ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በኬንያ አል-ሸባብ በተጠረጠረበት ጥቃት 5 ሰዎች በአደባባይ ተቀሉ
በኬንያ ጽንፈኛው እስላማዊ ቡድን አል-ሸባብ ሳይፈጽመው አልቀረም በተባለ ጥቃት አምስት ሰዎች አንገታቸው ተቀላ።
ይህ የሆነው በሕንድ ውቅያኖስ ዳርቻ በምትገኘው እና ለሶማሊያ ቅርብ በሆነችው የኬንያዋ ላሙ ግዛት ነው።
አል-ሸባብ በተጠረጠረበት ድርጊት አምስት ሰዎች ከመገደላቸው በተጨማሪ በርካታ ቤቶች ተቃጥለዋል።
የፖሊስ ሰነድ ጥቃቱን ያደረሱት ግለሰቦች በቁጥር ከ20 እስከ 30 እንደሚሆኑ ያሳያል።
ጥቃት አድራሾቹ ቅዳሜ ምሽት በሥፍራው የሚገኝ አንድ ገበያ ተቆጣጥረው አምስት ወንዶችን ከቤታቸው ጎትተው አምጥተው ቀልተዋቸዋል።
የዓይን እማኞች እንደገለጡት ጥቃቱን ያደረሱት ግለሰቦች የወታደር መለዮ ለብሰው ነበር።
ከሁለት ሳምንታት በፊት የኬንያ መከላከያ ኃይል አባላትና ሌሎች ሰዎችን ያሳፈረ መኪና መንገድ ላይ የተቀበረ ተቀጣጣይ ፈንጅ ረግጦ በርካቶች ተጎድተው ነበር።
ባለፉት ወራት በኬንያ እና ሶማሊያ ድንበር ላይ የሚገኙ መንገዶች በመሰል ቦንቦች እየተሞላ መጥቷል።
ቤት ውስጥ በሚሠራው ቦንብ [አይኢዲ] ምክንያት የፀጥታ አካላትን ጨምሮ በርካታ ሰዎች ከዚህ ቀደም ተገድለዋል።
ላሙ የተሰኘችው የባሕር ዳርቻ ኬንያና ሶማሊያ ከሚወሳኑበት ሥፍራ አቅራቢያ ትገኛለች።
የአል-ሸባብ ታጣቂዎች በላሙ በተደጋጋሚ ጥቃት አድርሰዋል።
ከዘጠኝ ዓመታት በፊት የአል-ሸባብ ታጣቂዎች ፔኬቶኒ በተሰኘው ሥፍራ ቢያንስ 90 ሰዎችን መግደላቸው ይታወሳል።
ኬንያ በላሙ በኩል ከሶማሊያ ጋር የሚያዋስናትን ድንበር ከዘጋች ከ10 ዓመት በላይ ሆኗታል።
ነገር ግን ባለፈው ወር የሃገር ውስጥ ደኅንነት ሚኒስትሩ በላሙ፣ ጋሪሳ እና ማንዴራ በኩል ያሉ ድንበሮች በሚቀጥሉት 90 ቀናት እንደሚከፈቱ ገልጠዋል።