ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በመቀለ አሉላ አባነጋ አየር ማረፊያ አደጋ የደረሰበት አውሮፕላን ያጋጠመው ምንድን ነው?
ከአዲስ አበባ ተነስቶ መቀለ አሉላ አባነጋ አየር ማረፊያ ረቡዕ፣ ሐምሌ 9/ 2017 ዓ.ም. ከምሽቱ 2 ሰዓት አካባቢ ያረፈው የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ካረፈ በኋላ ቀላል አደጋ ገጥሞት እንደነበር መንገደኞች ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ የበረራ ቁጥር ET-298፣ Q 400 የተሰኘው አውሮፕላን፣ ከአውሮፕላን መንደርደሪያው 50 ሜትር ያህል ተንሸራቶ ወጥቶ ወደ እርሻ ቦታ መግባቱን እና አንደኛው ክንፉ መጎዳቱንም ተናግረዋል።
አደጋው ባጋጠመበት ወቅት ሰማዩ በከባድ ደመና ተሸፍኖ የነበረ ሲሆን፣ ፓይለቶቹ ሁለት ጊዜ ለማሳረፍ ሞክረው ስላልተሳካላቸው እንደገና እንዲበር አድርገው በሦስተኛው ሙከራ ማሳረፍ ቢችሉም፤ ከመንደርደሪያው ተሸንራቶ ወጥቶ በግራ በኩል ረጅም ርቀት ተንጋዶ እንደሄደ በአውሮፕላኑ ውስጥ የነበሩት ማዕረግ ኪሮስ ለቢቢሲ ትግርኛ ተናግረዋል።
አውሮፕላኑ አደጋውን ተከትሎ በግራ ክንፉ በኩል መሰበር ቢያጋጥመውም ከከፋ አደጋ መትረፉን ግን ቢቢሲ ከተሳፋሪዎች አረጋግጧል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በበኩሉ በትናንት ምሽት ባወጣው መግለጫ "በዛሬው ዕለት ከአዲስ አበባ ተነስቶ መቀሌ አሉላ አባነጋ አየር ማረፊያ ካረፈ በኋላ ከአውሮፕላን መንደርደሪያው መጠነኛ የመንሸራተት እክል አጋጥሞታል። አውሮፕላኑ በሚያርፍበት ጊዜ ዝናብ እየዘነበ ነበር" ብሏል።
ባጋጠመው መጠነኛ አደጋ መንገደኞች ላይ ጉዳት ባይደርስም ሁለት የበረራ ሠራተኞች መጠነኛ ጉዳት ስለደረሰባቸው በአምቡላንስ ወደ ሕክምና ተቋም መወሰዳቸው ተገልጿል።
አየር መንገዱም የበረራ ሠራተኞቹ ሕክምናቸውን ጨርሰው ወደ ሆቴል መወሰዳቸውን በመግለጫው አስታውቋል።
የመቀለ ከንቲባ ዶ/ር ረዳኤ በርሄ "የተጎዱት ግለሰቦች ለሕክምና በአስቸኳይ ሆስፒታል መወሰዳቸውን" በመቀለ ለሚገኘው 104.4 ኤፍኤም ተናግረዋል።
ከንቲባው በተጨማሪ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የተጎዱትን ሠራተኞች ወደ ሆስፒታለ እንዲሄዱ እንዲሁም ደኅንንታቸው ማረጋገጡን እና ለመንገደኞቹ መኪና መመደቡን ተናግረዋል።
በወቅቱ መንገደኞች ተደናግጠው እንደነበር እና ጩኸትም መሰማቱን ቢቢሲ ከተሳፋሪዎች የሰማ ሲሆን፤ የእሳት አደጋ መኪና እና አምቡላንስ በአየር ማረፊያ ደርሰዋል ብለዋል።
አውሮፕላኑ ሁለት ፓይለቶች፣ አራት የበረራ ሠራተኞችን ጨምሮ በርካታ ሕጻናት ያሉበት 49 መንገደኞችን አሳፍሮ እንደነበር የመቀለ ከተማ ኤፍኤም ሬዲዮ በዘገባው ላይ አመልክቷል።
አየር መንገዱ አደጋውን አስመልክቶ ዝርዝር መረጃዎችን ባይሰጥም በሚያርፍበት ጊዜ ዝናብ እየዘነበ እንደነበር ገልጾ "ለተፈጠረው የደንበኞች መጉላላት ይቅርታ ጠይቋል።"
መቀለ በሚገኘው አሉላ አባ ነጋ አየር ማረፊያ ላይ እንዲህ ዓይነት ተመሳሳይ አደጋ ሲያጋጥም የአሁኑ ለሁለተኛ ጊዜ ነው።
ባለፈው ዓመት ጥር 9/ 2016 ዓ.ም. የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን በመቀለ አሉላ አባነጋ አየር ማረፊያ መጠነኛ አደጋ አጋጥሞት እንደነበር ይታወሳል።
መንገደኞችን አሳፍሮ የነበረው አውሮፕላን አደጋው የገጠመው በመቀለ በሚያርፍበት ወቅት ነበር።
ለዚህ አደጋ መንስዔ የአውሮፕላኑ ጎማ በመተንፈሱ እንደሆነ ባለሥልጣናቱ በወቅቱ ተናግረው ነበር።