እስራኤል በጋዛ በርካታ ሰዎችን ከገደለው የአየር ጥቃት በኋላ የምድር ላይ ዘመቻዎችን ቀጠለች

የእስራኤል ወታደሮች እየተራመዱ

የፎቶው ባለመብት, Israel Defense Forces

እስራኤል፤ በሀማስ በሚመራው የጤና ሚኒስቴር መረጃ መሰረት በሁለት ቀናት ውስጥ ከ430 በላይ ሰዎችን ከገደሉት ተከታታይ የአየር ጥቃቶች በኋላ፤ ሠራዊቷ በጋዛ የምድር ላይ ዘመቻ መጀመሩን አስታወቀች።

የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት፤ የጋዛ ሰርጥ ሰሜናዊ እና ደቡባዊ ክፍል በሚከፍለው የኔትዛሪም ኮሪደር ወታደሮቹ መሰማራታቸውን ገልጿል።

በጋዛ ላይ እንደአዲስ መፈጸም የመጀመረው ጥቃት፤ ከጥር ወር ጀምሮ ሲተገበር የነበረው ደካማ ተኩስ አቁም ፍጻሜ ሆኗል።

ከዚህ ቀደም ብሎ የተባበሩት መንግሥታት በዴር አል ባላህ በሚገኘው ቅጥር ግቢው ውስጥ በተከሰተ ፍንዳታ አንድ ሰራተኛውን ጨምሮ ሁለት ሰዎች መገደላቸውን አስታውቆ ነበር።

የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ይህንን ፍንዳታ በተመለከተ ምርመራ እንደሚያከናውን ቢገልጽም ለዚህ ጥቃት እስራኤል ተጠያቂ የመሆኗን ጉዳይ አስተባብሏል።

የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት፤ በሰሜን እና ደቡባዊ ጋዛ "መካከል በከፊል የሚለይ ስፍራን" ለመፍጠር ሲባል ወታደሮች "ዒላማ ተኮር የምድር ላይ እንስቃሴዎች" ማከናወን መጀመራቸውን ገልጿል።

ቢቢሲ፤ በሰሜናዊ ጋዛ የሚገኘው ቤት ሃኑን የተባለ ስፍራን ጨምሮ ሠራዊቱ እየተንቀሳቀሰ ባለባቸው አካባቢዎች ነዋሪዎች አከባቢውን እንዲለቅቁ ትዕዛዝ እየተሰጠ መሆኑን ተመልክቷል።

ሠራዊቱ፤ የጋዛ ነዋሪዎች የምድር ድንበር በሚገኝባቸው ሶስቱም አቅጣጫዎች የሚገኝ ሰፊ አካባቢን ለቅቀው እንዲወጡ በርካታ ትዕዛዞችን አስተላልፏል። ይህ እርምጃ በአጭር ጊዜ ውስጥ ግዙፍ የምድር ላይ ኦፕሬሽን ሊከናወን እንደሚችል ያመለክታል።

ይህ የልቀቁ ትዕዛዝ በጦርነቱ ምክንያት በተደጋጋሚ ተፈናቅለው ከተኩስ አቁሙ ወቅት ወደ መኖሪያቸው በተመለሱ አብዛኛዎቹ ፍልስጤማውያን ቤተሰቦች ላይ ፍርሃት ፈጥሯል።

አካባቢውን በእስራኤል ሠራዊት ምልክት ከተደረገበት በኋላ ቤተሰቦች ደህንነት ፍለጋ፤ መሸከም የቻሉትን እቃ ይዘው በእግር፣ በጋሪ ወይም በተሽከሪካሪ ስፍራውን ለቅቀው ሲሄዱ ታይቷል።

የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር እስራኤል ካትዝ ረቡዕ ባስተላለፉት መልዕክት፤ በፍልስጤም ግዛት ተይዘው ያሉ ቀሪዎቹ ታጋቾች እንዲለቀቁ "የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ" ሰጥተዋል።

አሁንም ድረስ በህይወት እንዳሉ የሚታመኑትን 24 ሰዎች ጨምሮ 59 ታጋቾች በሀማስ እንደተያዙ እስራኤል ትናገራለች።

የመከላከያ ሚኒስትሩ ካትዝ፤ የእስራኤል ፍላጎቶች ካልተፈጸሙ አማራጭ ሚሆነው "ሙሉ በሙሉ ውድመት እና ጥፋት እንደሆነ" በመጥቀስ ሀማስ እንዲወገድ የሚተላለፈውን ጥሪ ደግመው አሰምተዋል።

ይህ የሰራዊቱ እንቅስቃሴ የተከናወነው ረቡዕ ዕለት በዴር አል ባላህ የሚገኘው ቅጥር ግቢ ላይ በደረሰ ጉዳት የተባበሩት መንግስታት ሠራተኛ ከተገደለ በኋላ ነው።

የመንግስታቱ ድርጅት የፕሮጀክት አገልግሎቶች ጽሕፈት ቤት፤ "የተነጠለ" ቦታ በሚገኝ ህንጻ ላይ "ያልፈነዳ ፈንጂ እንደወደቀ ወይም እንደተተኮሰ" አስታውቋል። ስፍራው ላይ የፈጠረው ምን አይነት ክስተት እንደሆነ ወይም ምን አይነት ከባድ መሳሪያ ጥቅም ላይ እንደዋለ እስካሁን መማረጋገጫ አለመኖሩንም ጽህፈት ቤቱ ገልጿል።

በአየር ጥቃት የወደመ ህንጻ ላይ ህጻን ልጅ ቆማ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የተመድ የፕሮጀክት አገልግሎቶች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ጆርጅ ሞሬራ ዳ ሲልቫ፤ "ይህ [ክስተት] አደጋ አልነበረም" ብለው እንደሚያምኑ ገልጸዋል። አክለውም፤ በጋዛ ያለው ሁኔታ "ከአዕምሮ በላይ ነው" ብለዋል።

የተመድ ዋና ጸኃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ሙሉ ምርመራ እንዲካሄድ ጠይቀዋል።

ማክሰኞ ዕለት እስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያምን ኔትያናሁ "በሙሉ ኃይል ውጊያ በድጋሚ መጀመሩን" የተናገሩ ሲሆን ማንኛውም የተኩስ አቁም ድርድር "ከተኩስ ውስጥ" ሆኖ እንደሚካሄድ ገልጸዋል።

ረቡዕ ዕለትም የአየር ጥቃቶች መፈጸማቸው ቀጥሏል። ከጥቃቱ እንደ አዲስ መጀመር ወዲህ በጋዛ የተፈጸመው የመጀመሪያው የቦንብ ድብደባ ግን ደካማው የተኩስ አቁም እና የታጋቾች ልውውጥ ስምምነት ጥር 11/2017 ዓ.ም. ከተፈረመ ወዲህ ትልቁ ሆኖ ተመዝግቧል።

እስራኤል እና ሀማስ ተፈራረሙትን የተኩስ አቁም ከመጀመሪያ ደረጃው በኃላ እንዴት እንደሚቀጥል መስማማት አልቻሉም። ለዚህ ሲባል የሚደረገው ድርድር ይጀመራል ተብሎ የተጠበቀው ከስድስት ሳምንታት በፊት ነበር።

ሀማስ፤ አሜሪካውያን ታጋቾችን እና አራት አስከሬኖችን እንዲሁም አሁን ያለው አካሄድ እንዲቀጥም ፈቃደኛ ቢሆንም የተኩስ አቁሙ በእስራኤል ፍላጎቶች መሰረት በድጋሚ ድርድር እንደረግበት አይፈልግም።

እስራኤል በበኩሏ በሀማስ ላይ ጫና ለመፍጠር ከተያዘው መጋቢት ወር ጀምሮ ወደ ገዛ ማንኛውም ምግብ፣ ነዳጅ እና የህክምና አቅርቦቶች እንዳይገባ አግዳለች።

አሁን ደግሞ ሀማስ፤ እስራኤል ከአሜሪካ ጋር በመሆን ያረቀቀችውን እና እንደገና ለድርድር ቀረበውን የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲፈርም ለማድረግ ሲባል ወታደሮቿን እና ከፍተኛ ሠራዊት ኃይል ለመጠቀም ፈቃደኛ እንደሆነች አሳይታለች።

ሀማስ በመስከረም 26/2016 ዓ.ም. በእስራኤል ላይ በፈጸመው ጥቃት 1,200 ሰዎች የተገደሉ ሲሆን 251 ሰዎች ታግተዋል። ከታጋቾቹ ውስጥ 25 ያህሉ በተኩስ አቁም ስምምነቱ የመጀመሪያው ደረጃ አፈጻጸም ተለቅቀዋል።

እስራል ለዚህ ጥቃት ምላሽ የሰጠችው ግዙፍ ወታደራዊ ጥቃት በመፈጸም ነው። በሀማስ የሚመራው ጤና ሚኒስቴር መረጃ መሰረት የእስራኤል ጥቃት 48,500 ፍልስጤማውያንን ገድሏል፤ በቤቶች እና መሰረተ ልማቶች ላይም ከፍተኛ ውድመት አስከትሏል።