ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የኢትዮጵያ እና የሌሎች አገራት የአባልነት ጥያቄን የሚመለከተው የብሪክስ ስብስባ እና ዓላማው
የብሪክስ አገራት መሪዎች ዛሬ [ነሐሴ 16/2015 ዓ.ም.] በአፍሪካዊቷ የቡድኑ አባል በደቡብ አፍሪካ፣ ጆሃንስበርግ ከተማ ይገናኛሉ።
የብራዚል፣ የሩሲያ፣ የሕንድ፣ የቻይና እና የደቡብ አፍሪካ መሪዎች በዚህ ስብሰባ ከሚያነሷቸው ቁልፍ የመወያያ አጀንዳዎች አንዱ ቡድኑ አዲስ አባል አገራትን በሚቀበልበት ጉዳይ ላይ እንደሚሆን ተገልጿል።
በማደግ ላይ ያሉ አገራት በዓለም የአስተዳደር ሥርዓት ውስጥ የጎላ ድርሻ እንዲኖራቸው ለማድረግ ያለመውን ብሪክስን ለመቀላቀል እስካሁን 40 ወይም ከዚያ በላይ አገራት እንደሚፈልጉ ደቡብ አፍሪካ ገልጻለች።
የብሪክስ ቡድን እንዴት ተፈጠረ?
ብሪክስ ብራዚል፣ ሩሲያ፣ ሕንድ፣ ቻይና እና ደቡብ አፍሪካን ያቀፈቡድን ነው።
ብሪክስ የሚለው መጠሪያ የእነዚህን አገራት ስም የእንግሊዝኛ የመጀመሪያ ፊደል በመጠቀም የተፈጠረ ስያሜ ነው።
ምሕጻረ ቃሉን ለመጀመሪያ ጊዜ ያስተዋወቁትም በጎልድ ማን ሳክስ ኢንቨስትመንት ባንክ የሚሠሩት የምጣኔ ሃብት ባለሙያው ጂም ኦ’ኔል ሲሆኑ፣ ጊዜውም እንደ አውሮፓውያኑ 2001 ነበር።
ባለሙያው መጀመሪያ ላይ ስያሜውን ‘ብሪክ’ ነበር ያሉት። ይህም የብራዚል፣ የሩሲያ፣ የሕንድ እና የቻይናን ስም የእንግሊዝኛ የመጀመሪያ ፊደላትን የሚይዝ ነው።
እነዚህ አገራት በጊዜው ትልቅ፣ መካከለኛ ገቢ ያላቸው እና ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት እያስመዘገቡ የነበሩ ናቸው። በዚህም የተነሳ የምጣኔ ሃብት ባለሙያው እነዚህ አገራት በአውሮፓውያኑ 2050 የዓለምን ኢኮኖሚ ሊመሩ እንደሚችሉ ተንብየው ነበር።
ይህንንም ተከትሎ እንደ አውሮፓውያኑ 2006 አራቱ አገራት አንድ ላይ ለመሆን ወስነው 'ብሪክ' የሚለውን ቡድን መሠረቱ።
መጀመሪያ ላይ ደቡብ አፍሪካ የስብስቡ አባል አገር አልነበረችም። በወቅቱ ስያሜው አንዳንዴ ‘ብሪክ’ አንዳንዴም በስተመጨረሻ የምትገኘው ኤስ (S) ፊደል የአባል አገራቱን ብዛት ለማመልከት ‘ብሪክስ’ እየተባለ ይጠራ ነበር።
ከዚያ ግን እንደ አውሮፓውያኑ 2010 ደቡብ አፍሪካ ይህንን ቡድን ተቀላቀለች። ‘ብሪክ’ የሚለው የስብስቡ ስምም ከደቡብ አፍሪካ ስም የእንግሊዝኛ የመጀመሪያው ፊደልን ጨምሮ ‘ብሪክስ’ የሚለውን ስያሜ በዘላቂነት ያዘ።
ብሪክስ ምን ያህል ጠንካራ ነው?
የብሪክስ አገራት በአጠቃላይ 3.24 ቢሊዮን የሕዝብ ብዛት አላቸው። አገራቱ ያላቸው ብሔራዊ ገቢም አንድ ላይ ሲሰላ 26 ትሪሊዮን ዶላር ይደርሳል። ይህም ማለት ደግሞ ከዓለም ምጣኔ ሃብት 26 በመቶውን የሚይዝ ነው።
ሆኖም በፖለቲካ እና ምጣኔ ሃብታዊ ትስስር ላይ ጥናት እንደሚያካሂደው የአሜሪካ ተቋም የአትላንቲክ ምክር ቤት ከሆነ፣ የብሪክስ አገራት በተባበሩት መንግሥታት ዋና የገንዘብ ተቋም (አይኤምኤፍ) ያላቸው ድምጽ 15 በመቶ ብቻ ነው።
የብሪክስ ዋና ዓላማ ምንድን ነው?
ብሪክስ የተመሰረተው እንደ አይኤምኤፍ እና ዓለም ባንክ ያሉ ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማትን አሰራር የማሻሻያ መንገዶችን ለመፈለግ፣ እንዲሁም ለታዳጊ አገራት ምጣኔ ሃብት ድምጽ እና ውክልና ለመፍጠር ነው።
በ2014 (እአአ) የብሪክስ አገራት በማደግ ላይ ባሉ አገራት ውስጥ ለመሠረተ ልማት እና ለዘላቂ ልማት ፕሮጀክቶች ሃብት የማሰባሰብ ዓላማ ያለውን ‘ኒው ዲቨሎፕመንት ባንክ’ (ኤንዲቢ) በ250 ቢሊዮን ዶላር አቋቁመዋል።
የብሪክስ አባል ያልሆኑት ግብፅ እና የተባበሩት አረብ ኤምሬትስም ባንኩን ተቀላቅለዋል።
መቀመጫውን ሻንግሃይ ቻይና ያደረገው ይህ ባንክ ትኩረቱን በንጹህ ኃይል፣ በትራንስፖርት መሠረተ ልማት፣ በውሃ እና ንጽህና፣ ዲጂታል መሠረተ ልማት፣ የአካባቢ ጥበቃ እና ማኅበራዊ መሠረተ ልማት ላይ አድርጓል።
አገራቱ በዓለም የፋይናንስ ጉዳዮች ላይ ትልቅ ሚና ይኖረዋል የተባለለትን ኤንዲቢን ይፋ ማድረጋቸው እንደ መጀመሪያው ስኬታቸው ታይቷል።
ባንኩ በአባል አገራቱ ውስጥ ያለውን ከፍተኛ የመሠረተ ልማት የገንዘብ አቅርቦት ክፍተት ለመፍታት ያለመ ነው።
ኤንዲቢ እስከ 2017 (እአአ) ድረስ በ11 ፕሮጀክቶች ላይ መዋዕለ ነዋይ አፍስሷል። እስከ 2016 ብቻ ባለው ጊዜም 1.5 ቢሊዮን ዶላር ማበደር ችሏል።
የብሪክስ አባላት የጋራ ገንዘብ ይፈጥራሉ?
በቅርቡ በብራዚል እና በሩሲያ የሚገኙ እውቅ ፖለቲከኞች በዓለም አቀፍ ንግድ እና ፋይናንስ ላይ የአሜሪካ ዶላር ያለውን የበላይነት ለመገዳደር ለብሪክስ ቡድን አንድ የመገበያያ ገንዘብ እንዲፈጠር ምክረ ሃሳብ አቅርበዋል።
ሆኖም በብሪክስ እና በእስያ የደቡብ አፍሪካው አምባሳደር የሆኑት አኒል ሶክላል ከነገ [ማክሰኞ] ጀምሮ በደቡብ አፍሪካ፣ ጆሃንስበርግ በሚካሄደው የቡድኑ ጉባኤ ላይ ይህ አጀንዳ አለመሆኑን ተናግረዋል።
መጀመሪያ ላይ የ‘ብሪክስ’ን ሃሳብ ያመነጩት የጎልድማን ሳክስ የምጣኔ ሃብት ባለሙያው ጂም ኦ’ኔል አንድ የመገበያያ ገንዘብ የመፍጠሩን ሃሳብ “አስቂኝ” ሲሉ ለዩናይትድ ኪንግደሙ ፋይናንሻል ታይምስ ጋዜጣ ተናግረዋል።
የብሪክስ አባላት አንድነት እና ልዩነት?
በደብሊን ትሪኒቲ ኮሌጅ የዲቨሎፕመንት ጂኦግራፈር የሆኑት ፕሮፌሰር ፓድሬግ ካርሞዲይ እያንዳንዳቸው የብሪክስ አገራት በሚገኙበት ቀጠና ወሳኝ አገራት ናቸው ይላሉ።
ይሁን እንጂ ከእነዚህ ሁሉ ቻይና ዋነኛዋ ተፅዕኖ ፈጣሪ አገር ሆናለች ይላሉ። በብሪክስ አማካኝነት አሁን ላይ ያለውን የዓለም ኢኮኖሚ ሥርዓት እንዲወገድ አሊያም እንዲሻሻል በመጠየቅ በደቡባዊው የዓለም ክፍል የራሷ ድምጽ ከፍ ብሎ እንዲሰማ እየሠራች ነው ብለዋል።
ሆኖም ሕንድ በእስያ ፓስፊክ ቀጠና የቻይና ተቀናቃኝ ናት። ለረጅም ጊዜ የቆየ የድንበር ይገባኛል ውዝግብም አለባት፣ እንዲሁም በቀጠናው ያላትን ተፅዕኖ ለማስፋፋት ከአሜሪካ እና ከሌሎች አገራት ጋር እየሠራች ትገኛለች።
ከዚህም በተጨማሪ የብሪክስ አገራት ከምዕራባውያን አገራት ጋር ሊኖራቸው ስለሚገባ ግንኙነትም ልዩነት አላቸው።
ተቀማጭነቱን ለንደን ባደረገው የጥናት ተቋም ቻተም ሐውስ ውስጥ የግሎባል ኢኮኖሚ እና የፋይናንስ ፕሮግራም ዳይሬክተር የሆኑት ክሪኦን በትለር፣ ሩሲያ ዩክሬንን በመውረሯ ምክንያት የሚገጥማትን ማዕቀብ ለማስወገድ ብሪክስ ይረዳኛል በሚል ከምዕራባውያኑ ጋር እያካሄደች ያለው ትግል አካል አድርጋ ነው የምትመለከተው ይላሉ።
ምዕራባውያኑ አገራት የሩሲያ ነዳጅ ወደ አገራቸው እንዳይገባ ማዕቀብ መጣላቸውን ተከትሎም ሕንድ እና ቻይና ዋነኛ የነዳጅ ሸማች ደንበኞቿ ሆነዋል።
ከዚህም ባሻገር ሩሲያ የካቲት ወር ላይ ከቻይና እና ደቡብ አፍሪካ ጋር የጋራ ወታደራዊ ልምምድ አድርጋለች።
ይሁን እንጂ ሌሎች የብሪክስ አባል አገራት ቡድኑ ግልጽ የሆነ ፀረ ምዕራባውያን ስብስብ እንዲሆን አይፈልጉም።
በትለር እንደሚሉት ደቡብ አፍሪካ፣ ብራዚል እና ሕንድ የተከፋፈለ ዓለም አይፈልጉም፤ ምክንያቱም ምዕራባውያኑን መቃወም ለፀጥታ እና ለእድገታቸው ጎጂ ስለሚሆን።
ብሪክስን መቀላቀል የሚፈልጉት አገራት?
በብሪክስ እና በእስያ የደቡብ አፍሪካ አምባሳደር የሆኑት አኒል ሶክላል እንደተናገሩት እስካሁን 22 አገራት በይፋ የቡድኑ አባል ለመሆን ጥያቄ ያቀረቡ ሲሆን፣ ተመሳሳይ ቁጥር ያላቸው አገራት ስብስቡን ለመቀላቀል ያላቸውን ፍላጎት ገልጸዋል።
እነዚህም መካከል ኢራን፣ አርጀንቲና፣ ኩባ፣ ካዛክስታን፣ ኢትዮጵያ፣ ሳዑዲ አረቢያ፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ እና ቬንዙዌላ ይገኙበታል።
ፕሮፌሰር ካርሞዲይ እንደሚሉት የኃይል ሚዛኑ ከምዕራብ ዓለም እየራቀ ነው የሚል እሳቤ ስላለ በርካታ በማደግ ላይ ያሉ አገራት እንደ ብሪክስ ኃይላቸውን እያሳደጉ ያሉ አገራትን ይፈልጋሉ። ነገር ግን ብሪክስ ብቸኛ ስብስብ ነው።
ብሪክስ አዲስ አባላትን መቀበሉ ያለውን ተፅዕኖ ያዳክመው ይሆን? ለሚለው ጥያቄም “ጥቂት አገራት ይገባሉ። የሚገቡትም እንደ ኢራን ካሉ ውስብስብ አገራት ይልቅ፣ እንደ አርጀንቲና ያሉ አገራት ናቸው” ሲሉ ግምታቸውን ያስቀምጣሉ።
በብሪክስ ጉባኤ የመወያያ አጀንዳዎች?
የ2023 የብሪክስ መሪዎች ጉባኤ ዛሬ ማክሰኞ የሚጀመር ሲሆን፣ ከነሐሴ 16 አስከ 18/2015 ዓ.ም. ለተከታታይ ቀናት ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ይካሄዳል።
በጉባኤው ላይም ማን ብሪክስን ሊቀላቀል እንደሚችል በሚወስነው ደንብ ላይ ተነጋግረው ውሳኔ ማሳለፍ የመሪዎቹ ዋናው አጀንዳቸው ይሆናል።
ሌሎች አጀንዳዎች ላይም እንደሚነጋገሩ የሚጠበቅ ሲሆን፣ ከእነዚህ መካከል የአየር ጠባይ ለውጥን መታገል፣ በማደግ ላይ ባሉ አገራት የንግድ፣ የኢንቨስትመንት ዕድሎች እና የፈጠራ ሥራን ማስፋፋትን የመሳሰሉ ርዕሰ ጉዳዮች ይነሳሉ።
እንዲሁም በማደግ ላይ ላሉ አገራት ድምጽ ሊሆን የሚችል የዓለም አስተዳዳር ሥርዓት ማሻሻያ ላይ ይነጋገራሉም ተብሏል።
ደቡብ አፍሪካ ለጉባኤው ከአፍሪካ፣ ከላቲን አሜሪካ፣ ከእስያ እና ከካረቢያን ከ60 በላይ የሚሆኑ አገራት መሪዎችን ጋብዛለች።
ሆኖም የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በብሪክስ ስብሰባ ላይ ለመታደም ወደ ደቡብ አፍሪካ አያቀኑም።
ምክንያቱም ዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት (አይሲሲ) በፕሬዝዳንት ቭላዲሚር ፑቲን ላይ የእስር ማዘዣ በማውጣቱ ነው።
አይሲሲ ይህንን ማዘዣ ያወጣው ሕፃናትን ከዩክሬን ማፈናቀልን ጨምሮ በጦር ወንጀሎች ተጠያቂ በመሆናቸው እንደሆነ ተገልጿል። ፑቲን ግን ይህን አልፈፀምኩም ብለዋል።
ደቡብ አፍሪካ የዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት አንዷ ፈራሚ በመሆኗም አይሲሲ የእስር ትዕዛዝ ያወጣባቸው ፑቲን የደቡብ አፍሪካን መሬት ከረገጡ በቁጥጥር ሥር የማዋል ግዴታ አለባት።
ፕሬዝዳንት ፑቲን ጉባኤውን በበይነ መረብ እንደሚሳተፉ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሰርጌይ ላቭሮቭ በአካል ተገኝተው ጉባኤውን እንደሚካፈሉ ተናግረዋል።