በርካታ የትራምፕ ዕጩ የካቢኔ አባላት የቦምብ ጥቃት ማስፈራሪያ ደረሰባቸው

ተመራጩ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ያጯቸው በርካታ የካቢኔ አባላት እና የዋይት ሐውስ ተሿሚዎች የቦምብ ጥቃት ማስፈራሪያ ደረሳቸው።

ኤፍቢአይ የተባለው የፌዴራል ወንጀል ምርመራ ቢሮ “በርካታ የቦምብ ጥቃት ማስፈራሪዎች” መሰንዘራቸውን ገልጿል።

ቢሮው እንዳለው በርካታ ሐሰተኛ የስልክ ጥሪዎች የተደረጉት ፖሊስ ዒላማ ይሆናሉ ወደተባሉ ግለሰቦች መኖሪያ ቤት እንዲሄድ በሚል ነው።

ዕጩ የመከላከያ፣ የቤቶች፣ የግብርና ሚኒስትሮች ዛቻ ከደረሰባቸው ሰዎች መካከል ሲሆኑ፣ በተባበሩት መንግሥት የአሜሪካ ተወካይ ይሆናሉ የተባሉትም ግለሰብ እንዲሁ ዒላማ ሆነዋል።

አዳዲሶቹ የትራምፕ የካቢኔ አባላት ማስፈራሪያ የደረሳቸው ማክሰኞ ምሽት እና ረቡዕ መሆኑን ያሳወቀው ፖሊስ ምርመራ መክፈቱን ገልጿል።

የትራምፕ የሽግግር ሂደት ቃል አቀባይ የሆኑት ካሮላይን ሌያቪት የትራምፕ ተሿሚዎች “በጣም አስፈሪ እና አሜሪካዊ ባልሆነ ሁኔታ ነው ከነቤተሰቦቻቸው ዛቻ የደረሰባቸው” ብለዋል።

የተመራጮቹን ደኅንነት ለመጠበቅ “ሕግ አስከባሪዎች በፍጥነት ሁኔታውን ተቆጣጥረውታል” ሲሉም አክለዋል።

ቃለ አቀባይዋ ጨምረው “ምንም ዓይነት ማስፈራሪያ እና አመፅ እንደማይገታን ፕሬዝደንት ትራምፕ ጥሩ ማሳያ ናቸው” ብለዋል።

ኤፍቢአይም ሆነ የትራምፕ የሽግግር ሂደት ቡድን ማስፈራሪያ የደረሰባቸውን ሰዎች ስም ይፋ አላደረጉም።

ትራምፕ በተባበሩት መንግሥታት የአሜሪካ አምባሳደር እንዲሆኑ የመረጧቸው ኤሊስ ስቴፋኒክ ዛቻው እንደደረሳቸው ያሳወቁ የመጀመሪያዋ ግለሰብ ሲሆኑ፣ እሳቸው እና ቤተሰቦቻቸው የቦምብ ጥቃት ማስፈራሪያ እንደተሰነዘረባቸው ተናግረዋል።

ዕጩው የመከላከያ ሚኒስትር ፒተር ሄግሴዝ በተመሳሳይ የግድያ ዛቻ እንደደረሰባቸው አስታውቀዋል።

በቀድሞው ትዊተር በአሁኑ ኤክስ ማኅበራዊ ሚድያ ገፃቸው ይህን ያሳወቁት ሄግሴዝ ረቡዕ ጠዋት ዛቻ እንደደረሰባቸው ገልፀው “ማንኛውም ማስፈራሪያ ትራምፕ የጣሉብኝን አደራ ከማስፈፀም አያግደኝም” ብለዋል።

በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ሁለት ጊዜ የግድያ ሙከራ የተቃጣባቸው ፕሬዝደንት ትራምፕ የቦምብ ጥቃት ማስፈራሪያ ከደረሳቸው ሰዎች መካከል አለመሆናቸውን የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን አስታውቀዋል።

መገናኝ ብዙኃን እንደሚሉት የቦምብ ጥቃት ማስፈራሪያ የደረሳቸው ዕጩ ተሿሚዎች ሴክሬት ሰርቪስ በተባለው የደኅንነት መሥሪያ ቤት ጥበቃ እየተደረገላቸው አይደለም።

የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሚኒስትር እንዲሆኑ በትራምፕ የተመረጡት ሊ ዜልዲን ደግሞ “ለፍልስጤም ድጋፍ ያለው የሚመለስል” መልዕክት ያለበት የቦምብ ጥቃት ዛቻ ደርሶብኛል ብለዋል።

አዲሱን የትራምፕ አስተዳደር ለማገልገል ከተሾሙ ሰዎች መካከል በርካቶቹ ዛቻ እንደደረሰባቸው ኤፍቢአይ አስታውቆ ከሌሎች የፀጥታ መሥሪያ ቤቶች ጋር በመቀናጀት ጥበቃውን ማጠናከሩን ገልጿል።

ትራምፕ ላይ የቀረበውን የወንጀል ክስ የሚመለከቱ ሰዎች ላይ በቅርቡ ተመሳሳይ የቦምብ ጥቃት ማስፈራሪያ እንደደረሰባቸው ይታወሳል።

ባለፈው ዓመት በገና በዓል ወቅት የአሜሪካ ፖለቲከኞች በተመሳሳይ የቦምብ ጥቃት ማስፈራሪያ ደርሶባቸውን እንደነበር አይዘነጋም።