አሜሪካ የናይሮቢው የአልሻባብ ጥቃት መሪን ለጠቆመ 10 ሚሊዮን ዶላር ልትሰጥ ነው

አሜሪካ ከሦስት ዓመት በፊት በኬንያ ዋና ከተማ ናይሮቢ በሚገኝ ሆቴል እና ቢሮዎችን በአንድነት በያዘ ተቋም ላይ የተፈጸመውን ጥቃት አቀናብሯል ያለችውን የአልሻባብ ቡድን መሪን ለጠቆመ ከፍተኛ የገንዘብ ሽልማት ልትሰጥ ነው።

እንደ አውሮፓውያኑ 2019 ዱሲት በተባለው ተቋም ላይ የተፈጸመውን የሽብር ጥቃትን መርቷል የተባለውን ሞሐመድ አብዲ አደንን ለመያዝ የሚረዳ መረጃን ለሚሰጥ የአሜሪካ መንግሥት 10 ሚሊዮን ዶላር እንደሚሸልም አስታውቋል።

ሞሐመድ አብዲ አደን ዱሲትዲ2 በተባለው ሆቴል ላይ ተፈጽሞ ለ22 ሰዎች ሞት ምክንያት የሆነውን ጥቃት ያቀደው የአልሻባብ ህዋስ ክፍል አባል ነው።

ከአልቃኢዳ ጋር ትብብር እንዳለው የሚነገርለት የሶማሊያው ታጣቂ ቡድን አልሻባብ በወቅቱ ጥቃቱን ለመፈጸሙ ኃላፊነቱን ወስዶ ነበር።

አሜሪካ እንደምትለው ከዚህ ጥቃት ጋር በተያያዘ አደን ከሌሎች ተጠርጣሪ የታጣቂው ቡድን አባላት ጋር እየተፈለገ ነው።

ይህ ተፈላጊውን የሽብር ቡድን አባል ያለበትን ለጠቆመ ሰው በአሜሪካ የቀረበው የገንዘብ ሽልማት ከኬንያ ባለሥልጣናትም ሙሉ ድጋፍን አግኝቷል።

ከዚህ የሽብር ጥቃት ጋር በተያያዘ በተለያየ ደረጃ ሚና ነበራቸው የተባሉ በርካታ ሰዎች ተይዘው ጉዳያቸው ለፍርድ ቀርበዋል። ነገር ግን አስካሁን ከተጠርጣሪዎቹ መካከል በተፈጸመው ጥቃት አንድም ሰው የጥፋተኝነት ውሳኔ አልተሰጠውም።

አሜሪካ በአልሻባብ መሪዎች ላይ የምታደርገውን ክትትል እያጠናከረች ሲሆን፣ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይም በኬንያ የአልሻባብ ክንፍ መሪ የሆነውን መአሊም አይማንን ለመያዝ የሚያስችል ማንኛውንም መረጃ ለሚሰጣት 10 ሚሊዮን ዶላር ለመስጠት ቃል ገብታለች።

መአሊም ኬንያ ከሶማሊያ ጋር በምትዋሰንበት ድንበር አቅርራቢያ የኬንያ እና የአሜሪካ ሠራዊት አባላት በሚገኙበት የጦር ሠፈር ላይ ከተፈጸመ ጥቃት ጋር እጁ አለበት ተብሎ ነው በአሜሪካ እየተፈለገ የሚገኘው።

አሜሪካ በምታካሂደው የፀረ ሽብር ዘመቻ ኬንያ በአካባቢው ቁልፍ አጋሯ ናት።

አልሻባብ ኬንያ በሶማሊያ ውስጥ በተሰማራው የአፍሪካ ኅብረት ኃይል በኩል ሠራዊቷን በማሰለፏ የጥቃቱ ኢላማ መሆኗን በተደጋጋሚ ሲገልጽ ቆይቷል።

ኬንያ በአካባቢው ከሶማሊያ በመቀጠል የቡድኑ ከባድ ጥቃት የተፈጸመባት አገር ስትሆን፣ ዋና ከተማዋን ናይሮቢን ጨምሮ በሌሎችም የአገሪቱ ክፍሎች ቡድኑ በርካታ ሰዎችን የገደሉ የስብር ጥቃቶች ፈጽሟል።

በአሁኑ ጊዜ የሶማሊያ መንግሥት በአልሻባብ ላይ ከፍተኛ ዘመቻ ከፍቶ በሚወስዳቸው እርምጃዎች በይዞታው ስር የነበሩ ከተሞችን እየለቀቀ በመሸሽ ላይ ይገኛል።

ለዚህም አሜሪካ ለሶማሊያ ማዕከላዊ መንግሥት በቅርቡ በሚሊዮን ዶላሮች የሚያወጡ ወታደራዊ ድጋፎችን የሰጠች ሲሆን፣ በተጨማሪም በሰው አልባ አውሮፕላኖች ሶማሊያ ውስጥ በምትፈጽማቸው ጥቃቶች መሪዎቹ ላይና ተዋጊዎቹ ላይ ጉዳት ስታደርስ ቆይታለች።

አሁን ደግሞ የቡድኑ አንቀሳቃሾች ናቸው በተባሉ እና የተለያዩ የሽብር ጥቃቶችን በመሩ እንዲሁም ቁልፍ ሚና የነበራቸውን አባላቱን ለመያዝ የሚያስችል መረጃን ለሚሰጡ ጠቋሚዎች በሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር በሽልማት ለመስጠት ቃል ገብታለች።