ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የአንድ ቢሊየን ዶላር ልገሳ ያገኛው የአሜሪካው ዩኒቨርስቲ ዶክተሮችን በነጻ ሊያስተምር ነው
የአሜሪካው ኒው ዮርክ ዩኒቨርስቲ የህክምና ትምህርት ቤት አንድ ቢሊየን ዶላር ልገሳ ከአንዲት ግለሰብ በማግኘቱ የህምክና ትምህርት ከክፍያ ነጻ ሊሰጥ ነው።
የቀድሞዋ ፕሮፌሰር እና በሕይወት የሌሉት የዎል ስትሪት ባለሃብት የነበሩት ግለሰብ ሚስት የሆኑት የ93 ዓመቷ ዶ/ር ሩት ጎትስማን 1 ቢሊየን ዶላር በልገሳ ያበረከቱት በኒው ዮርክ ዩኒቨርስቲ ለአልበርት አንስታይን የህክምና ትምህርት ቤት ነው።
ይህም የገንዘብ ልገሳ ለአንድ የአሜሪካ ትምህርት ቤት በታሪክ ከተሰጠ ገንዘብ ከፍተኛው ሲሆን፣ የህክምናው ትምህርት ቤትም አስካሁን ካገኘው ቀዳሚው ልገሳነው ተብሏል።
የዩኒቨርስቲው ዲን ደ/ር ያሮን ዮመር ልገሳውን በተመለከተ “ትምህርት ቤታችን መክፍል የሚችሉትን ብቻ ሳይሆን ለተነሳንለት ዓላማ ቁርጠኝነት ያላቸውን ተማሪዎችን ለመሳብ መሠረታዊ ለውጥ ያመጣል” ብለዋል።
በህክምናው ትምህርት ቤት የሚማሩ ተማሪዎች በዓመት ወደ 59 ሺህ ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ መክፈል የሚጠበቅባቸው በመሆኑ በርካቶች ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ ለከፍተኛ ዕዳ ይዳረጋሉ።
የህክምናው ትምህርት ቤት ልገሳውን ማግኘቱን ተከትሎ እንዳሳወቀው የዚህን ዓመት የትምህርት ክፍያ የፈጸሙ ተማሪዎች ገንዘባቸው የሚመለስላቸው ሲሆን፣ ከመጪው ነሐሴ ጀምሮ ደግሞ በነጻ ትምህርታቸውን ይቀጥላሉ።
ከፍተኛ መጠን ያለው ይህ ልገሳ “ተማሪዎቻችንን ከዕዳ ነጻ በማውጣት በገንዘብ ምክንያት የሚስተጓጎሉ ሃሳቦችን እና ፕሮጀክቶችን ያለችግር እንዲያካሂዱ ያደርጋቸዋል” ሲሉ የዩኒቨርስቲው ዲን ተናግረዋል።
የገንዘብ ልገሳውን የሰጡት የ93 ዓመቷ ዶ/ር ጎትስማን ከአውሮፓውያኑ 1968 አንስቶ በትምህርት ቤቱ በመምህርነት ያገለገሉ ሲሆን፣ በሙያቸው ባካሄዷቸው ጥናቶች እና ምርምሮች ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተዋል።
በኒውዮርክ ካሉ ባለሃብቶች አንዱ የነበሩት የዶክተሯ ባለቤት ዴቪድ ጎትስማን ያረፉት ባለፈው ዓመት በ96 ዓመታቸው ነበር።
ለጋሷ ዶ/ር ጎትስማን ባስተላላፉት መልክዕክት በህክምና ትምህርት ቤቱ የሚሠለጥኑ ዶክተሮች ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ “ምርጥ የሚባለውን የጤና ክብካቤ አገልግሎት በዩኒቨርስቲው ዙሪያ ላሉ ድሃ ማኅበረሰቦች ብሎም በመላው ዓለም እንደያዳርሱ” ጥሪ አቅርበዋል።
ጨምረውም “ይህን ያህል መጠን ያለውን ገንዘብ ትቶልኝ ያለፈውን ባለቤቴን አመሰግነዋለሁ። ይህንንም ገንዘብ ለዚህ ለተቀደሰ ዓላማ ሳበረክት እጅግ ታላቅ ደስታ ይሰማኛል” ብለዋል።
ዶክተር ጎትስማን ከኒው ዮርክ ታይምስ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ባለቤታቸው ከማረፋቸው በፊት ያላቸውን ከፍተኛ መጠን ያለውን ሃብት በሙሉ ወደ እሳቸው ያስተላለፉ ሲሆን በገንዘቡም “ትክክል ነው ያልሽውን ሁሉ አድርጊበት ብሎኛል” በማለት በውርስ ካገኙት ገንዘብ አንድ ቢሊዮን ዶላሩን ለህክምና ትምህርት ቤቱ አበርክተዋል።