እራኤል ውስጥ በተፈጸመ የየመን የድሮን ጥቃት 20 ሰዎች መጎዳታቸው ተገለጸ

የነፍስ አድን ሠራተኞች፣ ፖሊሶች እና ወታደሮች በአደጋ ስፍራው ተሰብስበው

የፎቶው ባለመብት, Israel Defense Forces

የእስራኤል ጦር ከየመን የተነሳ ድሮን ወደ ሀገሪቱ መተኮሱን ከገለጸ በኋላ በደቡብ እስራኤል በደረሰ ጥቃት ቢያንስ 20 ሰዎች መቁሰላቸውን የነፍስ አድን ሠራተኞች ተናገሩ።

የተተኮሰውን ድሮን ለማክሸፍ ተሞክሮ እንደነበር የገለጸው የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት፤ ነገር ግን በቀይ ባህር ዳርቻ ላይ በምትገኘው የመዝናኛ ከተማ ኢላት ጥቃት ማድረሱን አስታውቋል።

ማገን ዴቪድ አዶም የተባለው የአስቸኳይ ህክምና አገልግሎት ተቋም መረጃ እንደሚያመለክተው፤ ከባድ የአካል ጉዳት የደረሰባቸውን ሁለት ወንዶች ጨምሮ 20 ሰዎች ወደ ሆስፒታል ተወስደዋል።

በኢራን የሚደገፈው ሁቲ ለደረሰው ጥቃት ኃላፊነት እንደሚወስድ አስታውቋል። የታጣቂ ቡድኑ ቃል አቀባይ ያህያ ሳሬያ፤ "ስኬታማ" በሆነ ዘመቻ "የጠላት እስራኤል ዒላማዎች" ላይ ሁለት ድሮኖች መተኮሳቸውን ተናግሯል።

የእስራኤል የቴሌቪዥን ጣቢያ በቀጥታ ስርጭት ባስተላለፈው ምስል፤ የድሮን ጥቃቱን እና ጥቃቱ ከተፈጸመበት ስፍራ ጭስ ሲወጣ አሳይቷል።

ማህበራዊ ሚዲያ ላይ የተለቀቀ እና ቢቢሲ ትክክለኛነቱን ያረጋገጠው ሌላ ምስል ደግሞ አንድ ወደታች እየተምዘገዘገ የነበረ ድሮንን ያሳያል። ቪድዮው ላይ ድሮኑ በህንጻ እስከሚሸፈን ድረስ ወደታች ሲወርድ የሚታይ ሲሆን ከጥቂት ቅጽበታት በኋላ ደግሞ ወፎች ወደ ሰማይ በርረው ተበትነዋል።

የእስራኤል መከላከያ ሰራዊት ባወጣው መግለጫ፤ "የሰራዊቱ ወታደሮች እና ፖሊስ የደረሳቸውን የሰው አልባ አውሮፕላን ጥቃት ሪፖርት ተከትሎ ወደ ኢላት ተሰማርተዋል" ብሏል።

ወታደሮች እና የፖሊስ አባላት ነዋሪዎች አካባቢውን ለቅቀው እንዲወጡ እያገዙ መሆኑን እንዲሁም የተጎዱ ሰዎችን ለማንሳት ሄሊኮፕተር መላኩን አስታውቋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር እስራኤል ካትዝ፤ "በኢላት የሰው አልባ አውሮፕላን ጥቃት የተጎዱ ሰዎች ፈጽሞ እንዲድኑ እመኛለሁ" ብለዋል። "እስራኤልን የጎዳ የትኛውም አካል ሰባት እጥፍ ይጎዳል" ሲሉም ዝተዋል።

ከዚህ አስቀድሞ የእስራኤል ጦር በከተማዋ የማስጠንቀቂያ ደውል ድምጽ እንዲሰማ መደረጉን ገልጾ ነበር። ከተጎጂዎች ቁጥር አንጻር ሲታይ ክስተቱ በሁቲ ከተፈጸሙ ከባድ ጥቃቶች አንዱ ነው።

በሐምሌ 2016 ዓ.ም. ወደ ቴል አቪቭ የተተኮሰ የሁቲ ድሮን የአሜሪካ ኤምባሲ ቅርንጫቅ አካባቢ በሚገኝ አፓርትመንት ላይ ባደረሰው ጥቃት አንድ ሰው ሲገደል 10 ሰዎች ቆስለው ነበር።

ታዋቂ የቱሪስት መዳረሻ የሆነችው ኢላት ከቅርብ ጊዜ የድሮን ጥቃቶች የሚፈጸሙባት ስፍራ ሆናለች። በከተማዋ ሆቴሎች በሚገኙበት ስፍራ ባለፈው ሳምንት ጥቃት መፈጸሙን የሀገሪቱ ባለስልጣናት ተናግረዋል። ጉዳት ስለመድረሱ ግን አልተዘገበም።

ከሳምንታት በፊት ደግሞ በሰሜናዊ ኢላት በሚገኘው ራሞን አየር ማረፊያ ላይ በተፈጸመ የሁቲ ድሮን ጥቃት አንድ ሰው ቆስሏል።

አማጺው የሁቲ ቡድን በተደጋጋሚ ሚሳኤል እና ድሮኖችን ወደ እስራኤል ሲተኩስ ቆይቷል። ቡድኑ እነዚህ ጥቃቶች የሚፈጽመው በጋዛ ጦርነት ውስጥ ለሚገኙ ፍልስጤማውያን አጋርነት ለማሳየት መሆኑን ይገልጻል።

በተጨማሪም ሁቲዎች የገዛ ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ በቀይ ባህር በኩል የሚያልፉ መርከቦችን ሲያጠቁ ቆይተዋል።

እስራኤልን ጠላት አድርጎ የሚቆጥረው ሁቲ፤ ሰንዓ እና ሰሜን ምዕራባዊ የመንን የሚቆጣጠር ቢሆንም እንደ የሀገሪቱ መንግሥት እውቅና አይሰጠውም።

እስራኤል በምላሹ የቀይ ባህር ወደብ የሆነውን ሁዳይዳህን ጨምሮ በሁቲ ቁጥጥር ስር በሚገኙ የየመን ክፍሎች ላይ የቦንብ ድብደባ ፈጽማለች።

እስራኤል በሰንዓ እና አለ ጃዋፍ ግዛት በፈጸመችው ጥቃት 25 በሰዎች መገደላቸውን በሁቲ የሚመራው ጤና ሚኒስቴር ነሐሴ መጨረሻ ላይ አስታውቋል።

ከዚያ አስቀድሞም በቡድኑ የተሾሙት ጠቅላይ ሚኒስትር አህመድ ጋሌብ ናስር አል ራሃዊ በእስራኤል ጥቃት እንደተገደሉ ተገልጿል።