ስለ አቶ ግርማ የሺጥላ ግድያ እስካሁን የሚታወቁ ጉዳዮች

የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ አባል እና የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ግርማ የሺጥላ ሐሙስ 19/2023 ዓ.ም. በተፈጸመባቸው ጥቃት መገደላቸው ተገልጿል።

የገዢው ፓርቲ ከፍተኛ ባለሥልጣን የሆኑት አቶ ግርማ በግልጽ ማንነታቸው ባልታወቁ ታጣቂዎች የተገደሉት ከዋና ከተማዋ አዲስ አበባ 250 ኪሎሜትር በስተሰሜን በሚገኝ ስፍራ ላይ ነው።

የዚህን ከፍተኛ የገዢው ፓርቲ አባል ግድያን በተመለከተ እስከ አሁን የምናውቃቸው የሚከተሉት ጉዳዮች ናቸው።

ግድያው የት ተፈጸመ?

የገዢው ብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ አባል እና በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የብልጽግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ እና ከፍተኛ አመራር የሆኑት አቶ ግርማ የሺጥላ የተገደሉት በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ውስጥ ነው።

ከቀናት በፊት በዞኑ ዋና ከተማ ደብረ ብርሃን ውስጥ የተለያዩ የልማት እና የመሠረተልማት ሥራዎችን ሲጎበኙ የነበሩት አቶ ግርማ፣ በዚያው ዞን ውስጥ ወደሚገኘው የትውልድ ቦታቸው መሃል ሜዳ ተጉዘው ሲመለሱ ለህልፈት የዳረጋቸው ጥቃት እንደተፈጸመባቸው ተነግሯል።

ከአቶ ግርማ እና አብረዋቸው በነበሩ ሰዎች ላይ ጥቃቱ የተፈጸመው ሐሙስ ሚያዝያ 19/2015 ዓ.ም. ከሰዓት በኋላ መንዝ ጓሳ በተባለ ስፍራ ላይ ነበር።

የአማራ ክልል ባወጣው መግለጫ ላይ እንዳመለከተው ጥቃቱ የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ አባል እና የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊው በአቶ ግርማ የሺጥላ፣ በግል ጠባቂዎቻቸው እና በቤተሰቦቻቸው ላይ መፈጸሙን አመልክቷል።

ቢቢሲ ከአካባቢው ነዋሪዎች ባገኘው መረጃ መሠረት ጥቃቱ ከተፈጸመ በኋላ የተጎዱ ሰዎችን ሕይወት ለማትረፍ በሄሊኮፕተር ተወስደዋል።

ሐሙስ ከሰዓት በኋላ በተፈጸመው ጥቃት አቶ ግርማ የሺጥላ እና ሌሎች አራት ሰዎች የተገደሉ ሲሆን፣ በቀዳሚነት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የሐዘን መግለጫ አውጥተዋል።

በማስከተልም የአማራ ክልል መንግሥት፣ የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት እንዲሁም የተለያዩ ክልሎች በከፍተኛ ባለሥልጣኑ ላይ ተፈጸመውን ግድያ አውግዘው ሐዘናቸውን ገልፀዋል።

ግድያውን ማን ፈጸመው?

ለአቶ ግርማ የሺጥላ ግድያ ኃላፊነት የወሰደም ሆነ በስም በቀጥታ ተጠያቂ የሆነ አካል የለም።

ይሁን እንጂ የአማራ ክልል እና የፌደራል መንግሥት ለባለሥልጣኑ ግድያ “ኢ-መደበኛ ኃይሎች” እና “ጽንፈኛ ኃይሎች”ን ተጠያቂ አድርገዋል።

የአማራ ክልል የአቶ ግርማ ግድያን በተመለከተ ቀደም ሲል ባወጣው መግለጫ ላይ ኃላፊው የተገደሉት “በኢ-መደበኛ ኃይሎች” ነው ብሎ ነበር።

ይሁን እንጂ የክልሉ ኮሚኒኬሽን የቀደመ መግለጫውን በማንሳት በአዲስ የቀየረ ሲሆን፣ በአዲሱ መግለጫውም አቶ ግርማ የተገደሉት “በኢ-መደበኛ ኃይሎች” የሚለውን በታጠቁ “ጽንፈኛ ኃይሎች” በሚል ቀይሮታል።

ከዚህ ቀደም የአማራ ክልል አመራሮችም ሆኑ የፌደራል መንግሥት ባለሥልጣናት በመንግሥት አደረጃጀት ስር የሌሉ እና ታጥቀው የሚንቀሳቀሱትን “ኢ-መደበኛ ኃይል” በማለት ይጠሯቸዋል።

በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ደግሞ የብሔር ፖለቲካን የሚያከሩትን ደግሞ “ጽንፈኛ ኃይሎች” በማለት ሲገልጿቸው እንደነበረ ይታወቃል።

የክልሉ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ከዚህ ቀደም በሰጧቸው መግለጫዎች ፋኖን እና “በፋኖ ስም” ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ ኃይሎችን “ኢ-መደበኛ” ብለው ሲገልጿቸው ነበር።

የቀድሞ የአማራ ክልል ርዕስ መስተዳደር እና የአሁኑ የብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ተመስገን ጥሩነህ ባለፈው ዓመት ፋና ቴሌቪዥን ላይ እንደተናገሩት ኢመደበኛ የተባሉት ኃይሎች የተለያየ ቅርጽ እንዳላቸው ገልጸዋል።

በዚህም በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ወቅት ከመንግሥት ጎን ተሰልፈው የተዋጉ መኖራቸውን ገልጸው፣ አልፎ አልፎ ዝርፊያ የሚፈጽሙ እንዳሉም አመልክተዋል።

አቶ ግርማ ለምን ዒላማ ሆኑ?

የአቶ ግርማ የሺጥላን ግድያ ቀድመው ይፋ ያደረጉት ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ ሲሆኑ፣ ኃላፊው የተገደሉት በሚያራምዱት የተለየ ሃሳብ መሆኑን አመልክተዋል።

ጠቅላይ ሚንስትሩ በመግለጫቸው፤ “ከእኛ የተለያ ሐሳብ ማሰብ አልነበረበትም ብለው የሚያምኑ ነውጠኞች እና ጽንፈኞች በፈጸሙት አስነዋሪ እና አሰቃቂ ተግባር” አቶ ግርማ ተገድለዋል ብለዋል።

የአማራ ክልልም “ጽንፈኛ ኃይሎች በሀሳብ ትግል ማሽነፍ ያልቻሉትን በኃይል ለማስፈጸም ያደረሱት ጥቃት” በማለት ግድያውን የገለጸው ሲሆን፣ አቶ ግርማ ዒላማ የተደረጉት የተለየ አቋም በማንጸባረቃቸው መሆኑን ጠቅሷል።

በይፋዊ መግለጫዎች “ጽንፈኞች” የማይቀበሉት እና አቶ ግርማ የሚያራምዱት የተለየ አመለከታት ምን እንደሆነ በግልጽ የተባለ ነገር ባይኖርም፤ ባለሥልጣኑ ሕይወታቸው ከማለፉ በፊት የክልል ልዩ ኃይሎችን እንደ አዲስ ማደራጀትን በተመለከተ በሚሰጧቸው አስተያየቶች ትችት ሲቀርብባቸው ነበር።

በአቶ ግርማ ላይ ግድያው የተፈጸመው የፌደራል መንግሥቱ የክልል ልዩ ኃይሎችን መልሶ በማደራጀት ወደ መከላከያ፣ ፌደራል እና ክልል ፖሊሶች ለማካተት ከሳምንታት በፊት ያወጣው ዕቅድ በአማራ ክልል ከፍተኛ ሕዝባዊ ተቃውሞን ካስከተለ በኋላ ነው።

አቶ ግርማ በወቅቱ ልዩ ኃይሎችን መልሶ ለማደረጃት የተጀመረውን ሥራ በተመለከተ በአማራ ክልል እና በፌደራል የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ላይ በመቅረብ ከሚያስረዱ ባለሥልጣናት መካከል አንዱ ነበሩ።

በዚህም የተነሳ የአማራ ክልል የፀጥታ እና የደኅንነት ስጋት ስላለበት ልዩ ኃይሉን ማፍረስ ተገቢ አይደለም ከሚሉ ወገኖች በኩል አቶ ግርማ ጠንካራ ተቃውሞ እና ትችት ሲቀርብባቸው ነበር።

የአቶ ግርማ ሚና በአስተዳደር እና በፓርቲ ውስጥ?

በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ውስጥ መሃል ሜዳ እንደተወለዱ የሚነግረው አቶ ግርማ የሺጥላ ለሦስት አስርት ዓመታት ለሚጠጋ ጊዜ በፓርቲ እና በመንግሥት የኃላፊነት ደረጃዎች ከወረዳ እስከ ክልል ድረስ አገልግለዋል።

በዚህም በሰሜን ሸዋ ዞን የአንፆኪያ ገምዛ ወረዳ የኢኮኖሚ ዘርፍ ኃላፊ፣ የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ፣ የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ እና የተለያዩ ቢሮዎች ኃላፊ ሆነው የሰሩ ሲሆን የሰሜን ሸዋ ዞን ምክትል እና ዋና አስተዳዳሪ ሆነው አገልግለዋል።

የአማራ ክልል ምክር ቤት አባል የነበሩት አቶ ግርማ የሺጥላ በሰሜን ሸዋ ዞን ውስጥ ከሰሩባቸው ኃላፊነቶች ባሻገር በክልሉ ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ ሆነው ሰርተዋል።

አቶ ግርማ በፓርቲ ኃላፊነት ላይም የተለያዩ ቦታዎችን በመያዝ የሰሩ ሲሆን፣ የኢህአዴግ አንድ አካል የነበረው የብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) የሰሜን ሸዋ ዞን ጽህፈት ቤት ኃላፊ፣ የደብረ ብርሃን ከተማ የፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ነበሩ።

አስከ ህልፈታቸው ድረስ ደግሞ የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ አባል እና በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የገዢው ብልጽግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሆነው ሲሰሩ ቆይተዋል።