ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የሶማሊያ መንግሥት፣ ከፍተኛ መሪውን ጨምሮ ከ130 በላይ የአልሻባብ አባላትን ገደልኩ አለ
ከእስላማዊው ቡድን ጋር ጦርነት ውስጥ ያለው የሶማሊያ መንግሥት አንድ የአልሻባብ ከፍተኛ አመራርን ጨምሮ ከ130 በላይ የቡድኑ ተዋጊዎችን መግደሉን አስታወቀ።
የሶማሊያ መንግሥት እንዳለው በአልሻባብ ታጣቂዎች ላይ ይህ ጉዳት የደረሰው አሜሪካንን ጨምሮ ከዓለም አቀፍ አጋሮች ጋር ባካሄዱት ወታደራዊ ዘመቻ አማካይነት ነው።
በሶማሊያ ውስጥ ብዙም እንቅስቃሴ ከማያደርገው ከአይኤስ ቡድን ጋር ወዳጅ የሆነው አልሻባብ የመንግሥት ኃይሎች በሚመሩት ዘመቻ አማካይነት ባለፉት ስድስት ወራት በቁጥጥሩ ስር ከነበሩ የአገሪቱ ግዛቶች ተባሯል።
ከገለልተኛ ወገን ለማረጋገጥ አዳጋች ቢሆንም አሁን ደግሞ የሶማሊያ መንግሥት በወሰደው እርምጃ ከቡድኑ ከፍተኛ አመራሮች መካከል አንዱ እና ሌሎች በርካታ ተዋጊዎቹ መገደላቸው ተገልጿል።
ይህም ባለፉት ወራት ካጋጠሙት ፈታኝ ሁኔታዎች በተጨማሪ ለአልሻባብ ጉዳት እንደሚሆን ይታመናል።
የአልሻባብ በርካታ ተዋጊዎች እና ከፍተኛ አመራሩ መገደላቸውን ይፋ ያደረገው የሶማሊያ ማስታወቂያ ሚኒስቴር እንዳለው፣ ዘመቻው የተካሄደው ከአገሪቱ ዓለም አቀፍ አጋር ኃይሎች ጋር በመቀናጀት ነው።
ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ላይ ደግሞ የአሜሪካ ልዩ ኃይል በሰሜናዊ ሶማሊያ ክፍል ባካሄዱት ዘመቻ የኢስላሚክ ስቴት (አይኤስ) ታጣቂዎች ከፍተኛ አመራር የሆነን ግለሰብ መግደሉን ማሳወቁ ይታወሳል።
የአሜሪካ ወታደሮች ሶማሊያ ውስጥ ወሰዱት በተባለው እርምጃ የተገደለው ቢላል አል ሱዳኒ ከሚባለው የአይኤስ ቁልፍ ሰው በተጨማሪ 10 ረዳቶቹን መገደላቸው ተገልጿል።
የቀድሞ የአልሻባብ አባል የነበረው አል-ሱዳኒ ከበርካታ ዓመታት በፊት ከቡድኑ ተለይቶ፣ ሞዛምቢክ እና ምሥራቃዊ ዲሞክራቲክ ኮንጎን ጨምሮ በተለያዩ የአፍሪካ አገራት የአይኤስ መስፋፋትን ለማገዝ ሲሰራ ቆይቷል።
አልሱዳኒ የተገደለው የአሜሪካ ወታደሮች በሰሜናዊ ሶማሊያ በምትገኝ ተራራ ላይ ባለ ዋሻ እርሱን ለመያዝ ዘመቻ ባደረጉበት ወቅት በተካሄደ የተኩስ ልውውጥ ወቅት ነው።
አሜሪካ የሶማሊያ መንግሥት ሠራዊት በአልሻባብ ላይ እያካሄደ ላለው ዘመቻ ድጋፍ እንደምታደርግ ይታወቃል።
በቅርቡም የአሜሪካ አየር ኃይል በሶማሊያ በፈጸመው ጥቃት 30 የሚደርሱ የአልሸባብ ቡድን አባላት መገደላቸውን የአሜሪካ ሠራዊት አስታወቆ ነበር።
የሶማሊያ መንግሥት በአልሸባብ ላይ የተጠናከረ ወታደራዊ ዘመቻ እየወሰደ ባለበት በዚህ ወቅት ታጣቂ ቡድኑ በበኩሉ ተደጋጋሚ ጥቃቶችን እያደረሰ ይገኛል።
አሜሪካ ሶማሊያ የምታካሄደውን ዘመቻ ለመደገፍ የድሮን ጥቃቶችን በማድረግ ድጋፍ ስትሰጥ ቆይታለች።
ለዓመታት ሰፊውን የሶማሊያን ግዛት በመቆጣጠር ማዕከላዊውን መንግሥት ሲፈትን የቆየው አልሻባብ ከአልቃኢዳ ጋር ግንኙነት እንዳለው ይታመናል።
አልሻባብ ከሶማሊያ ባሻገር በተለያዩ ጎረቤት አገራት ውስጥ ጥቃቶችን ሲፈጽም የቆየ ቡድን ሲሆን፣ ኢላማውም ምዕራባውያንን እና ተቋማቶቻቸውንም ያካትታል።
አሜሪካም ቡድኑን ለመወጋት ለሶማሊያ እና ለአካባቢው አገራት ድጋፍ እያደረገች ሲሆን፣ የምትፈልጋቸውን የቡድኑን አመራሮች ለሚጠቁሙ ሰዎችም በሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር ሽልማት ለመስጠት በተደጋጋሚ ቃል መግባቷ ይታወቃል።