የዓለም ባንክ ፕሬዝደንት “ቻይና ለአፍሪካ የምትሰጠው ብድር አሳስቦኛል” አሉ

የዓለም ባንክ ፕሬዝደንት ቻይና ለአፍሪካ ሃገራት የምትሰጠው ብድር እያሳሰባቸው እንደሆነ ለቢቢሲ ተናገሩ።

ዴቪድ ማልፓስ እንደሚሉት ቻይና ብድር ስትሰጥ የምታስቀምጠው ቅደመ ሁኔታ “ግልፅ” መሆን አለበት።

እንደ ጋና እና ዛምቢያ ያሉ ሃገራት ለቻይና ብድራቸውን መክፈል አቅቷቸው እየታገሉ መሆኑ ይፋ መሆኑ ወቅት ነው የዓለም ባንክ ፕሬዝዳንት ይህን ያሉት።

ቻይና ግን ብድር የምትሰጠው ዓለም አቀፍ ሕግን ተከትላ መሆኑን ተገልጻለች።

እያደጉ ያሉ ሃገራት ከሃገራትና ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ተበድረው መሠረተ ልማትና ምጣኔ ሃብታቸውን ያጠናክራሉ።

ነገር ግን ባለፈው ዓመት አሜሪካና ሌሎች ምጣኔ ሃብታቸው ያደገ ሃገራት የወለድ መጠናቸውን ከፍ ማድረጋቸው ብድር የወሰዱ ሃገር መክፈል እንዲቸገሩ አድርጓቸዋል።

አብዛኛዎቹ ሃገራት ብድር ሲወስዱ በዩኤስ ዶላርና ዩሮ በመሆኑ ይህ የወለድ መጠን መጨመር ጫና አሳድሮባቸዋል።

አልፎም እያደጉ ያሉ ሃገራት የመገበያያ ገንዘባቸው እየተዳከመ ሲመጣ የወሰዱትን ብድር የመክፈል አቅማቸው ይዳከማል።

“ይህ ማለት የምጣኔ ሃብት እድገቱ እየተጓተተ ነው ማለት ነው” ይላሉ የባንኩ ፕሬዝደንት ማልፓስ።

የአሜሪካዋ ምክትል ፕሬዝደንት ከማላ ሃሪስ በቅርቡ ሶስት የአፍሪካ ሃገራትን ጎብኝተው ተመልሰዋል። ለታንዛኒያና ለጋና የገንዘብ እርዳታ ለማድረግም ቃል ገብተዋል።

አሜሪካና ቻይና በተፈጥሮ ሃብት በታደለችው አፍሪካ ያላቸውን ጫና ፈጣሪነት ለማስጠበቅ ፉክክር ውስጥ ከገቡ ሰንበትበት ብለዋል።

ከማላ ሃሪስ በጋና በነበራቸው ቆይታ “አሜሪካ ለአፍሪካ ምን አደርጋለሁ ሳይሆን፤ ከአፍሪካ ጋር ምን አደርጋለሁ ነው የምትለው” ብለዋል።

የዓለም ባንኩ ፕሬዝደንት ሁለቱ ኃያላን ሃገራት እያደረጉት ያለው ፉክክር “ምናልባት እያደጉ ላሉ ሃገራት ምጣኔ ሃብት ጠቃሚ ሊሆን ይችላል” ባይ ናቸው።

“እኔ የማበረታታው የሚፈርሙት ኮንትራክት ግልፅ እንዲሆን ነው። ኮንትራክት ተፈራርመው ለማንም እንዳታሳዩ ማለት ተገቢ አይደለም።”

አክለው አንዳንድ የአፍሪካ ሃገራት ፕሬዝዳንቶች ብድር መክፈል ካልቻልን በሚል የሕዝብ ንብረት እያስያዙ መሆኑ አደጋ ነው ብለዋል።

ኪዬል ኢንስቲትዩት የተሰኘ ተቋም ያወጣው መረጃ እንደሚያሳየው ከ2016-2021 ባለው ጊዜ ለ22 ሃገራት 185 ቢሊየን ዶላር አበድራለች።

ቻይና በብድሯ አማካይነት ሌሎች ሃገራትን እየበደለች ነው በሚለው ክስ አትስማማም።

ተሰናባቹ የዓለም ባንክ ፕሬዝደንት በዩክሬን ጦርነት ምክንያት የምግብ ዋጋ መናር፣ የማዳበሪያና ኢነርጂ ዋጋ መጨመር ለደሃ ሃገራት በጣም አሳሳቢ መሆኑንም ገልጠዋል።