ካናዳ በእያንዳንዱ ሲጋራ ላይ የጤና ማስጠንቀቂያ እንዲጻፍ ሀሳብ አቀረበች

የካናዳ መንግሥት ግለሰቦች በሚጠቀሙት በእያንዳንዱ ሲጋራዎች ላይ የጤና ማስጠንቀቂያ እንዲጻፍበት ሃሳብ አቀረበ።

ይህ በአገሪቷ ያለውን ከፍተኛ ሲጋራ የማጨስ ልማድን ለማስወገድ የተወሰደ በዓለም የመጀመሪያው እርምጃ ይሆናል ተብሏል።

የአዕምሮ ጤና እና የሱስ ሚኒስትር ካሮላይን ቤኔት፣ እርምጃው በርካታ ሰዎችን ተደራሽ ለማድረግ ይረዳል የሚል ተስፋ እንዳላቸው ተናግረዋል።

ሚኒስትሯ አክለውም የዚህ ዋናው ኢላማ በፓኬቱ ላይ የታተሙትን መረጃዎች ችላ በማለት ብዙውን ጊዜ ሲጋራ የሚያጨሱ ወጣቶች ናቸው ብለዋል።

በዚህ በቀረበው ሃሳብ ላይ ለ75 ቀናት የሚቆየውና ከሕዝብ ጋር የሚደረገው ምክክር ቅዳሜ ዕለት ተጀምሯል።

ሚኒስትር ካሮላይን ግለሰቦች በሚጠቀሙት የትንባሆ ውጤቶች ላይ የጤና ማስጠንቀቂያ መጨመር መልዕክቱ በርካታ ሰዎች ጋር እንደደረሰ ለማረጋገጥ ይረዳል” ሲሉ ለጋዜጠኞች አስረድተዋል።

በካናዳ እአአ በ2001 የተዋወቀው እና በሲጋራ ፓኮዎች ላይ ያለው የጤና ማስጠንቀቂያ ምስል መንግሥት ያሰበውን ያህል ውጤት አላስገኘም።

የካናዳ የልብ እና ስትሮክ ፋውንዴሽን አዲሱን ረቂቅ ሃሳብ ተቀብሎታል።

የፋውንዴሽኑ ሥራ አስፈጻሚ ዶግ ሮት ለካናዳ መገናኛ ብዙኃን- ሲቢሲ ፣ “ካናዳ አሁን ለሲጋራ በዓለም ላይ በጣም ጠንካራ የሆነ የጤና ማስጠንቀቂያ ሥርዓት ይኖራታል” ሲሉ ተናግረዋል።

“እነዚህ ገዳይ የሆኑ ምርቶች ናቸው፤ በመሆኑም እነዚህ እርምጃዎች ወጣቶች እና የማያጨሱ ሰዎች እንዳያጨሱ ግንዛቤ ለመስጠት፣ የሚያጨሱ ደግሞ ለማቆም የሚያደርጉትን ጥረት ለማገዝ ይረዳል” ብለዋል ዶግ።

 እአአ በ2020 የወጣው የካናዳ ስታስቲክስ መረጃ ከአራት ሚሊየን በላይ ካናዳውያን በየቀኑ አሊያም አልፎ አልፎ እንደሚያጨሱ ያመለክታል።

ከ38 ሚሊየን በላይ ሕዝብ በሚኖርባት ካናዳ፣ ትንባሆ ማጨስ ቀድሞ መከላከል ለሚቻል በሽታ እና ያለእድሜ ለሚከሰት ሞት ግንባር ቀደም ምክንያት ነው።

እንደ ካናዳ የሳንባ ማኅበር ከሆነ በየዓመቱ 48 ሺህ የሚሆኑ ካናዳውያንም ሲጋራ በማጨስ ምክንያት ይሞታሉ።