በመንግሥት እና በታጣቂ ቡድኑ መካከል የተጀመረው ንግግር ያጫረው ተስፋ እና ስጋት

የኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥት እና የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት በአገሪቱ የኦሮሚያ ክልል ውስጥ ላለፉት አራት ዓመታት ሲካሄድ የነበረውን ግጭት ለማብቃት ንግግር ማድረግ ጀምረዋል።

ሮይተርስ የዜና ወኪል የቀጠናዊ ድርጅቱን ኢጋድ ቃል አቀባይን ጠቅሶ እንደዘገበው በሁለቱ ወገኖች መካከል የሚደረገው ንግግር ታንዛኒያ ውስጥ ማክሰኞ ዕለት ተጀምሯል።

የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ባለሥልጣን (ኢጋድ) ዋና ፀሐፊ ቃል አቀባይ ኑር ሞሐመድ ሼክ እንዳሉት በተጀመረው ንግግር “ፖለቲካዊ ስምምነት ላይ ይደረሳል” የሚል ተስፋ አላቸው።

ለዓመታት በመንግሥት ኃይሎች እና በአማጺው መካከል በተካሄዱ ግጭቶች እና በተፈጸሙ ጥቃቶች የተጎዱ እና ሰላማቸውን አጥተው ስጋት ውስጥ የኖሩት የምዕራብ ኦሮሚያ ነዋሪዎች ንግግር ሊጀመር መሆኑ የተለየ ስሜት ፈጥሮባቸዋል።

በምዕራብ ኦሮሚያ የተለያዩ አካባቢዎች ለዓመታት የቆየው የደኅንነት ስጋት በነዋሪዎች ዘንድ ከባድ ፍርሃት እና አለመረጋጋትን ፈጥሮባቸዋል። በዚህም ሳቢያ ቢቢሲ ያናገራቸው ሁሉም ነዋሪዎች ስማቸው እንዲጠቀስ ፈቃደኛ አይደሉም።

አንድ ነዋሪ የመንግሥት እና ታጣቂ ቡድኑ ድርድር ውጤታማ እንዲሆን “ፀሎት አደርጋለሁ” ሲል፣ በሥራ ቦታው በታጣቂ ቡድኑ ልታገት እችላለሁ ብሎ የሚሰጋው መሃንዲስ ደግሞ ሁለቱ ወገኖች ቢስማሙም “ለደኅንነቴ ማረጋገጫ ስለመሆኑ እርግጠኛ አይደለሁም” ይላል።

ከኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ተለይቶ የወጣው እና መንግሥት ሸኔ የሚለው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት፣ ፖለቲካዊ አጀንዳን አንግቦ ባለፉት ዓመታት በአራቱ የወለጋ ዞኖች፣ በምዕራብ ሸዋ እና ደቡብ ኦሮሚያ አካባቢዎች ሲንቀሳቀስ ቆይቷል።

በእነዚህ ዓመታት ታጣቂ ቡድኑ ከመንግሥት ኃይሎች ጋር ግጭት ውስጥ ቆይቷል። የታጣቂ ቡድኑን እንቅስቃሴ ተከትሎ ዜጎች ለሞት እና ስደት ተዳርገዋል፣ ንብረት ወድሟል፣ በበርካታ አካባቢዎችም ሰላም ርቋቸው ቆይተዋል።

ባለፈው እሁድ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ይፋ እንዳደረጉት እና ታጣቂ ቡድኑ እንዳረጋገጠው፣ የፌደራል መንግሥቱ እና የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ልዑኮቻቸውን ወደ ታንዛኒያ ልከው ለንግግር መቀመጣቸው ለብዙዎች የሰላም ተስፋን የፈነጠቀ ነው።

አስተያየቱን ለቢቢሲ የሰጠው በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ የሻምቡ ከተማ ነዋሪው፤ ባለፉት ዓመታት “ሰው ሞቷል፣ ተፈናቅሏል፣ ንብረት ተዘርፏል። የሞተ ሰውን መቅበር እንኳን ከባድ ነበር” በማለት ሕዝቡ በከፍተኛ እንግልት ውስጥ ማለፉን ይናገራል።

“መንግሥት እና ተቃዋሚዎቹ ለመነጋገር ስለመስማማታቸው ስንሰማ እውነት አልመሰለንም። ሕዝቡ በጣም ተደስቷል። ...ከዚያ ሁሉ መከራ በኋላ ሕዝቡ እረፍ እንዲያኝ እጸልያለሁ” በማለት ተናግሯል።

በሆሮ ጉዱሩ ዞን ዓባይ ጮመን ተብላ በምትጠራ አነስተኛ ከተማ የመንግሥት ሠራተኛ የሆነችው ነዋሪ ደግሞ፣ በሰላም እጦት ‘የተመሰቃቀለው ሕይወቷ’ ከሰላም ንግግሩ በኋላ ቀድሞ ወደነበረበት ቦታ ይመለሳል ብላ ተስፋ አድርጋለች።

ይህች የዓባይ ጮመን ነዋሪ በአካባቢው ሕይወት ምን ያክል አስቸጋሪ እንደሆነ ለማስረዳ ወርሃዊ ደሞዟን ከባንክ ለማውጣት 100 ኪሎ ሜትር መጓዝ ግድ እንደሆነባት ታስረዳለች።

“እኛ ጋር [ዓባይ ጮመን] ባንኮች ‘ሊዘረፉ’ ይችላሉ ስለሚባል ብዙ ካሽ የሚይዙ አይመስለኝም። ስለዚህ በቀን ከ1ሺህ ብር በላይ ማውጣት አይቻልም። 1ሺህ ብርም የማይገኘበት ቀን በጣም ብዙ ነው። ስለዚህ ወደ ሻምቡ ሄደን ነው ደሞዛችንን የምናወጣው። ደርሶ መልስ 100 ኪሎ ሜትር አካባቢ ቢሆንም ትራንስፖርት ስለማይገኝ ዕድለኛ የሆነ በአንድ ቀን ደርሶ መልስ ይቻላል።

“ሻምቡም ቢሆን ባንክ ላይ አንዳንዴ በጣም ወረፋ አለ። አንዳንዴ ደግሞ እዛም ከ1ሺህ ብር በላይ ማውጣት አትችሉም እያሉ ከባንክ የምናወጠው መንገድ ላይ ያልቃል” በማለት ትናገራለች።

አማጺው ቡድን ይንቀሳቀስባቸው በነበሩ በርካታ አካባቢዎች ባንኮች ላይ ጥቃት ተፈጽሞ ዝርፊያ መፈጸሙ በተደጋጋሚ ተዘግቧል። እንዲሁም የደኅንነት ስጋት በመኖሩ የባንኮች ብቻ ሳይሆን የተለያዩ ተቋማት የሥራ እንቅስቃሴ መስተጓጎል ገጥሞት ቆይቷል።

***

ነዋሪነቱን በምዕራብ ሸዋ ሆለታ ከተማ ያደረገው መሃንዲስ ደግሞ መንግሥት እና አማጺው ለንግግር መቀመጣቸው ለሰላም ዕድል እንደሚሰጥ ቢያስብም፣ ይህ የታጣቂዎቹን እንቅስቃሴ ሙሉ በሙሉ ያስቀራል ብሎ አያስብም።

ይህ መሃንዲስ ከሆለታ ከተማ በቅርብ ርቀት ባለ የሲሚንቶ ፋብሪካ ውስጥ የሚሰራ ሲሆን፣ በሥራ ቦታው በተደጋጋሚ ሠራተኞች በታጣቂዎች እየታገቱ የማስለቀቂያ ገንዘብ እንደሚጠየቁ ይናገራል።

“ወደ ሥራ ስሄድ በየትኛውም ሰዓት ልታገት እንደምችል እሰጋለሁ። እስካሁን የታገቱት በሙሉ ገንዘብ ከፍለው እንጂ በፖሊስ ነጻ የወጣ የለም። ማስለቀቂያ እስከ 500 ሺህ ብር ለሚቀበሉት ታጣቂዎች ይህ ንግድ ሆኗል” ይላል።

ፖለቲካዊ ጥያቄ አንስተው ከሚንቀሳቀሱት ባሻገር ሰዎችን በማገት እና ጥቃት በመፈጸም ገንዘብ የሚቀበሉ እና ንብረት የሚዘርፉ በመኖራቸው “ስምምነት ቢደረስ እንኳን እያገቱ ገንዘብ የሚጠየቁት ታጣቂዎች ጉዳይ ያሳስበኛል” ይላል።

የሲሚንቶ ፋብሪካዎች በብዛት በሚገኙበት የምዕራብ ሸዋ ዞን አካባቢ ባለፉት ዓመታት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሠራተኞች እና የንግድ ሰዎች እየታገቱ የማስለቀቂያ ገንዘብ ይጠየቃሉ።

የአካባቢው ባለሥልጣናት፣ ታጋቾች እና ነዋሪዎች እገታውን የሚፈጽሙት የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ታጣቂዎች ናቸው ይላሉ።

የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ቃል አቀባይ ኦዳ ተርቢ ግን እገታውን የሚፈጽሙት የታጣቂ ቡድኑ አባላት አለመሆናቸውን ከዚህ ቀደም ለቢቢሲ ገልጸዋል።

***

ለሁለት ዓመታት የዘለቀው ደም አፋሻሹ የሰሜን ኢትዮጵያው የእርስ በርስ ጦርነት በፌደራል መንግሥት እና በህወሓት መካከል የተደረሰው ሰምምነት እንዳስቆመው ሁሉ የመንግሥት እና የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ንግግር ሰላም ለራቀው የኦሮሚያ ክልል ሰላምን ሊያመጣ ይችላል ተብሎ ተስፋ ተደርጓል።

ከሁለት ቀናተ በፊት የታጣቂ ቡድኑ ዋና አዛዥ መሮ ዲሪባ ንግግሩ “በመተማመን ላይ ተመስርቶ ከተካሄደ ለሰላም ወሳኝነት አለው” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥትም “ጦርነት ይብቃ፤ ሰላም እናጽና” በማለት ልዩነትን በንግግር ለመፍታት ፍላጎቱን አሳይቷል።

በኢትዮጵያ መንግሥት እና በኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት መካከል በዚህ ሳምንት ይካሄዳል የተባለው ንግግር ታንዛኒያ ዛንዚባር ውስጥ ማክሰኞ ሚያዝያ 17/2015 ዓ.ም. መጀመሩ ተዘግቧል።

ከጥቂት ወራት በፊት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ሽመልስ አብዲሳ፣ ታጣቂው ቡድን መሳሪያውን ፈትቶ ወደ ሰላም እንዲመጣ መንግሥት ፍላጎት እንዳለው ገልጸው ነበር።

መንግሥት ሸኔ ብሎ የሚጠራው አማጺው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ከሁለት ዓመት በፊት በሕዝብ ተዋካዮች ምክር ቤት በሽብር ቡድንነት መፈረጁ ይታወሳል።