አስተማማኝ በሚባሉት ቦይንግ 787 ድሪምላይነር አውሮፕላኖች ላይ የሚነሳው ጥያቄ ምንድን ነው?

ቢያንስ 270 ሰዎች የሞቱበት የኤር ኢንዲያ አውሮፕላን የመከስከስ አደጋ በቦይንግ ዘመናዊ እና ታዋቂ አውሮፕላኖች ላይ ከደረሱት አደጋዎች መካከል አንዱ ነው።

እስካሁን ድረስ ግን በጣም አስተማማኝ አውሮፕላን እንደሆነ ተደርጎ ይቆጠር ነበር።

በረራ ቁጥር 171 ከአውሮፕላን ማረፊያው በተነሳ በ30 ሰከንድ ውስጥ የተከሰከሰበት ምክንያት እስካሁን አልታወቀም።

መርማሪዎች የአደጋ ምክያት ለማወቅ ጥረት እያደረጉ ነው። ነገር ግን የአደጋው መንስዔ ከአውሮፕላኑ ጋር ሊያያዝ ይችላል የሚሉ ሰዎች ቁጥር ቀላል አይደለም።

787 ድሪምላይነር፣ ከዘመናዊ እና ነዳጅ ቆጣቢ አውሮፕላኖች መካከል ቀዳሚው ነው ማለት ይቻላል።

አደጋው ከመከሰቱ በፊት ቦይንግ 787 ለአስር ዓመታት ተኩል ለሚጠጋ ጊዜ ምንም ዓይነት ከባድ አደጋ ሳይደርስበት አገልግሎት እየሰጠ ቆይቷል።

በእነዚህ ዓመታት እንደ ቦይንግ ዘገባ ከአንድ ቢሊዮን በላይ መንገደኞችን አጓጉዟል።

በአሁኑ ጊዜ በዓለም ዙሪያ ከ1,100 በላይ አውሮፕላኖች አገልግሎት እየሰጡ ነው።

ይኹን እንጂ በተከታታይ የጥራት ቁጥጥር ችግሮችም አጋጥሞታል።

በአውሮፕላኑ ላይ የሠሩ ሰዎች ስለ የምርት ጥራት ደረጃዎች ብዙ ስጋቶችን አንስተዋል።

አንዳንዶች አደገኛ ሊሆኑ የሚችሉ እንከን ያለባቸው አውሮፕላኖች ወደ አገልግሎት እንዲገቡ መፈቀዱን ተናግረዋል። ይህንን ግን ኩባንያው ያለማቋረጥ አስተባብሏል።

የሶኒክ ክሩዘር እና የ9/11 ውጤት

እንደ አውሮፓውያኑ በታኅሣሥ 2009 ቀዝቀዝ ባለ ማለዳ ነበር አዲሱ ቦይንግ 787 ድሪምላይነር አውሮፕላን በሲያትል አቅራቢያ በሚገኘው በፔይን ፊልድ አየር ማረፊያ ማኮብኮቢያ ላይ ይፋ የተደረገው።

በደስታ የተሞሉ በርካታ ሰዎች ተሰብስበው እያዩት ወደ ሰማይ ያለችግር እየቀዘፈ በረረ።

በረራው ዓመታት የፈጀ የምርምር ውጤት እና በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር መዋዕለ ነዋይ የፈሰሰበት ነበር።

ቦይንግ 787 የተፀነሰው የነዳጅ ዋጋ ለአየር መንገዶች ትልቅ ራስምታት በሆነበት በ2000ዎቹ መጀመሪያ ላይ ነበር።

በዚህም የተነሳ ቦይንግ ለረዥም ርቀት በረራ የሚያገለግል ነዳጅ ቆጣቢ አውሮፕላን ለመሥራት ወሰነ።

የአቪዬሽን ታሪክ ምሁር የሆኑት ሼአ ኦክሌይ "በ1990ዎቹ መገባደጃ ላይ ቦይንግ ሶኒክ ክሩዘር የተባለውን ዲዛይን እየሠራ ነበር" ሲሉ ወደ ኋላ መለስ ብለው የነበረውን ሁኔታ ያስታውሳሉ።

ይህ የተራቀቁ መሳሪያዎች እና ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች የተገጠመለት አውሮፕላን በድምፅ ፍጥነት እስከ 250 መንገደኞችን አሳፍሮ እንዲበር ነበር የታሰበው።

የመጀመሪያው ትኩረት ከነዳጅ ዋጋ ይልቅ ፍጥነት ሲሆን፤ በዚህም አንድ ጉዞ የሚፈጀውን ሰዓት ማሳጠር ትልቁ ግብ ሆኖ ተቀምጦ ነበር።

"ነገር ግን በአውሮፓውያኑ መስከረም 11/2001 (9/11) የተፈጸመው የሽብር ጥቃት ያስከተለው ተፅዕኖ የዓለም አየር መንገድ ኢንዱስትሪን ክፉኛ ጎድቶታል" ሲሉ ኦክሌይ ተናግረዋል።

"አየር መንገዶቹ ነዳጅ ቆጣቢ እና ረዥም ርቀት የሚበር አውሮፕላን እንደሚፈልጉ ለቦይንግ አሳውቀዋል። ከፍጥነቱ በስተቀር ከሶኒክ ክሩዘር ጋር ተመሳሳይ አቅም ያለው አውሮፕላን ፈለጉ።"

ቦይንግ የመጀመሪያ ሃሳቡን ትቶ 787ን መሥራት ጀመረ። ይህን በማድረግም ለአየር መንገዶች አዲስ የቢዝነስ ሞዴል ለመፍጠር ረድቷል።

ግዙፍ አውሮፕላኖችን በመጠቀም በርካታ ተጓዦችን በአንድ ጊዜ "ከአንድ መዳረሻ ወደ ሌላ መዳረሻ" ከማጓጓዝ ይልቅ፣ ከዚህ በፊት ያልነበረውን አነስ ባሉ አውሮፕላኖችን በትናንሽ ከተሞች መካከል ባልተጨናነቁ ቀጥተኛ መስመሮች ማብረር ይችላሉ።

ግዙፉ ኤርባስ እና ነዳጅ ቆጣቢው ቦይንግ

በወቅቱ የቦይንግ ​​ተቀናቃኝ የሆነው የአውሮፓው ግዙፉ ኤርባስ የአውሮፕላን አምራች ተቃራኒውን መንገድ ይከተል ነበር።

በተቻለ መጠን ብዙ ተሳፋሪዎችን ለማጓጓዝ የሚያስችል ግዙፍ ኤ380 አውሮፕላንን በማምረት፣ በትላልቅ እና በተጨናነቁ የዓለማችን አየር ማረፊያዎች መካከል በተጨናነቁ መስመሮች እንዲጓዝ ለማድረግ ታቅዶ ነበር።

በጥንቃቄ ከታየ የቦይንግ አካሄድ ብልሃት የተሞላበት ነበር። ነዳጅ የሚበላው ኤ380 የተባለው 251 አውሮፕላኖችን ብቻ ካመረተ በኋላ በ2021 ከገበያ ውጪ ሆኗል።

የኤሮዳይናሚክ አድቫይዘሪ ዋና ዳይሬክተር የሆኑት ሪቻርድ አቡላፊያ "ኤርባስ ወደፊት ሰዎች በፍራንክፈርት፣ በሂትሮው ወይም በናሪታ አውሮፕላን ማረፊያዎች ጉዟቸውን መለወጥ የሚፈልጉባቸው ግዙፍ ማዕከሎች እንደሚሆኑ አስቦ ነበር።"

"ቦይንግ ግን 'አይሆንም፤ ሰዎች ከአንድ ስፍራ ወደ ሌላ ስፍራ በቀጥታ መብረር ይፈልጋሉ' አለ። እና ቦይንግ በጣም ትክክል ነበር።"

ቦይንግ 787 በእውነትም ምርጥ አውሮፕላን ነበር። ክብደትን ለመቀነስ በአሉሚኒየም ሳይሆን ከካርቦን ፋይበር ውህዶች የተሠራ የመጀመሪያው የንግድ አውሮፕላን ነበር።

ከጄነራል ኤሌክትሪክ እና ከሮልስ ሮይስ ከፍተኛ ብቃት ያላቸውን ዘመናዊ ሞተሮችን የተገጠመለት ሲሆን፣ ብዙ ሜካኒካል እና አየር የማመቂያ ሥርዓቶችን በቀላል ኤሌክትሪኮች ተክቷል።

ይህ ሁሉ ከቀድሞው ቦይንግ 767፣ 20 በመቶ የበለጠ ቀልጣፋ ያደርገዋል ሲል ኩባንያው ገልጿል።

እንዲሁም ከዚህ ቀደም ከነበሩት አውሮፕላኖች ሁሉ በጣም አነስተኛ ድምጽ እንዲያወጣ ተደርጎ የተሠራ መሆኑንም አክሎ ተናግሯል።

787 ድሪምላይነር በመላው ዓለም ረዥም ርቀት በመጓዝ የሚታወቅ አውሮፕላን ነው። ቦይንግ ለተለያዩ አየር መንገዶች ሸጦትም ትርፋማ ሆኗል።

በበረራ ላይ ሳሉ የሚነሱ እሳቶች እና ሌሎች የአውሮፕላኑ እንከኖች

አውሮፕላኑ ወደ አገልግሎት ከገባ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ከባድ ችግሮች እንዳሉበት መታየት ጀመረ።

በጥር ወር 2013 በቦስተን ሎጋን ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የነበረ ቦይንግ 787 የሊቲየም አዮን ባትሪዎች በእሳት ተያያዙ።

ከሳምንት በኋላ በጃፓን በረራ ላይ የነበረ ሌላ 787 ባትሪዎች ከተገቢው በላይ በመሞቃቸው የተነሳ በድንገት ለማረፍ ተገደደ።

አውሮፕላኑ ለብዙ ወራት በዓለም ዙሪያ እንዲቆም ከተደረገ በኋላ ቦይንግ የመፍትሄ ሃሳብ ይዞ መጣ።

ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የዕለት ተዕለት ሥራዎቹ በተገቢው መንገድ የተሳለጡ ቢሆንም ምርቱ ግን በጣም ከባድ ችግር ገጠመው።

ተንታኞች እንደሚናገሩት ይህ የሆነው በከፊል ቦይንግ ለ787 ከሲያትል 2000 ማይል ርቀት ላይ በሰሜን ቻርለስተን ደቡብ ካሮላይና፣ አዲስ የመገጣጠሚያ ስፍራ ለመክፈት በመወሰኑ ሊሆን ይችላል።

ይህንን ለማድረግ የወሰነበት ምክንያት ደግሞ በአካባቢው ባለው ዝቅተኛ የሠራተኛ ማኅበር አባልነት እና ከአካባቢው አስተዳደር ያገኘው መልካም ድጋፍን ለመጠቀም በማሰብ ነው።

"ከባድ የግንባታ ጉዳዮች ነበሩ" ይላሉ አቡላፊያ። "አንዳንድ የሚታወቁ የምርት ጉዳዮች፣ በተለይ ከተለመዱት ቦታዎች ውጪ ቦይንግ ለመጀመሪያ ጊዜ የማምረቻ ስፍራ ከመክፈቱ ጋር የተያያዙ ናቸው።"

የመረጃ አቀባዮችን ክሶች ውድቅ ማድረግ

በአውሮፓውያኑ 2019 ቦይንግ የአውሮፕላኑ የተለያዩ ክፍሎች በሚገጣጠሙበት ወቅት የመጀመሪያውን የምርት ግድፈት አግኝቷል።

ከዚያም በኋላ ብዙ ችግሮች በመገኘታቸው ኩባንያው የሚያደርገውን ምርመራ በማስፋት ተጨማሪ ችግሮች መኖራቸውን ተረድቷል።

በግንቦት 2021 እና ሐምሌ 2022 መካከል ባለው ጊዜ ውስጥ አቅርቦቶች በከፍተኛ ሁኔታ ተስተጓጉለዋል። በሚቀጥለው ዓመት እንዲሁ ለተወሰነ ጊዜ ምርት እንዲቆም ተደርጓል።

ነገር ግን በቦይንግ 787 ድሪምላይነር ፕሮግራሙ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሊያደርሱ የሚችሉ ውንጀላዎች የተሰሙት ከኩባንያው የአሁን እና የቀድሞ ሠራተኞች ነው።

በጣም ታዋቂ ከሆኑት መካከል በደቡብ ካሮላይና በሚገኘው የ787 ፋብሪካ የጥራት ቁጥጥር ሥራ አስኪያጅ የነበረው ሟቹ ጆን ባርኔት ይገኝበታል።

በፍጥነት አውሮፕላኖችን ለማምረት የሚደረገው ጫና የደኅንነት ቁጥጥርን በእጅጉ ጎድቷል ሲል ባርኔት ይናገራል።

እአአ በ2019 የቦይንግ 787 ድሪምላይነር አውሮፕላን በጉዞ ላይ ሳለ አደጋ ቢደርስ ተጓዦች ኦክስጅን ላያገኙ እንደሚችሉ ባደረገው ጥናት ማረጋገጡን ተናግሯል።

ጆን ባርኔት የሠራው ጥናት፤ አውሮፕላኑ ውስጥ በአደጋ ጊዜ ኦክስጅን የሚያሠራጨው መሳሪያ የተበላሸ ወይም የማይሠራ መሆኑን እንዳሳየው ይፋ አድርጓል።

በአንድ የቦይንግ ማምረቻ ፋብሪካ ውስጥ ሆን ተብሎ የማይሠሩ መሳሪያዎች እንደሚገጠሙም ተናግሯል።

ቦይንግ የጆን ባርኔትን ክስ አጣጥሎ፤ ሁሉም አውሮፕላኖቹ በጥራት እንደተሠሩ እና በደኅንነት ረገድም አስተማማኝ እንደሆኑ ገልጿል።

በ2019 ባርኔት፤ ሠራተኞች ጫና እያደረባቸው ጥራታቸው የወረዱ ቁሳቁሶችን አውሮፕላኖች ላይ እየገጠሙ ነው ሲል ለቢቢሲ ተናግሮ ነበር።

ግለሰቡ አክሎ በተለይ በኦክስጅን መሳሪያዎቹ ላይ ችግር መኖሩን ጠቁሞ፤ በአደጋ ጊዜ ከአራት የኦክስጅን ጭምብሎች አንዱ ላይሠራ ይችላል ሲል መረጃ አሾልኳል።

ጆን ባርኔት እንደሚለው ወደ ሳውዝ ካሮላይና የድርጅቱ ጣቢያ ከተዛወረ በኋላ አውሮፕላኖች ቶሎ እንዲደርሱ በሚል በፍጥነት ይመረቱ ነበር፤ ይህ ደግሞ ደኅንነታቸውን አደጋ ላይ ይጥለዋል።

ቦይንግ ይህን ወቀሳ ፍፁም ሐሰት ነው ሲል ያስተባብላል።

ግለሰቡ ለቢቢሲ ጨምሮ እንደተናገረው ኩባንያው የሚገባውን መመሪያ እየተከተለ ስላልሆነ አንዳንድ ቁሳቁሶች ሳይገጠሙ እየተረሱ ነው።

አንዳንድ ጊዜ ጥራታቸውን ያልጠበቁ ቁሳቁሶች ከቆሻሻ መጣያ እየተነሱ ተገጥመው አውሮፕላኑ በፍጥነት እንዲጠናቀቅ ይደረጋል ሲልም ተናግሮ ያውቃል።

ባርኔት ይህንን በተለመከተ ያለውን ስጋት ለአለቆቹ ቢያሳውቅም ምንም ዓይነት ምላሽ አለማግኘቱን ይናገራል።

የግለሰቡን ቅሬታ ቦይንግ ቢያስተባብለውም በአውሮፓውያኑ 2017 የአሜሪካው አቪዬሽን ባለሥልጣን (ኤፍኤኤ) ባደረገው ምርመራ አንዳንድ የባርኔት ቅሬታዎች ውሃ ያነሳሉ ብሎ ነበር።

በተለይ የአንዳንድ ቁሳቁሶች የጥራት ማነስ እና የኦክስጅን ጭምብሎች ችግር ማስተዋሉን ያሳወቀው ባለሥልጣኑ ቦይንግ ይህን በፍጥነት እንዲያስተካክል ትዕዛዝ ሰጥቷል።

የድርጅቱ የቀድሞ የጥራት ተቆጣጣሪ ኢንጂነር ጆን፤ በጤና እክል ምክንያት ቦይንግን እስከለቀቀበት ጊዜ ድረስ ለ32 ዓመታት ሠርቷል።

በ2017 (እአአ) ኦክስጅን በአግባቡ የማያስተላልፉ መሳሪያዎች ከአገልግሎት ውጪ መደረጋቸውን ቦይንግ ገልጿል።

ከእያንዳንዱ ተሳፋሪ ወንበር በላይ የሚገኙ የኦክስጅን ማስተላለፊያዎች በተደጋጋሚ መሞከራቸውንም አክሏል።

"ትልቅ ነገር የመከሰቱ ነገር የጊዜ ጉዳይ ነው"

ባርኔት ወደ አገልግሎት የገቡ አውሮፕላኖች ከባድ አደጋ ሊያስከትሉ የሚችሉ ድብቅ ጉድለቶችን ሊሸከሙ እንደሚችሉ አሳስበዋል።

በ2019 "አንድ ትልቅ ችግር በ787 የመከሰቱ ነገር የጊዜ ጉዳይ ነው ብዬ አምናለሁ" ብለው ነበር። "ይህ ስጋቴ ስህተት እንዲሆን እጸልያለሁ" ሲሉም አክለዋል።

በ2024 መጀመሪያ ላይ ባርኔት ሕይወታቸውን አጠፋ። በጊዜው በኩባንያው ላይ ለረጅም ጊዜ ሲካሄድ በነበረው ምርመራ ላይ ማስረጃዎችን ሲሰጡ ቆይተዋል።

እርሳቸው ያቀረቡት አብዛኛ ማስረጃ የፋብሪካው የቀድሞ የጥራት ሥራ አስኪያጅ ሲንቲያ ኪችንስ በተመሳሳይ መልኩ ተናግረውታል።

እአአ በ2011 የምርት ሂደቱ እንዳይቋረጥ ለማድረግ ደረጃቸውን ያልጠበቁ ክፍሎች ሆን ተብሎ ከተጣሉበት ማጠራቀሚያዎች ተነስተው በአውሮፕላኖች ላይ ተገጥመዋል በማለት ለተቆጣጣሪዎች ቅሬታ አቅርባ ነበር።

ቦይንግን በ2016 የለቀቀችው ኪችንስ ሠራተኞች የጥራት ደረጃቸው ዝቅ ያሉ ሥራዎችን እንዳላየ እንዲያልፉ መደረጋቸውን እንዲሁም ሆን ተብሎ ችግር ያለባቸው እቃዎች፣ አደገኛ የኤሌትሪክ መቋረጥ ሊያስከትሉ የሚችሉ ጭምር በአውሮፕላኑ ላይ እንዲገጠሙ መደረጋቸውን ገልጻለች።

ቦይንግ ለእነዚህ ክሶች ምላሽ አልሰጠም።

ነገር ግን ኪችንስ እአአ በ2016 "በሥራ አፈፃፀም ማሻሻያ ላይ መሆኗ ከተነገራት በኋላ" ሥራ መልቀቋን ተናግራለች።

በመቀጠልም በቦይንግ ላይ ክስ መሥርታለች።

በቅርቡ ደግሞ ሦስተኛው መረጃ አቀባይ ባለፈው ዓመት በሴኔት ኮሚቴ ፊት ቀርቦ በቦይንግ የምርት ጥራት ጉድለት መኖሩን በሚመለከት ምስክርነቱን ሲሰጥ የመገናኛ ብዙኃን መነጋገርያ ሆኖ ነበር።

"ከባድ ችግሮች ይታዩ ነበር"

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ቦይንግ በኮርፖሬት ባህሉ እና የምርት ደረጃው ላይ ከፍተኛ ጫና እየደረሰበት መሆኑ አያጠያይቅም።

በብዛት በተሸጡት 737 ማክስ አውሮፕላኖቹ ላይ የደረሱት የመከስከስ አደጋዎች እና ባለፈው ዓመት በደረሰው ሌላ ከባድ አደጋ የተነሳ ኩባንያው ከተሳፋሪዎች ደኅንነት ይልቅ ትርፍን ያሳድዳል በሚል በተደጋጋሚ ተከሷል።

ባለፈው ዓመት ኩባንያውን የተቀላቀለው ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኬሊ ኦርትበርግ ይህንን ለመቀየር ጠንክሮ እየሠራ መሆኑን ያስረዳል።

በኩባንያው ውስጥ ያለውን የሥራ ሂደት በማስተካከል እና አጠቃላይ የደኅንነት እና የጥራት ቁጥጥር ዕቅድ ላይ ከተቆጣጠሪዎች ጋር በመሥራት ላይ እንደሚገኝም ይገልጻል።

ነገር ግን 787 ከዚህ ቀደም በቀረቡበት ውንጀላዎች ስሙ ጠልሽቷል። ይህ ቀጣይነት ያለው የደኅንነት ስጋት ሊፈጥር ይችላል?

ሪቻርድ አቡላፊያ ይህ አያሳምናቸውም።

"ታውቃለህ፤16 ዓመታት ሲበር ቆይቷል።1,200 አውሮፕላኖች አሉት፤ ከአንድ ቢሊዮን በላይ መንገደኞችን አመላልሷል። ነገር ግን እስካሁን ምንም ዓይነት የመከስከስ አደጋ አልገጠመውም" ብለዋል።

"ይህ ድንቅ የደኅንነት ታሪክ ነው።"

ማንኛውም ዓይነት ዋና ዋና እክሎች ቢኖሩበት ኖሮ ቀደም ብለው ይገለጡ ነበር ሲሉ ያስባሉ።

"በእርግጥ የምርት ችግሮች ለአጭር ጊዜ አሳሳቢ ናቸው ብዬ አስባለሁ" ብለዋል።

"ባለፉት ጥቂት ዓመታት በ787 ምርት ላይ እጅግ የላቀ ቁጥጥር ተደርጓል።በአሮጌ አውሮፕላኖች ላይ ምንም ዓይነት ከባድ ችግሮች ቢኖር እስከ አሁን ይታዩ ነበር ብዬ አስባለሁ።"

በአህመዳባድ የተከሰከሰው የኤር ኢንዲያ አውሮፕላን ከ11 ዓመት በላይ አገልግሏል።

ነገር ግን በቀድሞው የቦይንግ መረጃ አቀባይ ኤድ ፒየርሰን የተቋቋመው ፋውንዴሽን ፎር አቪዬሽን ሴፍቲ የተባለው የአሜሪካ ድርጅት ከዚህ አደጋ በፊት ስለ 787 ስጋት እንደነበረው ተናግሯል።

ፒርሰን "አዎ፣ ይህ ሊሆን የሚችለው በደኅንነት ስጋት ምክንያት ነው" ብለዋል።

ከአውሮፕላኑ ጋር በተያያዘም "የተፈጠሩ ጉዳዮችን በሚመለከት ሪፖርቶችን እንከታተላለን። የቁጥጥር ሰነዶችን እንመለከታለን። የበረራ ብቁነት መመሪያዎቹ የተለያዩ ጉዳዮችን የሚገልጹ ናቸው። እና ያ እንድትጠይቅ ያደርግሃል።"

ከእንደዚህ ዓይነት ጉዳዮች አንዱ ከመታጠቢያ ክፍል ወደ ኤሌክትሪክ መሳሪያዎች ሊፈስ የሚችል ውሃ ነው ሲሉ ያስረዳሉ።

ባለፈው ዓመት የአሜሪካ አቪየሽን አየር መንገዶች በተወሰኑ 787 ሞዴሎች ላይ ያሉ ፍሳሾቹ ሳይታወቁ መቆየታቸውን የሚገልጹ ሪፖርቶችን ተከትሎ መደበኛ ፍተሻ እንዲያካሂዱ መመሪያ ሰጥቷል ብለዋል።

ይኹን እንጂ የሕንዱ አደጋ መንስኤ እስካሁን ያልታወቀ መሆኑን ተናግረዋል።

እናም ምርመራው በፍጥነት መከናወኑ አስፈላጊ ነው። ይህም በአውሮፕላኑ፣ በአየር መንገዱም ሆነ በሌሎች ቦታዎች ላይ የሚነሱ ችግሮች መፍትሄ እንዲያገኙ ያስችላል።

ለጊዜው ግን የ787 የደኅንነት ታሪክ አስተማማኝ ሆኖ ይቀጥላል።

የአቪዬሽን አማካሪ የሆነው ሊሃም ማኔጂንግ ዳይሬክተር ስኮት ሃሚልተን "በአሁኑ ጊዜ የኤር ኢንዲያ አውሮፕላን አደጋ መንስኤ ምን እንደሆነ አናውቅም" ብለዋል።

"ነገር ግን ስለ አውሮፕላኑ በምናውቀው መሠረት 787ን ለመሳፈር አላቅማም።"