ዶናልድ ትራምፕ ከፕሬዝዳንት ፑቲን ጋር ከተወያዩ በኋላ ከዩክሬን ጋር ንግግር እንደሚጀመር ተናገሩ

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በትናንትናው ዕለት ከቭላድሚር ፑቲን ጋር በስልክ "ረዥም እና ውጤታማ" ውይይት ማድረጋቸውን ገልጸው መሪዎቹ በዩክሬን ያለውን ጦርነት ለማቆም ድርድር ለመጀመር መስማማታቸውን አስታወቁ።

ትረምፕ ትሩዝ በተሰኘው ማኅበራዊ ድረገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሑፍ ከሩሲያው ፕሬዝዳንት ጋር "ቡድኖቻችን በአፋጣኝ ድርድር እንዲጀምሩ ተስማምተናል" እንዲሁም አንዳችን የሌላኛውን አገር እንድንጎበኝ ግብዣ አቅርበናል ብለዋል።

ከዚህ በኋላም የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘለንስኪ ከትራምፕ ጋር ስለ "ዘላቂና አስተማማኝ ሰላም" መነጋገራቸውን ተናግረዋል።

ከተፋላሚዎቹ ወገኖች ጋር የስልክ ውይይት የተደረገው ትራምፕ እና የመከላከያ ሚኒስትራቸው ዩክሬን ኔቶን ልትቀላቀል አትችልም በማለት ከተናገሩ በኋላ ሲሆን ይህም ኪየቭን በብርቱ የሚያስከፋ ነው።

ዜለንስኪ አርብ ዕለት በሙኒክ በሚካሄደው ስብሰባ ላይ ምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩን ማርኮ ሩቢዮ እንደሚያገኟቸው ተናግረዋል ።

ትራምፕ ትሩዝ በተሰኘው ማኅበራዊ ድረገጻቸው ላይ "ይህን አስቀያሚ፤ ግዙፍ እና ሙሉ በሙሉ አላስፈላጊ የሆነ፣ ሞት እና ውድመት የሞላበት ጦርነት ለማቆም ጊዜው አሁን ነው። እግዚአብሔር የሩሲያ እና የዩክሬን ሕዝቦችን ይባርክ!" ብለዋል።

ዶናልድ ትራምፕ በማኅበራዊ ድረገጻቸው ላይ ከፑቲን ጋር ፊት ለፊት ስለሚገናኙበት ቀን በይፋ ያሉት ነገር ባይኖርም፣ በኋላ ግን በዋይት ሀውስ ለጋዜጠኞች "ሳዑዲ አረቢያ ውስጥ እንገናኛለን" ሲሉ አስታውቀዋል።

የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ፤ ከፑቲን አብሮ ለመስራት 'ጊዜው አሁን ነው' የሚለውን የትራምፕን ሃሳብ እንደሚደግፉ ተናግረዋል።

በፑቲን እና በትራምፕ መካከል የተደረገው የስልክ ውይይት ለአንድ ሰዓት ተኩል የሚጠጋ ጊዜ የፈጀ ሲሆን፣ የሩሲያው ፕሬዝዳንት ሞስኮን እንዲጎበኙ ግብዣ ማቅረባቸውን ቃል አቀባዩ ገልጸዋል።

ትራምፕ ዩክሬን እኤአ ከ2014 በፊት ወደነበራት ድንበር ትመለሳለች ተብሎ የማይታሰብ መሆኑን በዋይት ሀውስ ለጋዜጠኞች ተናግረው ነገር ግን ከቢቢሲ ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ "የተወሰደው መሬት የተወሰነው ይመለሳል" ብለዋል።

ባለፈው ሐሙስ የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር ፒት ሄግሰት፤ ለኔቶ የመሪዎች ጉባኤ ዩክሬን ኔቶን ልትቀላቀል የምትችልበት እድል እንደሌለ የተናገሩትን እንደሚስማሙበት ፕሬዝዳንት ትራምፕ አስታውቀዋል።

ትራምፕ "ይህ ምናልባት እውነት ይመስለኛል።"

የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት ዩክሬን ከሩሲያ ጋር የምታደርገውን ጦርነት መደገፍ ሊቀጥል እንደሚችል የአገሪቱ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አንጌላ ቴይነር ለአይቲቪ ተናግረዋል።

የቢቢሲው ጄምስ ዋተር ሃውስ በዩክሬን ዋና ከተማ ያለውን ስሜት ሲገመግም የሄግሰት ንግግር ለኪየቭ አስደንጋጭ እንደሚሆን ተናግሯል።

አዲሱ የአሜሪካ አስተዳደር ከቀድሞው ጋር ሲነጻጸር ለዩክሬን ያለው ርኅራኄ አነስተኛ መሆኑ ቢታወቅም፣ የቢቢሲ ዘጋቢ አክሎም፣ የሄግሥት እያንዳንዱ ንግግር ሞስኮን ማስደሰቱ አይቀርም ሲል ያስቀምጣል።

አክሎም የኔቶ አባልነት ውድቅ ከተደረገ፣ ዩክሬን ማሸነፍ አትችልም ከሚለው አመለካከት ጋር ተደምሮ ወደፊት የሁለቱ አገራት ጦር ተፋጥጠው በሚገኙበት የድንበር አካባቢ እንዴት ቁጥጥር ማድረግ እንደሚቻል ጥያቄ ውስጥ ገብቷል ሲል ትንታኔውን ሰጥቷል።

ይህን ሁሉ ከግምት ውስጥ በማስገባት ሩሲያ በዩክሬን ላይ ለ11 ዓመታት የፈፀመችውን ወታደራዊ ትንኮሳን በተጨባጭ የመለሰ ነው ሲል የቢቢሲ ዘጋቢ ያብራራል።

ዘለንስኪ ደጋግመው "ከዩክሬን ውጭ በዩክሬን ላይ ምንም አይነት ንግግር ሊኖር አይችልም" ሲሉ ቢሟገቱም፤ የትራምፕ እና ፑቲን የስልክ ውይይት ግን እርሳቸው በሌሉበት የተከናወነ ነው።

ዜለንስኪ ከትራምፕ ጋር ያደረጉት የስልክ ውይይት በተለያዩ ጉዳዮች ላይ "ትርጉም እና ጥልቀት ያለው ውይይት" እንደነበር ተናግረው፤ ኪየቭን በመጎብኘት ላይ የሚገኙትን የአሜሪካ የገንዘብ ሚኒስትር ስኮት ቤሴንንም ማግኘታቸውን ተናግረዋል።

"ከዩክሬን በላይ ማንም ሰላምን የሚፈልግ የለም። ከአሜሪካ ጋር በመሆን የሩስያን ጥቃት ለማስቆም እና ዘላቂ አስተማማኝ ሰላም ለማረጋገጥ ቀጣይ እርምጃዎቻችንን እየቀረፅን ነው" ሲሉ ዘሌንስኪ ተናግረዋል።

የዩክሬኑ መሪ አክለውም "ተጨማሪ ግንኙነቶችን ለማድረግ እና መጪ ስብሰባዎችን ለማዘጋጀት ተስማምተናል" ብለዋል።

በአሜሪካ እና በዩክሬን መሪዎች መካከል የተደረገው የስልክ ውይይት ለአንድ ሰዓት ያህል የቆየ እንደነበር ኤኤፍፒ ዘግቧል።

ዘሌንስኪ ማክሰኞ ከታተመው ዘ ጋርዲያን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ሁለቱ አገራት የያዝዋቸውን ግዛቶች እንዲቀያየሩ የሰላም ሰምምነቱ አካል ሆኖ መቅረቡን ተናግረዋል።

የፑቲክ ቃል አቀባይ ፔስኮቭ ግን "ፈጽሞ የማይቻል" ሲሉ ሀሳቡን ውድቅ አድርገዋል።

"ሩሲያ ግዛቶቿን ለመቀያየር ንግግር አላደረገችም፤ አታደርግምም። የዩክሬን ኃይሎች ከእነዚህ አካባቢዎች እንዲወጡ ይደረጋል። ያልተደመሰሱት በሙሉ እንዲቀጡ ይደረጋል" ብለዋል።

ዜሌንስኪ በበኩላቸው የአውሮፓ አገራት ብቻ ሳይሆኑ አሜሪካም ለአገራቸው የማንኛውም የደህንነት ማዕቀፍ አካል መሆን እንዳለባት አጥብቀው ተናግረዋል ።

"አሜሪካ የሌለችበት የደህንነት ዋስትና እውነተኛ የደህንነት ዋስትና አይደለም።"

እ.ኤ.አ. በ 2014 የሩሲያ ደጋፊ የነበረው የዩክሬን ፕሬዝዳነት ከስልጣን መውረዱን ተከትሎ ሞስኮ ክሬሚያን የወሰደች ሲሆን፣ በምስራቅ ዩክሬን ደግሞ የሩሲያ ደጋፊ የሆኑ ተገንጣዮችን ትደግፋለች።

የዛሬ ሦስት ዓመት ግጭቱ ወደ ሁሉን አቀፍ ጦርነት የገባው ሩሲያ ዩክሬንን መውረሯን ተከትሎ ነው።

ሞስኮ ኪየቭን ለመቆጣጠር ያደረገችው ሙከራ ቢከሽፍም የሩስያ ጦር በምስራቅ እና በደቡብ ያለውን የዩክሬን አንድ አምስተኛ ግዛት የተቆጣጠረ ሲሆን፣ በመላ አገሪቱ የአየር ድብደባ ፈጽሟል።

በጦርነቱ ጉዳት የደረሰባቸው እና የሞቱ ሰዎች ቁጥር በሩሲያ እና በዩክሬን መንግሥታት በይፋ ባይገለጽም፣ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሮች ሙት እና ቁስለኛ መሆናቸውበሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዩክሬናውያን ደግሞ መሰደዳቸው ይገመታል።