ለክተት ተጠርተው የነበሩት የኤርትራ ተጠባባቂ ጦር አባላት ወደየቤታቸው እየተመለሱ ነው

ትግራይ ውስጥ ሲካሄድ በነበረው ጦርነት ውስጥ ተሳትፎ የነበራት ኤርትራ ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር ላይ ጦርነቱ ማገርሸቱን ተከትሎ የተጠባባቂ ጦር አባላቷን በመጥራት ወደ ጦሩ እንዲቀላቀሉ ማድረጓ በስፋት ተዘግቧል።

ከሦስት ወራት በፊት በኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥት እና በህወሓት መካከል ጦርነት ለማቆም ስምምነት ከተደረሰ በኋላ በተለይ ካለፈው መስከረም ወዲህ ወደ ጦር ግንባሮች ተሰማርተው የቆዩ የተጠባባቂ ሠራዊት አባላት ወደ የቤታቸው እየተሸኙ እንደሆነ ቢቢሲ ያነጋገራቸው የተሸኚዎች እና ቤተሰቦቻቸው አረጋገጡ።

የተጠባባቂ ሠራዊት አባላት ተሰማርተው ከነበሩባቸው ግንባሮች ከተመለሱ በኋላ “የአንድ ወር የመንቀሳቀሻ ፍቃድ” ተሰጥቷቸው ወደ የመጡበት እንደተሸኙ ቢቢሲ ተረድቷል።

የመጨረሻው ዙር ጦርነት በተፋፋመበት እና ኤርትራ ሠራዊቷን ከኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ጎን አሰልፋ ከትግራይ ኃይሎች ጋር ስትዋጋ በነበረበት ጊዜ፣ ከመደበኛ ሠራዊቷ በተጨማሪ በተለያዩ የሥራ ዘርፎች ተሰማርተው የነበሩ ከ55 ዓመት በታች፣ በአንዳንድ ቦታዎችም ከዚህ በላይ የሆኑ ወንዶችን “ለክተት” መጥራቷ ይታወሳል።

ለሁለት ዓመታት የተካሄደውን ጦርነት ያበቃው በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ጥቅምት 23/2015 ዓ.ም. በተፈረመው ስምምነት፣ ከፌደራል መንግሥቱ ሠራዊት ውጪ የሆኑ ኃይሎች ከትግራይ እንዲወጡ እንዲሁም የህወሓት ተዋጊዎች ትጥቅ እንዲፈቱ እንደሚደረግ ተገልጿል።

ይህንንም ተከትሎ ከከጥር ወር መጀመሪያ አንስቶ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የኤርትራ ወታደሮች ድል እንደተቀዳጁ በሚገልጹ መፈክሮች ታጅበው ከተለያዩ የትግራይ ከተሞች በመውጣት ወደ ኤርትራ ግዛት መግባታቸውን ነዋሪዎች ለቢቢሲ መግለጻቸው ይታወሳል።

ወደ ኤርትራ ተመልሰው ቢቢሲ ያነጋገራቸው የተጠባባቂ ሠራዊት አባላት እንዳሉት “ሁሉም በጦር ግንባር ተሰማርተው የቆዩ የሕዝባዊ ሠራዊት አባላት ተመልሰዋል። በርካታ ቋሚ ሠራዊት አባላትም ወደ ቀድሞ ቦታቸው ተመልሰዋል” ይላሉ።

ባለፉት ስድስት ወራት በየግንባሩ ተሰልፈው የቆዩት የተጠባባቂው ሠራዊት አባላቶት “ሁሉም” እንደተመለሱ ቢቢሲ ያገኘው መረጃ ቢያመለክትም፣ የኤርትራ ሠራዊት ሙሉ በሙሉ ከትግራይ መውጣቱን በተመለከተ “የሚያውቁት ነገር እንደሌለ” ተናግረዋል።

ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ላይ በተባበሩት መንግሥታት የአሜሪካ አምባሳደር የሆኑት ሊንዳ ቶማስ ግሪን ፊልድ የኤርትራ ጦር ከትግራይ የመውጣት እንቅስቃሴ ማድረጉን ጠቅሰው፣ ነገር ግን በድንበር አካባቢ በኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ እንደሚገኛ መናገራቸው ይታወሳል።

ከቤተሰብ ጋር መገናኘት

ከጦር ግንባር ከተመለሱት የተጠባባቂ ጦር አባላት መካከል አንዱ የሆነው እና በጸሮና አካባቢ ተሰማርቶ የቆየው ስሙ እንዲገለጽ ያልፈለገው የዋና ከተማዋ አሥመራ ከተማ ነዋሪ “አዎ ተመልሰናል፤ አሁን ከልጆቼ ጋር ቤቴ ነኝ” በማለት ከጦር ግንባር መመለሱን ለቢቢሲ አረጋግጧል።

ግለሰቡ ላለፉት አምስት ወራት የነበረበትን ሁኔታ በተመለከተ ዝርዝር መረጃ ለመስጠት ፈቃደኛ ባይሆንም “በአጠቃላይ ሁኔታው አስቸጋሪ ነበር። ጦርነት ውስጥ ምን መልካም ነገር አለ?” ሲል በጥያቄ የነበረበትን ሁኔታ ገልጿል።

ጨምሮም እሱ በነበረበት አካባቢ የተሰማሩ የተጠባባቂ ጦር አባላት ወደ ውጊያ እንዳልገቡ በመግለጽ፣ ይሁን እንጂ በዕድሜ መግፋት፣ በጤና ሁኔታ፣ ቤተሰቦቻቸውን እና ልጆቻቸውን ከኋላ መተዋቸው በፈጠረባቸው ጫና “ሁኔታው በጣም ፈታኝ ነበር፣ ግን እንኳንም ከዚህ በላይ አልዘለቀ” ብሏል።

ሌላው ከጋሽ ባርካ ዞን ወደ ጦር ግንባር ተሰማርቶ የነበረው የተጠባባቂ ሠራዊት አባል በሰላም ወደ ቤቱ በመመለሱ ደስተኛ መሆኑን ገልጾ፣ ነገር ግን በነበረባቸው ስር የሰደደ በሽታ፣ በወባ፣ በአደጋና እና በሌሎች ምክንያቶች የሞቱ ወይም የአካል ጉዳት የደረሰባቸው ሊኖሩ እንደሚችሉ ያምናል።

የተጠባባቂ ሰራዊት አባላት በአካባቢያቸው አስተዳደር በኩል የደረሳቸውን ጥሪ ተከትሎ መስከረም ወር አጋማሽ ላይ ወደ ተመደቡበት ቦታ እንደሚሄዱ እንጂ የሚሄዱበት የጦር ግንባር በግልጽ አልተነገራቸውም ነበር።

ሆኖም አብዛኞቹ በደቡብ እና በጋሽ ባርካ ዞኖች በሚገኙት ግንባሮች ላይ “እንደ ተጠባባቂ ኃይል በተጠንቀቅ” እንደነበሩ ቢቢሲ ከተጠባባቂ ጦር አባላቱ ተረድቷል።

በኢትዮጵያ ሲካሄድ የነበረው ጦርነት እየተጠናከረ ሲሄድ ኤርትራ ውስጥ ከሞላ ጎደል በሁሉም አካባቢዎች ጾታ ሳይለይ ወጣቶች ይታፈሱ እንደነበር መዘገቡ አይዘነጋም።

የሁሉም የተጠባባቂ ጦር አባል ወደ ጦር ግንባር እንዲከት በታዘዘው መሠረት የጤና ችግር የነበረበት ባለቤቷ ለዘመቻ ሄዶ የነበረባት የደቡብ ዞን ነዋሪ የሆነችው አስመረት [ስሟ የተቀየረ] ባለቤቷ በሰላም መመለሱን አረጋግጣለች።

ሳህለ እና ሼካይ ብዙ የጤና ችግር እንዳልገጠማቸው ነገር ግን “ወታደርነት ከወጣትነት ጋር ነው የሚሄደው” ሲሉ ከእርጅና ጋር ተያይዞ እንዲሁም የቤተሰብ እና የልጆች ኃላፊነት መኖሩ በዘመቻው ጊዜ ብዙ እንደተቸገሩ አልደበቁም።

ደስታ እና ተስፋ

ከኢትዮጵያ የእርስ በርስ ጦርነት መባባስ ጋር ተያይዞ ከስድስት ወራት በፊት በተለይ በግል ሥራ ለተሰማሩት የተጠባባቂ ሠራዊት አባላት የቀረበው የክተት ጥሪ፣ በርካታ ቡተሰቦች አስቸጋሪ ወቅትን እንዲያሳልፉ ማስገደዱ ብዙዎቹ ይናገራሉ።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው የተጠባባቂ ሠራዊት አባላት እና ቤተሰቦቻቸው፣ አባወራዎች ወደ ጦር ግንባር ከተሰማሩ በኋላ የቤተሰቡ የገቢ ምንጭ በመቋረጡ ችግር አጋጥሟቸው ለወራት ቆይተዋል።

ጋሽባርካ ውስጥ በንግድ ሥራ ላይ ተሰማርቶ ቤተሰቡን ሲያስተዳድር የነበረው ሼካይ፣ ባለቤቱ እና ልጆቹ ሙሉ በሙሉ በእሱ ላይ ጥገኛ እንደነበሩ እና ወደ ሠራዊቱ ከተቀላቀለ በኋላ ቤተሰቡ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ወድቆ እንደነበር ለቢቢሲ ገልጿል።

“ሁኔታው ሳናስበው ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደረሰ። እና ከአካባቢያችን አርቀው የሚወስዱን አልመሰለንም፤ አልተዘጋጀንም። ቤተሰብ ግን ችግር ውስጥ መግባቱ አይቀርም. . .” ሲል ሁኔታው ድንገት ሆኖ ዕድል እንዳልሰጣቸው ያስታውሳል።

በተለይ ያለፉት ስድስት ወራት ኑሮ እንደከበዳት የምትገልጸው አስመረት “. . . ሕይወታችን ድሮም በድጋፍ ላይ የተመሠረተ ነበር። ነገር ግን በውጭ አገር የሚኖር ወንድሜ ረድቶናል” በማለት ወንድሟን ታመሰግናለች።

በግል እየሰሩ ቤተሰባቸውን ሲያስተዳድሩ የነበሩ የተጠባባቂ ሠራዊት አባላት፣ እነሱ ወደ ጦር ግንባር ከተንቀሳቀሱ በኋላ ቤተሰቦቻቸውን ለመደገፍ ወይም የሚያገኙትን ገቢ ለማካካስ በመንግሥት በኩል የተደረገ ነገር እንዳልነበረ አስተያየት የተጠባባቂ ጦሩ አባላት እና ቤተሰቦቻቸው ይናገራሉ።

በጦር ግንባር ተሰማርተው የቆዩት የኤርትራ የተጠባባቂ ሠራዊት አባላት እያንዳንዳቸው የአንድ ወር የመንቀሳቀሻ ፈቃድ ይዘው ወደየነበሩበት ተመልሰው ኑሯቸውን እና ሥራቸውን ወደነበረበት ለመመለስ እየጣሩ ይገኛሉ።

ከቀደመው የድንበር ጦርነት ማብቃት በኋላ የነበረው የ20 ዓመታት ፍጥጫ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ ሥልጣን መምጣታቸውን ተከትሎ የሰላም አየር ቢነፍስም ብዙም ሳይቆይ ነው በትግራይ ጦርነት ተቀስቅሶ የኤርትራ ሠራዊት መሳተፍ የጀመረው።

ይህም በርካታ ኤርትራውያን ስለወደፊቱ እርግጠኛ እንዳይሆኑ እንዳደረጋቸው የሚናገረው ሼካይ “ከዚህ በኋላ ምን ሊከተል ይችላል?” የሚል ጥያቄ አስጨናቂ ቢሆንም፣ በኢትዮጵያ እየታየ ያለው ሰላማዊ ሁኔታ ግን የሚያስጨንቀውን ነገር እንዲቀል እያደረገው መሆኑን ገልጿል።

ሳህለም በበኩሉ “እኛ ብቻ ሳንሆን በቋሚነት ሠራዊቱ ውስጥ የቆዩትም እየተመለሱ ነው” በማለት ለሰላም እና ለመደበኛ ሕይወት ያለውን ተስፋ ይገልጻል።