በዓለም ዙሪያ እየተስፋፋ ስለመጣው የሳንባ ምች በሽታ መታወቅ ያለባቸው 5 ነጥቦች

እንደ ሳንባ ምች ያሉ የመተንፈሻ አካላት በሽታዎች ክስተት መጠን ባልተለመደ መልኩ በዓለም ዙሪያ መጨመራቸው ሪፖርት ተደርጓል።

የቻይና ብሔራዊ ጤና ኮሚሽን እአአ በ2023 ኢንፍሉዌንዛ፣ ኮቪድ እና በህጻናት ላይ የሚከሰተው የባክቴሪያ ኢንፌክሽንን (ማይኮፕላስማ ኒሞኒያ) ጨምሮ በአገሪቱ በርካታ በሽታዎች መበራከታቸውን ዘግቧል።

የዓለም ጤና ድርጅት በበኩሉ ቻይና የሕፃናት የሳንባ ምች (ኒሞኒያ) ላይ የጤና ባለሙያዎች ስጋት የሚፈጥር ምንም ዓይነት ያልተለመደ በሽታ አምጪ ተህዋስያን እንዳላገኙ አስታውቋል።

ቻይና በኮቪድ ምክንያት ጥላው ከነበረው ጠንክር ያለ የወረርሽኝ ገደብ በኋላ የሕብረተሰቡ በሽታን የመከላከል አቅም ከመዳከሙ በላይ የመጀመሪያውን የክረምት ወቅት እያስተናገደች ነው።

ይህ በቻይና ተጥሎ የነበረው የእንቅስቃሴ ገደብ ከተነሳ በኋላ የመጀመሪያው ክረምት ነው። ጠንከር ያለ ወረርሽኝ ገደቦች የሕዝብን የመከላከል አቅም እንዲዳከም አድርጓል።

ኮቪድ በፈጠረው መገለል ምክንያት የሰዎች ተፈጥሯዊ በሽታን የመከላከል አቅም መቀነሱን ያወሳው የዓለም ጤና ድርጅት፣ ህጻናት ለመጀመሪያ ጊዜ ለበሽታው በመጋለጣቸው ቁጥሩ መጨመሩን ጠቅሷል።

ዩናይትድ ኪንግደም፣ ፈረንሳይ፣ ዴንማርክ እና አሜሪካን ጨምሮ በርካታ አገራትም የኮቪድ ወረርሽኝ ገደቦችን ካነሱ በኋላ ተመሳሳይ የጉንፋን መሰል በሽታዎች መስፋፋትን አይተዋል።

የዓለም ጤና ድርጅት እንደሚገልጸው ከሆነ የሳንባ ምች በዓለም አቀፍ ደረጃ ለልጆች ሕይወት ማለፍ ምክንያት ከሆኑ ተላላፊ በሽታዎች ዋነኛው ነው።

እአአ በ2019 ብቻ 740,180 ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ህፃናትን ሕይወት ቀጥፏል። በዚህ የዕድሜ ክልል ሕይወታቸው ካጡ ሕፃናት 14 በመቶዎቹ በዚህ ምክንያት የሞቱ ናቸው።

በደቡባዊ እስያ እና ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገራት የሟቾቹ ቁጥር ከዚህም ከፍ ያለ ነው።

ስለ የሳንባ ምች ማወቅ ያሉብን አምስት ነጥቦች የሚከተሉት ናቸው።

የሳንባ ምች ምንድን ነው?

እንደ ናሽናል ፋውንዴሽን ፎር ኢንፌክሺየስ ዲዚዝ (ኤንአይዲ) ከሆነ፣ የሳምባ ምች አብዛኛውን ጊዜ በኢንፌክሽን ምክንያት የሚመጣ የሳንባ መቆጣት ነው።

ማንኛውም ሰው በሳንባ ምች ሊያዝ ይችላል። አንዳንድ ሰዎች ግን በበሽታው የመያዝ ከፍተኛ ስጋት አለባቸው።

ህጻናት፣ በእድሜ የገፉ ሰዎች፣ ወይም እንደ የልብ ህመም፣ የስኳር በሽታ፣ የሳንባ በሽታ፣ በሽታ የመከላከል አቅምን የሚያዳክሙ እና አንዳንድ ካንሰሮችን የመሳሰሉ ሥር የሰደዱ የጤና እክሎች ያለባቸው ሰዎች የበለጠ ተጋላጭ ናቸው።

ምልክቶቹስ ምንድን ናቸው?

የዚህ በሽታ ዋነኛ ምልክቶች ትኩሳት፣ ብርድ ብርድ ማለት፣ ሳል፣ የትንፋሽ ማጠር እና የድካም ስሜት ናቸው።

ውስብስብ ደረጃ ላይ ሲደርስ የመተንፈሻ አካል መድከም፣ ለሕይወት አስጊ ህመም እና አለፍ ሲልም ሞትንም ሊያካትቱ ይችላሉ። በሽታው እንዳይባባስ ለመከላከል ቅድመ ምርመራ እና ህክምና አስፈላጊ ነው።

ሰዎች ለመተንፈስ መቸገር፣ በከንፈራቸው እና በጣታቸው ላይ ሰማያዊ ቀለም ሲያዩ፣ የደረት ህመም፣ ከፍተኛ ትኩሳት፣ ወይም ፈሳሽ ያለው ሳል ያሉ ምልክቶችን ሲያጋጥማቸው በፍጥነት የህክምና እርዳታ ማግኘት አለባቸው ሲል የአሜሪካ የሳንባ ማኅበር መክሯል።

የሳንባ ምች እንዴት ይስፋፋል?

የሳንባ ምች በተለያዩ መንገዶች ሊሰራጭ ይችላል። በልጆች አፍንጫ ወይም ጉሮሮ ውስጥ በብዛት የሚገኙት ቫይረሶች እና ባክቴሪያዎች ወደ ውስጥ ከገቡ ሳንባን ሊበክሉ ይችላሉ።

በተጨማሪም በሳል እና በማስነጠስ ወቅት የሚኖሩ የፈሳሽ ጠብታዎች፣ ወይም እቃዎችን በመንካት እና በላዩ ላይ ያሉ ጀርሞችን ወደ ሰውነት በማስገባት ሊሰራጭ ይችላል።

የሳንባ ምች መንስኤ የሆኑትን የተለያዩ በሽታ አምጪ ተህዋሲያን እና የሚተላለፉባቸውን መንገዶች በተመለከተ ተጨማሪ ምርምር መደረግ አለበት። ይህ ለህክምናው እና ለመከላከል እርምጃው ወሳኝ ጠቀሜታ አለው።

የሳንባ ምች እንዴት ይታከማል?

ኢንፌክሽኑ በፀረ ተህዋሲያን (አንቲባዮቲክ) መታከም የሚችል ከሆነ እነሱ ይታዘዛሉ። አንዳንድ ሰዎች አንቲባዮቲኮች ላያስፈልጋቸውም ይችላል።

አብዛኞቹ ሰዎች ከሁለት እስከ አራት ሳምንታት ውስጥ ይሻላቸዋል።

ይሁን እንጂ አንዳንድ ሰዎች ለከባድ ህመም የመጋለጥ ዕድላቸው ከፍተኛ ነው፤ ስለዚህም ለህክምና ወደ ሆስፒታል መሄድ ሊኖርባቸው ይችላል።

በሆስፒታል ውስጥ ለመተንፈስ እንዲረዳቸው ከሚሰጠው ከኦክሲጅን ጎን ለጎን ፈሳሽ እና አንቲባዮቲክስ ይሰጣቸዋል።

ሌሎች ሁኔታዎችን ለመፈተሽም የደረታቸው ኤክስሬይ መነሳት እና የደም ምርመራ ሊያደርጉ ይችላሉ።

የሳንባ ምች እንዴት መከላከል ይቻላል?

ለመከላከል ጥቂት እርምጃዎችን መውሰድ ይችላሉ።

ክትባቶች በሳንባ ምች ባክቴሪያ ወይም በጉንፋን ቫይረስ የሚመጣውን የሳንባ ምች ለመከላከል ይረዳሉ።

የአሜሪካ ብሔራዊ የልብ፣ የሳንባ እና የደም ተቋም እንደሚገለጸው ከሆነ ክትባቶች ሁሉንም የሳንባ ምች በሽታዎች መከላከል አይችሉም።

ክትባቱን ካልወሰዱ ሰዎች ጋር ሲነጻጸሩ፣ ክትባቱ የተሰጣቸው እና በሳንባ ምች የተያዙ ሰዎች ከባድ ያልሆነ፣ ቀላል ኢንፌክሽን እና ለረጅም ጊዜ የማይቆይ የሳንባ ምች ይኖራቸዋል።

ንጽህና (እጅን አዘውትሮ መታጠብ)፣ ማጨስን ማቆም እና የሰውነትን በሽታ የመከላከል ሥርዓትን በመደበኛ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በማድረግ እና ጤናማ አመጋገብን መከተል በሳንባ ምች የመያዝ ዕድልን የሚቀንሱ ሌሎች መንገዶች ናቸው።

የዩናይትድ ኪንግደም ብሄራዊ የጤና አገልግሎት በሳንባ ምች በሽታ የመጠቃት አደጋ የተጋለጡ ሰዎች ክትባት እንዲወስዱ ይመክራል።

ይህ ክትባት እንደ ማጅራት ገትር እና ሴፕሲስ ካሉ ከባድ በሽታዎችን ሊያስከትሉ ከሚችሉ አንዳንድ የባክቴሪያ ኢንፌክሽኖች ለመከላከል ይረዳል።