መንግሥት እና የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት በሚያደርጉት ንግግር የተለያዩ አገራት እንደሚሳተፉ ተነገረ

የኢትዮጵያ መንግሥት እና የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት በቀጣይ ቀናት ያደርጉታል በተባለው ንግግር ላይ የተለያዩ ምዕራባውያን እና የአፍሪካ አገራት በአሸማጋይነት እንደሚሳተፉ ምንጮች ለቢቢሲ ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እንዳሳወቁት በዚህ ሳምንት የሚጀመረው ንግግር ታንዛኒያ ውስጥ የሚካሄድ ሲሆን፣ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊትም ይህንኑ አረጋግጧል።

ለሚካሄደው ድርድር ቅርበት ያላቸው ምንጮች ለቢቢሲ እንደተናገሩት ሁለቱን ወገኖች በማቀራረብ እና ንግግሩን በማሸማገል የተለያዩ አገራት ይሳተፋሉ።

ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ ሁለት የቢቢሲ ምንጮች እንዳብራሩት መንግሥት ከታጣቂ ቡድኑ ጋር በሚደረገው ንግግር የስዊድን፣ የኖርዌይ፣ የኬንያ፣ የአውሮፓ ኅብረት እና የአሜሪካ ዲፕሎማቶች እንደሚገኙ ገልጸዋል።

ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው እነዚህ ምንጮች የተጠቀሷቸው አገራት በድርድሩ ይገኛሉ ይበሉ እንጂ የትኞቹ አገራት ምን ሚና ይኖራቸዋል፤ በዋናነት የማደራደር ኃላፊነትን የሚወስደው የትኛው አካል ነው የሚለው አልተለየም ብለዋል።

የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት አዛዥ መሮ ዲሪባም የሚመሩት ታጣቂ ቡድን ከፌደራል መንግሥቱ ጋር የሚያደራድር ሦስተኛ አካል መኖሩን ያረጋግጡ ሲሆን፣ አደራዳሪዎቹ እነማን እንደሆኑ በስም ከጥቀስ ተቆጥበዋል።

መሮ ዲሪባ ታጣቂ ቡድኑን ወክለው ከመንግሥት ጋር የሚደራደሩ የልዑክ ቡድን አባላት ወደ ታንዛኒያ ጉዞ እያደረጉ ስለመሆኑም ጨምረው ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እሁድ ሚያዚያ 15/2024 ዓ.ም. መንግሥታቸው ከታጣቂ ቡድኑ ጋር ለመነጋገር ቀጠሮ መያዙን ተናግረው ነበር።

የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊትም ለድርድር ያስቀመጠው ቅድመ ሁኔታ ተቀባይነት በማግኘቱ በታንዛኒያ በሚደረገው ንግግር ላይ እንደሚገኝ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

የሠራዊቱ ዋና አዛዥ መሮ ዲሪባ ይህ ንግግር በታንዛኒያዋ ራስ ገዝ ግዛት በሆነችው ዛንዚባር ደሴት ላይ እንደሚከናወን ገልጸው፤ “የጥይት ድምጽ ሳይሰማ የኦሮሞ ሕዝብ ጥያቄ መልስ የሚያገኝ ከሆነ በራችን ሁሌም ክፍት ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

መሮ እንደሚሉት “በቅርቡ” የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት እና መንግሥት ሦስተኛ ወገን ባለበት በኬንያ ለመነጋገር ቀጠሮ ይዘው የታጣቂ ቡድኑ ተወካዮች በቦታው ቢገኙም የመንግሥት ተወካዮች ግን ሳይገኙ ቀርተዋል ብለዋል።

“በሌሎች አገራት ግብዣ በኬንያ ለመገናኘት ቀጠሮ ነበር። ነገር ግን መንግሥት ሳይገኝ ቀረ” ያሉ ሲሆን፤ በአሁኑ ድርድር ስኬት ላይ ጥርጣሬዎች ቢኖሯቸውም የንግግር ሂደቱ ሰላም ሊያመጣ ይችላል የሚል ተስፋ እንዳላቸው ጨምረው ተናግረዋል።

“ንግግር መጀመሩ ጥሩ ነው። መነጋገር እና መፍታት ያለብን ብዙ ነገሮች ስላሉ ጉዳዩ በአንድ ጊዜ የሚጠናቀቅ አይሆንም” ብለዋል።

ቡድኑ ገለልተኛ የሆነ ሦስተኛ ወገን ባለበት በድርድሩ እንዲካሄድ እና በንግግሩ ወቅት በዘላቂነት ግልጸኝነት እንዲኖር ከስምምነት በመደረሱ በድርድሩ ለመገኘት ተስማምቻለሁ ብሏል ባወጣው መግለጫ።

መንግሥት እና ታጣቂ ቡድኑ ልዩነቶቻቸውን በንግግር ለመፍታት መስማማታቸው የተሰማው ለሁለት ዓመታት የተካሄደውን ደም አፋሳሹን የሰሜን ኢትዮጵያን የእርስ በርስ ጦርነት ለማስቆም አስተዋጽኦ ላበረከቱ ግለሰቦች የእውቅና የመስጠት ሥነ-ሥርዓት አዲስ አበባ ውስጥ በተካሄደበት ወቅት ነው።

አማጺው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት በምዕራባዊ እና በደቡባዊ የአገሪቱ ክፍሎች ሲያካሂድ የነበረውን እንቅስቃሴ ለማቆም ለድርድር የመቀመጥ ፍላጎት እንዳለውና ለዚህም ቅድመ ሁኔታዎችን ማስቀመጡ ይታወሳል።

ከእነዚህም መካከል ንግግሩ ከኢትዮጵያ ውጪ በሦስተኛ ወገን አሸማጋይነት ሊደረግ እንደሚገባ ገልጾ የነበረ ሲሆን፣ አሁን ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሳወቁት ድርድሩ ታንዛኒያ ውስጥ የሚካሄድ መሆኑ ታውቋል።

ቀደም ሲል ጠቅላይ ሚኒስትሩ እና የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር የሆኑት አቶ ሽመልስ አብዲሳ ከታጣቂው ቡድን ጋር መንግሥት ሰላም ለማውረድ ፍላጎት እንዳለው በተደጋጋሚ መግለጻቸው ይታወቃል።

ባለፉት ዓመታት በመንግሥት እና በአማጺው ቡድን መካከል በተካሄዱ ግጭቶች እና በተፈጸሙ ጥቃቶች በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሕይወት የጠፋ ሲሆን፣ በመቶ ሺዎች ደግሞ ለመፈናቀል ተዳርገዋል።