ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ትራምፕ ከባለፈው ምርጫ ጋር በተያያዘ በቀጣዩ ሀሙስ እንደሚታሰሩ ገለጹ
የቀድሞ የአሜሪካ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ በመጪው ሃሙስ በጆርጂያ በሚገኝ ፍርድ ቤት በመቅረብ ከምርጫ ጣልቃ መግባት ጋር በተያያዘ የቀረቡባቸው ክሶች ላይ ለመከራከር ማቀዳቸውን ተናግረዋል።
ትራምፕና ሌሎች ተከሳሾች እንደ አውሮፓውያኑ በ2020 በተካሄደው ምርጫ ወቅት በጆርጂያ ምርጫ ላይ ጣልቃ ለመግባት ሞክረዋል የሚል ክስ ቀርቦባቸዋል።
ጉዳዩን የሚከታተሉት ዳኛ የ200 ሺህ ዶላር ዋስትና ፈቅደውላቸዋል።
ለትራምፕ ዋስትና ሲሰጣቸው ምስክሮችን ለማስፈራራትና ለማዋከብ ካልሞክሩ ከእስር ነጻ ሆነው ጉዳያቸው እንዲከታተሉ ተፈቅዶላቸዋል።
ትራምፕ የማጭበርበር ሙከራና የሀሰት መግለጫዎች መስጠትን ጨምሮ የቀረቡባቸውን 13 ክሶች አይቀበሉም።
ትላንት ሰኞ የወጣው የፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ተከሳሹ ምስክሮችን ለማስፈራራት ወይም የፍርድ ሂደቱን ለማደናቀፍ እንዳይሞክሩ አዝዟል።
ይህም በማህበራዊ ሚዲያ የሚደረግ ሪፖርትን እንደሚጨምርም አመላክቷል።
ይህንንም ተከትሎ ትራምፕ ትላንት ማምሻውን በራሳቸው ማህበራዊ ትስርስር ገጽ ላይ ባሰራጩት መልዕክት “ይህንን ታምናላችሁ? ሀሙስ በአክራሪ ግራ ዘመሙ አውረጃ ጠቅላይ አቃቤ ህጓ ፋኒ ዊልስ ለመታሰር ወደ አትላንታ ጆርጂያ አቀናለሁ” ብለዋል።
ትራምፕ አቃቤ ህጓ ከጆ ባይደን አስተዳደር የፍትህ መስሪያ ቤት ጋር በማበር እሳቸውን ሊጎዱ እንዳቀዱም ከሰዋል።
ጠቅላይ አቃቤ ህጓ የትራምፕን ጉዳይ የሚከታተሉትን ዳኛ በቀጣዩ መስከረም መግቢያ ትራምፕ ላይ ይፋዊ ክስ እንዲመሰረት እና ጥፋተኛ ናቸው ወይስ አይደሉም የሚለውን ጉዳይ ለመወሰን የጊዜ ሰሌዳቸውን እንዲያስተካክሉ ጠይቀዋል።
በተጨማሪም የፍርድ ሂደቱ መጋቢት እንዲጀመር ሀሳብ አቅርበዋል።
ትላንት ሰኞ የትራምፕ ጠበቆች በአትላንታ ግዛት ፉልቶን ግዛት ታይተዋል።
ጠበቆቹ በስፍራው የተገኙት መርማሪዎችን ለማግኘትና የትራምፕ የዋስትና ጉዳይ ዝርዝር ላይ ለመደራደር እንደሆነ ሪፖርቶች ጠቁመዋል።
ትራምፕ እጃቸውን በሚሰጡበት ዕለት በስፍራው “ጠንካራ የእንቅስቃሴ ገደብ” እንደሚኖር የአካባቢው የጸጥታ ሃይል አሳውቋል።
ትራምፕ እጃቸውን ይሰጣሉ ተብሎ በሚጠበቅበት በዚህ ሳምንት በሚቀርቡበት ፍርድ ቤት አቅራቢያ በብረት ፍርግርጎች አጥር ተሰርተዋል።
እነዚህ የብረት ፍርግርጎች እስከ አርብ ድረስ እንደሚቆዩም የጸጥታ ሃይሎች ገልጸዋል።
ከትራምፕ ጋር 19 ተከሳሾች ፍርድ ቤት እንደሚቀርቡ ይጠበቃል።
ትራምፕና ሌሎቹ ተከሳሾች እንደ አውሮፓውያኑ በ2020 የተካሄደውን ምርጫ ባይደን በጆርጂያ ውጤት እንዲያጡ እና ሌላ ውጤት እንዲመጣ ሰርተዋል የሚል ክስ በዚህ ሳምንት ቀርቦባቸዋል።
የቀድሞ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ትራምፕ ብራድ ራፍንስፕሬገር ከተባሉ የጆርጂያው ሪፐብሊካን ባለስልጣን ጋር ባደረጉት የስልክ ልውውጥ በደምጽ ቆጠራ ወቅት 11 ሺህ 780 ድምጾችን እንዲፈልጉ ሲጠይቋቸው ተስምቷል።
በስልጣን ላይ ያለ ወይም የነበረ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ሶስት የወንጀል ክስ ሲቀርብበት ትራምፕ የመጀመሪያው ናቸው።
እሳቸው ግን ምንም ጥፋት የለብኝም ብለው የሚከራከሩ ሲሆን ክሶቹም ፖለቲካዊ ፍላጎት የተጫናቸው ናቸው ይላሉ።
የቅድሞ ፕሬዝዳንት ሪፐብሊካኖችን እየመሩ ሲሆን በ2024 ለሚደረገውና ምንአልባትም ባይደን ለሚሳተፉበት ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ተፎካካሪ ሆነው ይቀርባሉ።