የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ግርማ የሺጥላን ጨምሮ አምስት ሰዎች ተገደሉ

የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ አባል እና የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ የሆኑት አቶ ግርማ የሺጥላን ጨምሮ አምስት ሰዎች በተፈጸመባቸው ጥቃት ተገደሉ።

የገዢው ብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራር የሆኑት አቶ ግርማ የሺጥላ የተገደሉት በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ውስጥ ለሥራ ጉዳይ ተጉዘው ከሰሜን ሸዋ መሃል ሜዳ ወደ ደብረ ብርሃን በመመለስ ላይ ሳሉ መሆኑ ተነግሯል።

በአቶ ግርማ እና አብረዋቸው በነበሩ ሰዎች ላይ ጥቃቱ የተፈጸመው ሐሙስ ሚያዝያ 19/2015 ዓ.ም. ከሰዓት በኋላ መንዝ ጓሳ በተባለ ስፍራ ላይ “በታጠቁ ኢ-መደበኛ ኃይሎች” መሆኑን የአማራ ክልል ባወጣው መግለጫ ላይ አመልክቷል።

በዚህ ጥቃትም የብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራር የሆኑትን አቶ ግርማ የሺጥላን ጨምሮ አምስት ሰዎች መገደላቸውን ክልሉ አረጋግጧል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድም የፓርቲያቸው ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል በሆኑት በአቶ ግርማ የሺጥላ ሞት የተሰማቸውን ሐዘን በጽህፈት ቤታቸው በኩል ባስተላለፉት መልዕክት ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ሐሳብን በሐሳብ ማሸነፍ ያቃታቸው አካላት የወንድማችንን የግርማ የሺጥላን ነፍስ ነጥቀዋል” በማለት፣ “በሐሳብ የተለየንን ሁሉ በጠመንጃ ለማሳመን መነሣት የጽንፈኝነት የመጨረሻው ጥግ ነው” በማለት ግድያውን አውግዘዋል።

ጨምረውም አቶ ግርማ ተወልደው ባደጉበት አካባቢ፣ “ነውጠኛ ጽንፈኞች የፈጸሙት አስነዋሪ እና አሰቃቂ ተግባር፣ ጽንፈኝነትን በጊዜ ታግለን ካላስወገድነው ወደ መጨራረስ እንደሚወስደን ጉልህ ማሳያ ነው” ብለዋል።

በገዢው የብልጽግና ፓርቲ ውስጥ እና በአማራ ክልል ቅርንጫፉ ውስጥ ከፍተኛ አመራር በሆኑት በአቶ ግርማ የሺጥላ ላይ ለተፈጸመው ግድያ ተጠያቂው ማን እንደሆነ እስካሁን በስም የተጠቀሰ አካል የለም።

ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች እንደገለጹት ጥቃቱ የተፈጸመው አቶ ግርማ የሺጥላ እና አብረዋቸው ይጓዙ በነበሩ ሰዎች ላይ ነው።

የአማራ ክልል እንዳለው ጥቃቱ የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ አባል እና የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ በአቶ ግርማ የሺጥላ፣ በግል ጠባቂዎቻቸው እና በቤተሰቦቻቸው ላይ መፈጸሙን አመልክቷል።

ጥቃቱን ተከትሎ አቶ ግርማን ጨምሮ ጉዳት የደረሰባቸውን አብረዋቸው የነበሩ ሰዎች በአስቸኳይ ለህክምና ከጥቃቱ ስፍራ መወሰዳቸው ተነግሯል።

የአማራ ክልል ግድያውን ተከትሎ ሐሙስ ምሽት ባወጣው መግለጫ “የሽብር ድርጊት” ያለውን ፈጸሙ ባሉት ኃይሎች ላይ የክልሉ መንግሥት “የማያዳግም እርምጃ ይወስዳል። የጥቃቱን አድራሾችም ለሕግ ያቀርባል” ብሏል።

ጨምሮም “የጥፋት ኃይሎች. . . ክልሉን የማፍረስ ተልዕኮ ይዘው የሚንቀሳቀሱ መሆኑን” ገልጾ፣ እነዚህ ኃይሎችን እንደማይታገስ እና “ጥብቅ እርምጃ እንደሚወስድ” በመግለጫው አሳውቋል።

አቶ ግርማ የሺጥላ ከመገደላቸው አንድ ቀን ቀደም ብሎ በደብረ ብርሃን ከተማ እና በደብረ ብርሃን ዩንቨርስቲ አማካይነት እየተከናወኑ ያሉ የመሠረተ ልማት ግንባታዎችን መጎብኘታቸው ተዘግቦ ነበር።

ቢቢሲ ከአማራ ክልል እና ከፌደራል መንግሥቱ የሚመለከታቸው አካላት ስለጥቃቱ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ያደረገው ሙከራ አልተሳካም።