ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሁለተኛው የትራምፕ የሥልጣን ዘመን ለዓለማችን ምን ይዞ ይመጣል?
ባለፈው ኅዳር በተካሄደው ምርጫ ያሸነፉት ዶናልድ ትራምፕ ሰኞ ጥር 12/2017 ቃለ መሐላ ፈጽመው ሁለተኛውን የፕሬዝደንትነት ዘመናቸውን በይፋ ጀምረዋል።
ለሁለተኛ ጊዜ ወደ ዋይት ሐውስ የሚመጡት ትራምፕ የአሜሪካን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ እንደሚቀይሩት እና "አሜሪካ ፈረስት" [ከሁሉ በፊት አሜሪካ] የተሰኘውን አጀንዳቸውን ተግባራዊ እንደሚያደርጉት ይጠበቃል።
ይህ ፖሊሲ ከአሜሪካ ውጭ ያሉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ሊነካ ይችላል።
ሁለተኛው የትራምፕ ዘመን ሥልጣን ለዓለማችን ምን ይዞ ይመጣል?
ዩክሬን
ትራምፕ በምርጫ ቅስቀሳቸው ወቅት በተደጋጋሚ በሩሲያ እና በዩክሬን መካከል ያለውን ጦርነት "በአንድ ቀን" እንደሚያስቆሙት ቢናገሩም ዝርዝር መረጃ አልሰጡም።
ከሩሲያ ወረራ ጀምሮ አሜሪካ ለዩክሬን በወታደራዊ እርዳታ መልክ የምትሰጠው በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር ተገቢ አይደለም ሲሉ ተደምጠዋል።
ይህ አስተያየቶች ለዩክሬናውያን እና ለደጋፊዎቻቸው ስጋት ሆኗል። ዩክሬን ድንበሯን አሳልፋ ሰጥታ ጦርነቱን እንድትቋጭ ልትገደድ ትችላለች የሚል መላ ምትም አለ።
በዩክሬን እና በሩሲያ የትራምፕ ልዩ መልዕክተኛ ሆነው የተሰየሙት ኪዝ ኬሎግ ባለፈው ጥር ፎክስ ኒውስ ለተሰኘው የቴሌቪዥን ጣቢያ እንደተናገሩት ዩክሬን ከአሜሪካ እርዳታ የሚደርሳት ከሞስኮ ጋር የሰላም ድርድር ለማድረግ ከተቀመጠች ብቻ መሆን አለበት።
ትራምፕ ከሩሲያው ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር ለመገናኘነት ማሰባቸውን እና ቡድናቸው "ሁኔታዎችን እያመቻቸ" እንደሆነም ተናግረዋል።
ኔቶ
አሜሪካ፣ ዩናይትድ ኪንግደም፣ ጀርመን እና ፈረንሳይን ጨምሮ 32 አባል ሀገራት ያሉት የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) ጉዳይ ሌላኛው መነጋገሪያ ነው።
ትራምፕ በመጀመሪያው የሥልጣን ዘመናቸው ሌሎች አባል ሀገራት የሚጠበቅባቸውን ከጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት 2 በመቶ ድርሻ ማዋጣት ካልቻሉ አሜሪካ ኔቶን ለቃ እንደምትወጣ አስጠንቅቀው ነበር። አክለውም ድርሻውን የማይወጣ አባል ሀገር ቢወረር አሜሪካ አትከላከልም የሚል ሐሳብ ሰንዝረው ነበረ።
በጥር ወር መባቻ በሰጡት አስተያየት ደግሞ የኔቶ አባል ሀገራት ድርሻቸውን በማሳደግ ከጠቅላላ የሀገር ውስጥ ገቢያቸው 5 በመቶን እንዲያዋጡ ጠይቀዋል።
የትራምፕ የምርጫ ቅስቀሳ ድረ-ገፅ እንደሚለው የፕሬዝደንቱ ፍላጎት የኔቶን ዓላማ እና ተልዕኮ "ከመሠረቱ መቀየር" ነው።
ትራምፕ ከኔቶ አባልነት አሜሪካን ያስወጧት ይሆን? የሚለው ጥያቄ ገና ምላሽ አላገኘም። ነገር ግን ተንታኞች እንደሚሉት ትራምፕ ከኔቶ ሳይወጡ የቃል-ኪዳን ድርጅቱን ጥንካሬ ሊገዳደሩት ይችላሉ። ለምሳሌ በአውሮፓ ያሉ የአሜሪካ ወታደሮችን ቁጥር ሊቀንሱት ይችላሉ።
መካከለኛው ምሥራቅ
ትራምፕ በሐማስ እና በእስራኤል መካከል የተኩስ አቁም ስምምነት ከተደረሰ በኋላ ነው ወደ ሥልጣን የሚመጡት።
የትራምፕ አማካሪዎች ከተሰናባቹ ፕሬዝደንት ጆ ባይደን ጋር እንዲሁም ከኳታር እና ግብፅ ጋር በመተባበር ነው ድርድሩን ሲያካሂዱ የነበረው። ባይደንም ሆኑ ትራምፕ ለተኩስ አቁም ስምምነቱ ምስጋና እንደሚገባቸው ይናገራሉ።
ነገር ግን የተኩስ አቁም ስምምነቱ ተግባራዊነት በተለይ የመጨረሻው ክፍል ገና ጥያቄ ውስጥ ነው።
ትራምፕ በመጀመሪያው የፕሬዝደንትነት ዘመናቸው ለእስራኤል የሚያደሉ ፖሊሲዎችን ተግባራዊ አድርገዋል። ኢየሩሳሌም የእስራኤል ዋና ከተማ ናት በማለት የአገራቸውን ኤምባሲ ከቴል አቪቭ ወደ ኢየሩሳሌም እንዲዘዋወር ማድረጋቸው ይታወሳል።
አልፎም ከኢራን ጋር ከተገባው የኒውክሌር ስምምነት አሜሪካን በማግለል ኢራን ላይ ተጨማሪ ማዕቀብ ከመጣል ባለፈ የቴህራን ጠንካራ ክንድ ናቸው የሚባሉት ጄኔራል ቃሲም ሱሌማኒ የተገደሉት በትራምፕ ትዕዛዝ ነው።
ተቺዎች የትራምፕ ፖሊሲ መካከለኛው ምሥራቅን የማያረጋጋ እና ፍልስጤማውያንን የሚያገል ነው ይላሉ። አብርሀም አኮርድስ የተሰኘው በእስራኤል እና በዩናይትድ አረብ ኤሜሬትስ፣ ባህሬን፣ ሱዳን እና ሞሮኮ መካከል ሰላማዊ ግንኙነት እንዲፈጠር ያስቻለውን ስምምነት አስፈፅመዋል።
ነገር ግን ይህ ስምምነት የአረብ ሀገራት አቋም የሆነውን የፍልስጤምን ነፃነት እስራኤል ሳትቀበለው የተፈረመ ነው።
የጋዛ የተኩስ አቁም ስምምነት ይፋ ከሆነ በኋላ ትራምፕ በቀጣናው "ሰላምን በጥንካሬ አሰርፃለሁ" ብለዋል። ይህ በሳዑዲ አረቢያ እና በእስራኤል መካከል ስምምነት ሊኖር እንደሚችል ጠቋሚ ነው።
ቻይና
አሜሪካ ከቻይና ጋር ያላት ግንኙነት በዓለም ደኅንነት እና በንግዱ ዘርፍ ላይ ትልቅ አንደምታ አለው።
ትራምፕ በመጀመሪያው የሥልጣን ዘመናቸው ከቻይና ጋር የመረረ የንግድ ጦርነት ውስጥ ገብተው ነበር። በሁለተኛው ዘመናቸው ከቻይና የሚገቡ ምርቶች ላይ 60 በመቶ የታሪፍ ጭማሪ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አድርገው የመረጧቸው ማርኮ ሩቢዮ እንዲሁም የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪያቸው ማይክ ዋልትዝ በቻይና ላይ ጠንካራ እርምጃ መወሰድ አለበት ብለው የሚያምኑ ናቸው።
የቻይና ጉዳይ ሲነሳ የታይዋን ነገር የሚቀር አይደለም። አሜሪካ ለራስ ገዟ ታይዋን ወታደራዊ እገዛ ማድረጓን ቀጥላለች። ቻይና ታይዋንን ተገንጥላ እንደወጣች ነገር ግን በቤጂንግ አስተዳደር ሥር መሆኗ የማይቀር አካል አድርጋ ነው የምትቆጥራት።
ቻይና ታይዋንን ብትወር አሜሪካ ምን ታደርጋለች የሚለው እስካሁን ግልፅ አይደለም። ነገር ግን ባይደን አሜሪካ ታይዋንን ትከላከላለች የሚል ሐሳብ ሰጥተው ያውቃሉ።
ትራምፕ በምርጫ ቅስቀሳቸው ወቅት የቻይናው ፕሬዝደንት ዢ "ያከብረኛል፤ እብድ መሆኔንም ያውቃል" በማለት አሜሪካ ታይዋንን መከላከል እንደማይጠበቅባት ተናግረዋል።
ቻይና ታይዋንን የምትወር ከሆነ ቤይጂንግን የሚያሽመደምድ ታሪፍ እንደሚጭኑም ጠቁመዋል።
የስደተኞች ጉዳይ
ትራምፕ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሕጋዊ ወረቀት የሌላቸውን ስደተኞች ከአሜሪካ እንደሚያባርሩ በተደጋጋሚ ዝተዋል።
ዋይት ሐውስ በገቡ በመጀመሪያው ቀን "በአሜሪካ ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ ስደተኞችን በገፍ እናባራለን" ብለዋል።
በአሜሪካ 11 ሚሊዮን ገደማ ሕጋዊ ሰነድ የሌላቸው ስደተኞች እንዳሉ ይገመታል። አብዛኞቹ በአሜሪካ ለዓመታት ሥራ እየሠሩ የኖሩ ናቸው። ትራምፕ "በወንጀለኞች" እጀምራለሁ ቢሉም ዝርዝር መረጃ ከመስጠት ተቆጥበዋል።
አክለውም 'በርዝራይት ሲቲዝንሺፕ' የተባለው አሜሪካ በመወለድ የሚገኘውን የዜግነት መብትንም እንደሚያስቀሩት አሳውቀዋል።
በቅስቀሳቸው ወቅት የድንበር ጥበቃውን እንደሚያጠናክሩ እንዲሁም በመጀመሪያው ሥልጣን ዘመናቸው ተግባራዊ መሆን ጀምሮ የነበረውን ከአንዳንድ በተለይ ሙስሊም ከሆኑ ሀገራት የሚመጡ ዜጎች ላይ የሚደረግ እገዳን እንደሚቀጥሉበት አሳውቀዋል።
ነገር ግን የስደት ተንታኞች የትራምፕ ዕቅድ ብዙ ሕጋዊ፣ የሎጂስቲክ፣ የገንዘብ እንዲሁም የፖለቲካ አንድምታ እንዳለው ይናገራሉ።
በተጨማሪም የፓናማ ካናል እና የግሪንላንድ ጉዳይ እንዲሁም የአየር ንብረት ለውጥ በአዲሱ የትራምፕ የአስተዳደር ዘመን ዕጣ ፈንታቸው አሳሳቢ የሆኑ ጉዳዮች ናቸው።