ሙከራ ሳይሳካ ለህልፈት ተዳርጓል።

ፓስተር ፍራንሲስ ባራጃህ ጾሙን ከጀመረ በኋላ በታየበት ከፍተኛ አካላዊ ለውጥ የተነሳ የቤተክርስቲያኗ አባላት እና በዙሪያው ያሉ ሰዎች ሕልፈቱ ብዙም አላስደነቃቸውም።

ፍራንሲስ ባራጃህ በጾሙ ወቅት ከፍተኛ የክብደት መቀነስ እና የሰውነት አቋሙም ተቀይሮ እንደነበር ተነግሯል።

ፓስተሩ ከሃይማኖት ሰባኪነቱ በተጨማሪ ሞዛምቢክ ከዚምባብዌ ጋር በምትዋሰንባት ማኒካ ግዛት ውስጥ ባለችው ሜሲካ ከተማ ውስጥ ፈረንሳይኛ ቋንቋ መምህርም ነበር።

ፓስተር ፍራንሲስ ባራጃህ በመሠረታት እና በሚመራት ሳንታ ትሪንዳድ ወንጌላዊት ቤተክርስቲያን ውስጥ ምዕመናን እና ፓስተሩ የሚያደርጉት ጾም የተለመደ ቢሆንም፣ እሱ እንዳደረገው አይነት ግን ረጅም ቀናት ጾመው እንደማያውቁ የቤተክርስቲያኗ አባላት ተናግረዋል።

የፓስተሩ ወንድም ማርከስ ማኑኤል ባራጃህ ወንድሙ መጾሙን ገልጾ ገልጾ ነገር ግን በህክምና ባለሙያዎች የተሰጠው ምክንያትን እንደማይቀበለው ተናግሯል።

ለወንድሙ ሞት “እውነታው ወንድሜ ዝቅተኛ የደም ግፊት ነው” ብሏል።

በበማቲዎስ ወንጌል ላይ እንደሰፈረው ኢየሱስ ክስቶስ በበረሃ ውስጥ ለ40 ቀናት እና ሌሊቶች የጾመውን ጾም ለመጾም አደገኛ ሙከራ ሲደረግ ይህ የፓስተር ባራጃህ ሙከራ የመጀመሪያው አይደለም።

ከሰባት ዓመት በፊት በተመሳሳይ የሞዛምቢክ ጎረቤት በሆነችው ዚምባብዌ ውስጥ አንድ ግለሰብ ለ30 ቀናት ከጾመ በኋላ መሞቱን የአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

እንዲሁም ዩናይትድ ኪንግደም ለንደን ውስጥ በአውሮፓውያኑ 2006 ላይ አንዲት ሴት ተመሳሳይ ሙከራ አድርጋ ጾሙን ካጋመሰች በኋላ ለሞት መብቃቷን ሐኪም አረጋግጧል።