በአሁኑ ወቅት በአትሌቲክስ አዲስ የዓለም ክብረ ወሰን ማስመዝገብ እየከበደ መጥቷል?

ከአትሌቲክስ ውድድሮች መካከል በፈታኝነቱ የሚጠቀሰው የማራቶን ውድድር ክብረ ወሰን ከጊዜ እየተሻሻለ አሁን ላይ ደርሷል። ከዚህም በኋላ የውድድር ጊዜው እያጠረ ከሁለት ሰዓት በታች ይወርዳል ተብሎ ይጠበቃል።

ባለፈው መስከረም አጋማሽ በጀርመን በርሊን ከተማ በተካሄደ 48ኛው የማራቶን ውድድር ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ትዕግሥት አሠፋ የዓለም የሴቶች ማራቶን ክብረ ወሰንን በማራቶን ላይ እምብዛም በማይታይ ሁኔታ በሰፊ ደቂቃዎች ልዩነት አሻሽላ አድናቆትን እግኝታለች።

የ29 ዓመቷ ትዕግስት ከሦስት ዓመት በፊት ቺካጎ ላይ በኬንያዊቷ አትሌት ብሪጊድ ኮስጌ ተመዝግቦ የነበረውን 2:14.04 ክብረ ወሰን ወደ ሁለት ሰዓት ከ11 ደቂቃ ከ53 ሰከንድ በማውረድ ከሁለት ደቂቃ በላይ በማሻሻል ነው አሸነፈች።

ይህም በማራቶን ውድድር በሰፊ የሰዓት ልዩነት ከተሻሻሉ ክብረ ወሰኖች መካከል የሚጠቀስ ነው። አንዳንዶች እንዲያውም ይህንን ሰዓት መልሶ ለማሻሻል ዓመታትን ሊጠይቅ ይችላል እያሉ ነው።

ዩክሬናዊቷ አትሌት ያርስላቫ ማሁቺካ በሴቶች የከፍታ ዝላይ አዲስ የዓለም ክብረ ወሰን አስመዝግባለች።

ክብረ ወሰኑ ለ37 ዓመታት ሳይደፈር የቆየ ነበር። ሰኔ 30/2016 ዓ.ም. ነበር ክብረ ወሰኑን የሰበረችው።

ያርስላቫ ባለፈው ሳምንት በጀነረው የፓሪስ ኦሊምፒክ ላይ ዝነኛ ከሆኑ አትሌቶች አንዷ ናት።

የስፖርት ተንታኞች እንደሚሉት ስኬቷ ልዩ የአትሌቲክስ ምዕራፍ ነው።

በአትሌቲክስ አብዛኞቹ ክብረ ወሰኖች የተሰበሩት በአውሮፓውያኑ 1980ዎቹ ነበር።

ማሁቺካ የሠራችው ታሪክ

የ22 ዓመቷ አትሌት ማሁቺካ 2.10 ሜትር ከፍታ በመዝለል አዲስ የዓለም ክብረ ወሰን ይዛለች።

ከዚህ በፊት የነበረው የዓለም ክብረ ወሰን የ2.09 ሜትር ከፍታ ሲሆን፣ ይህም የተያዘው በ1987 በሮም በስቲፋ ኮስታዲኖቫ ነው።

ኮስታዲኖቫ አዲሱን የዓለም ክብረ ወሰን “ታሪካዊ” ብላዋለች።

ይህን ያለችው ለ37 ዓመታት ተይዞ የነበረው ክብረ ወሰን ስለተሻሻለ ብቻ ሳይሆን 2.10 ሜትር ከፍታ መዝለል “የሰው ልጅ ማድረግ ለሚችለው ነገር ገደብ እንደሌለው ያሳየ እና አንዳንድ ሪከርዶች እስከወዲያኛው አይሰበሩም የሚለውን የተዛባ ምልከታ ያስተካከለ” በመሆኑ ጭምር ነው።

ማሁቺካ ከቤተሰቦቿ ጋር የትውልድ ቀዬዋ ድንፒሪን ጥላ የወጣችው ሩሲያ ዩክሬንን ከወረረች በኋላ ነው።

ለሦስት ቀናት 2,000 ኪሎ ሜትር ተጉዛ ነው ቤልግሬድ፣ ሰርቢያ የገባችው።

ሰርቢያ ሳለች በዓለም የቤት ውስጥ ሻምፒዮና ላይ በከፍታ ዝላይ አዲስ የዓለም ክብረ ወሰን አስመዝግባለች።

አሁን የምትኖረው ፖርቹጋል ነው።

በደስታ ተሞልታ “በስተመጨረሻ ዩክሬንን በዓለም አትሌቲክስ መዝገብ ስሟን አስገባሁ” ብላለች።

በፓሪስ ኦሊምፒክ ላይ ደግሞ የወርቅ ሜዳሊያ ለማግኘት ተስፋ አድርጋለች።

የቀድሞ የዓለም ሪከርዶች

ዩሴን ቦልት የዓለማችን የአጭር ርቀት ፈጣን ሰው ነው።

ጃማይካዊው አትሌት 100 ሜትር ከ9.6 ሰከንድ በታች በመሮጥ የመጀመሪያው ሰው ነው።

በአውሮፓውያኑ በ2008 በበርሊን የዓለም ቻምፒዮና ላይ 9.58 ሰከንድ አስመዝግቧል።

አሁን በ1,500 ሜትር እና በአንድ ማይል የዓለምን ክብረ ወሰንን የያዘችው የኬንያዋ አትሌት ፌዝ ኪፕዬጎን ናት።

በ2024 እና በ2023 ነው እነዚህን ክብረ ወሰኖች የያዘችው።

ቬንዝዌላዊቷ ዩሊማር ሮጃስ በሴቶች ስሉስ (ትሪፕል) ዝላይ በ15.74 ሜትር የዓለም ሪከርድ ይዛለች።

አሁንም ድረስ ሊሰበሩ ያልቻሉ የዓለም ክብረ ወሰኖች የተመዘገቡት በአውሮፓውያኑ በ1980ዎቹ አጋማሽ ነው።

የቀድሞ ጋዜጠኛ እና አሁን የዩክሬን ወታደራዊ ኃይል ኃላፊ ዩሪ ኦኑሽቼንኮ “የተከለከሉ መድኃኒቶች” ከዚህ ጀርባ እንዳሉ ይናገራል።

“ብዙ አትሌቶች የሆርሞን እና ስቴሮይድ አበረታች መድኃኒቶች ይወስዳሉ። በስፖርት ውስጥ ባለፉት ከ35 እስከ 40 ዓመታት የተገኙ ለውጦች፣ የአመጋገብ ሥርዓት እና ልምምድ ዘመናዊ አትሌቶች እንደ ቀድሞዎቹ አትሌቶች ውጤት እንዲያመጡ አላስቻሉም” ይላል።

በሱፎልክ ዩኒቨርስቲ የስፖርት እና አካል ብቃት ሳይንስ መምህር ጆን ብሪወር “ያኔ ሪከርዶች ሲያዙ ሕጋዊ የነበሩ አበረታች መድኃኒቶች ለውጤቶቹ ድጋፍ አድርገዋል ማለት ይቻላል። አሁን እነዚህ መድኃኒቶች ሕገ ወጥ ናቸው” ይላል።

የአበረታች መድኃኒት አጠቃቀምን ለመመርመር ጥቅም ላይ የሚውለው አሠራር እንደተሻሻለ እና ስለ አበረታች መድኃኒት የሚሰጠው ትምህርትም እንደተለወጠ ይናገራል።

“ሁሉም አገር በዓለም ፀረ አበረታች መድኃኒት ተቋም ሥር የሚተዳደር፣ ብሔራዊ የፀረ አበረታች መድኃኒት ተቋም አለው” ሲል ያክላል።

በጥቅምት 6/1985 (እአአ) የምሥራቅ ጀርመኗ አትሌት ማሪታ ኮች 400 ሜትር በ47.6 ሰከንድ በመሮጥ የዓለም ክብረ ወሰንን ያዘች።

በአውስትራሊያ፣ ካንቤራ ላይ ነበር ይህ ክብረ ወሰን የተያዘው። እስካሁንም ማንም ሰው ሊያሻሽለው ባለመቻሉ መነጋገሪያ ሆኗል።

በወቅቱ ምሥራቅ ጀርመን ለአትሌቶች አበረታች መድኃኒት በመስጠት ትታወቅ ነበር።

ሆኖም ግን አትሌቷ የአበረታች መድኃኒት ምርመራ ወድቃ አታውቅም። ምንም ጥፋት እንዳልሠራችም ትናገራለች።

አሜሪካዊቷ ስፕሪንተር ፍሎረንስ ግሪፊት ጆይነር የዓለም የሴቶች የአጭር ርቀት ሩጫን ክብረ ወሰን የያዘችው በአውሮፓውያኑ በ1988 ነበር።

ክብረ ወሰኑን የያዘችው በ100 ሜትር እና በ200 ሜትር ሩጫ ሲሆን፣ በ1988 በበጋ ኦሊምፒክ 100 ሜትርን በ10.54 ሰከንድ አጠናቃለች። የቅርብ ተፎካካሪዋን በ0.30 ሰከንድ ነበር የቀደመችው።

በ200 ሜትር ሩጫ ደግሞ የዓለም ክብረ ወሰንን የያዘችው በ21.56 ሰከንድ ሲሆን፣ ይህንን ሪከርድ በ0.22 በማሻሻል በ21.34 ሰከንድ አዲስ ክብረ ወሰን ይዛለች።

አሁንም ድረስ እነዚህ ክብረ ወሰኖች አልተሰበሩም።

አበረታች መድኃኒት ወስዳለች በሚል ክስ ቢቀርብባትም በምርመራ ምንም አልተገኘባትም። በ1988 (እአአ) ውድድር ላይ 11 ጊዜ ብትመረመርም አበረታች መድኃኒት መውሰዷን የሚያመለክት ነገር አልተገኘም።

የሴቶች ረዥም ርቀት ዝላይ ሪከርድ የተያዘው በጋሊና ቺስታያኮቫ ነው። በቀድሞዋ ሶቭየት ኅብረት ሥር ውድድሩን በ1988 ስታደርግ 7.52 ሜትር ከፍታ ዘላለች።

በትሌቲክስ ታሪክ ለረዥም ጊዜ የቆየው ሪከርድ በጀርሚላ ክራታቾቪሎቫ ነው። በ1983 በተካሄ የ800 ሜትር ሩጫ ውድድር የ1፡53፡28 ሪከርድ ይዛለች።

የሰዎች አቅም ውስንነት

የስፖርት እና የአካል ብቃት ሳይንስ መምህሩ ጆን ብሪወር እንደሚለው፣ በዓለም አትሌቲክስ ክብረ ወሰኖችን መስበር ከባድ እየሆነ መጥቷል።

“ባለፉት ዓመታት የሚታየው ብቃት እያደገ መጥቷል። መጨረሻ ላይ የሰው ልጆች መሄድ የሚችሉበት ጥግ ድረስ ነው መሄድ የሚችሉት” ይላል።

ባለሙያው እንደሚያስረዳው፣ በጊዜ ሂደት የታየው የብቃት መሻሻል እንዲሁም የጊዜ እና የብቃት መሻሻል ነው።

“ይሄ ቀስ በቀስ የሰው ልጅ ሰውነት መሄድ የሚችልበት የብቃት ጥግ ድረስ መሄዱ አይቀርም” ሲል ያክላል።

በሥልጠና፣ በስፖርት ሳይንስ እና በቴክኖሎጂ ዕደገት በመታገዝ “በሁሉም ዘርፎች ለውጥ መፈለጋችንን እንቀጥላለን” ይላል።

አያይዞም “የመሻሻል ደረጃው ቀስ በቀስ ዝግ እያለ መሄዱ አይቀርም። በአንዳንድ ስፖርቶች ያየነውም ያንን ነው” በማለት ያስረዳል።

የመሮጫ ሜዳ መሻሻል እና ዘመናዊው የካርቦን ፋይበር መሮጫ ጫማ መመረት የቴክኖሎጂ ዕድገትን ካሳዩ መካከል ናቸው።

የካርቦን ፋይበር መሮጫ ጫማ ኃይልን ለአትሌቶች በመስጠት ጉልበታቸው እንዳይደክም የሚያግዝ ነው።

“አትሌቶቹ ኃይል ቆጥበው የተሻለ መሮጥ እንዲችሉ ያደርጋል። ረዥም ርቀት በፍጥነት መሮጥ ይችላሉ ማለት ነው” ሲልም ያስረዳል ባለሙያው።

የስፖርት የሥነ ልቦና ባለሙያ እና ላቲቲዩድ ፐርፎርማንስ መሥራች ሶፊ ብሩስ በበኩሏ የአትሌቶችን ብቃት በቴክኖሎጂ ታግዞ መለካት ቢቻልም እንኳን፣ “አንዳንድ ብቃቶችን ለመመዘን ይከብዳል። ለምሳሌ ተስፋ፣ ቁርጠኝነት፣ መነሳሳት የአእምሮ ብቃትን መለካት ያስቸግራል” ትላለች።

“እነዚህ ነገሮች ተደማምረው ብቃትን እንደሚያሳድጉ እና ለውጤታማነት ትክክለኛው ሰዓት፣ ከትክክለኛው ሁኔታ ጋር ለትክክለኛው ሰው መግጠም እንዳለበት ስናስብ ሪከርድ መስበር ምን ያህል ከባድ እንደሆነ እንረዳለን” ስትልም ታስረዳለች።

ሶፊ እንደምትለው፣ ክብረ ወሰኖች ያሉት “ለመሰበር ብቻ” አይለም።

“ሪከርዶች የለውጥ እና የዕድገት ምልክት ናቸው። በታሪክ የማይቻል የተቻለባቸውን እና አትሌቶች በስፖርት ታላቅ ነገር ያከናወኑባቸውን ጉልህ ቅጽበቶች ይወክላሉ” ትላለች።