ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ምዕራባውያንን ለማጥቃት ሩሲያ አገራትን ልታስታጥቅ እንደምትችል ፑቲን አስጠነቀቁ
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን አገራቸው የምዕራባውያንን ዒላማዎች ለማጥቃት አገራትን ልታስታጥቅ እንደምትችል አስጠነቀቁ።
ፑቲን ይህንን የገለጹት ምዕራባውያን ለዩክሬን የረዥም ርቀት ጦር መሳሪያ መስጠታቸውን በተቹበት ወቅት ነው።
አሜሪካን ጨምሮ በርካታ አገራት ዩክሬን በሩሲያ ውስጥ የሚገኙ ዒላማዎችን እንድትመታ ፈቃዳቸውን ሰጥተዋል።
እንዲህ ዓይነቱ እርምጃ ወደ “ከባድ ችግሮች” ሊያመራ ይችላል ሲሉ ፑቲን ለውጭ አገር ጋዜጠኞች ተናግረዋል።
“ግዛታችንን ለማጥቃት እና በጦር ቀጠና ችግር የሚፈጥርብን የጦር መሳሪያ ማቅረብ ይቻላል ብሎ የሚያስብ ካለ ለምንድነው እኛስ ተመሳሳይ የጦር መሳሪያ ለሌሎች አገራት በማቅረብ ይህንን በሚያደርጉት ላይ ጥቃት እንዲፈጸም የማድረግ መብት የማይኖረን? ” ሲሉ ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል።
"ይህም የተመጣጠነ ሊሆን ይችላል። በዚህ ዙሪያ እናስብበታለን።" ብለዋል።
ሩሲያ ለየትኛዎቹ አገሮች የጦር መሣሪያ ማቅረብ እንደምትችል አልገለጹም።
ለዩክሬን ባቀረበችላት የጦር መሳሪያዎች በሩሲያ ውስጥ ያሉ ዒላማዎችን መምታት እንደምትችል የገለጸቸውን ጀርመንን ለይተው አነስተዋል።
"በሩሲያ ግዛት የሚገኙ ዒላማዎችን የሚመቱ ተጨማሪ ሚሳኤሎች ይኖራሉ ማለታቸው የሩሲያ እና የጀርመንን ግንኙነት ያበላሻል" ብለዋል ፑቲን።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ዩክሬን በአሜሪካ የቀረበላትን የጦር መሳሪያ በመጠቀም በሩሲያ ኢላማዎችን እንድትመታ ፍቃድ ሰጥተዋታል።
ይህ ፈቃድ ግን በካርኪቭ ክልል አቅራቢያ ብቻ የሚገኙ ዒላማዎችን የሚመለከት ነው። ዩክሬን የረዥም ርቀት ኤቲኤሲኤምኤስ ሚሳኤሎችን በሩሲያ ምድር መጠቀም አትችልም ሲል ዋይት ሃውስ ገልጿል።
ዩክሬን ባለፉት ጥቂት ቀናት የአሜሪካ የጦር መሣሪያ ተጠቅማ ሩሲያ ውስጥ ጥቃት ፈጽማለች ሲሉ አንድ የአሜሪካ ሴናተር እና አንድ የምዕራብ አገር ባለስልጣን ረቡዕ ዕለት ለአሶሼትድ ፕሬስ ተናግረዋል።
በዩክሬንን ሰሜናዊ ድንበር አቅጣጫ ሩሲያ የከፈተችውን አዲስ ጥቃት ተከትሎ ከካርኪቭ በስተሰሜን ምስራቅ ከባድ ጦርነት እየተካሄደ ነው። የዩክሬን ሁለተኛ ትልቋ ግዛት ካርኪቭ ከሩሲያ ድንበር 30 ኪሜ ብቻ ርቃ ትገኛለች።
የዩናይትድ ኪንግደም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሎርድ ካሜሮን በበኩላቸው የብሪታንያ የጦር መሳሪያ አጠቃቀምን የምትወስነው ዩክሬን ናት ብለዋል። በሩሲያ ግዛት የሚገኙ ዒላማዎችን የመምታት መብት እንዳላትም አክለዋል።
ዩክሬን የሰሜን ኮሪያ ሚሳኤሎች በዩክሬን ግዛት ውስጥ ጥቅም ላይ እየዋሉ ነው ስትል፤ የምዕራቡ ዓለም የስለላ ድርጅቶች በበኩላቸው ሩሲያ በጦርነቱ ወቅት ኢራን ሰራሽ ድሮኖችን ስትጠቀም ቆይታለች ብለዋል።
ሩሲያ እአአ በ2022 ነበር ዩክሬንን ላይ ወረራ የፈጸመችው።
ፑቲን ከውጭ አገር ጋዜጠኞች ጋር ቆይታ ያደረጉት በሴንት ፒተርስበርግ በተካሄደው ዓመታዊው ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ፎረም ላይ ነው።
ሩሲያ የኒውክሌር ጦር መሣሪያን ፈጽማ አትጠቀምም ብለው ምዕራባውያን መገመታቸውም ስህተት ነው ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
ፑቲን በዩክሬን ሊፈጸም ስለሚችለው የኒውክሌር ጥቃት ስጋት ከሮይተርስ ለቀረበላቸው ጥያቄ "በአንዳንድ ምክንያቶች ምዕራባውያን ሩሲያ ፈጽሞ እንደማትጠቀምበት ያምናሉ" ብለዋል።
"እኛ የኒውክሌር ስርዓት አለን። ምን እንደሚል ተመልከቱ። ሉዓላዊነታችን እና ግዛታችን አደጋ ላይ ከወደቀ ሁሉንም መንገዶች መጠቀም እንደምንችል አስቀምጠናል።”
"ይህ በዋዛ መወሰድ የለበትም" ብለዋል።
ሩሲያ በኔቶ ግዛት ላይ ጥቃት ለመሰንዘር ዕቅድ አላት የሚለውን ሃሳብም ፑቲን ውድቅ አድርገውታል።
"ሩሲያን ጠላት እንድትሆን ማድረግ አያስፈልግም። በዚህ ራስን ብቻ ነው የምትጎዳው" ሲሉ ፑቲን ተናግረዋል።
"ሩሲያ ኔቶን ለማጥቃት ፈልጋለች ብለው ያስባሉ። አብዳቹሃል?”
ይህንንስ ማን አመጣው? ይሄ ሙሉ በሙሉ የማይሆን ነው። ሙሉ ለሙሉ የማይረባ ነገር ነው" ብለዋል።