ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በደቡብ ክልል በፖሊሶች ዐይን ላይ ሚጥሚጣ በመበተን 2 እስረኞች ሲያምልጡ 1 ተገደለ
በደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል ሃላባ ውስጥ አራት እስረኞች የፖሊስ አባላት ዐይን ላይ ሚጥሚጣ በመበተን ሊያመልጡ ሲሞክሩ አንደኛው ተገደለ።
የክልሉ ፖሊስ ለቢቢሲ እንደገለጸው በማረሚያ ቤት የፖሊስ አባላት ዐይን ላይ ሚጥሚጣ በመበተን ለማምለጥ ከሞከሩት 4 እስረኞች ሁለቱ ሲያመልጡ፣ አንዱ የተገደለ ሲሆን ሌላኛው ታራሚ ደግሞ ቆስሎ ተይዟል።
የደቡብ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የሚዲያ ክፍል ኃላፊ ምክትል ኮማንደር ታጁ ነጋሽ ለቢቢሲ እንደተናገሩት፣ ይህ ክስተቱ ያጋጠመው አራቱ የሕግ ታራሚዎች ሰኞ ጥር 01/2015 ዓ.ም. የፍርድ ቤት ውሏቸውን ጨርሰው ወደ ማረሚያ ቤት ሲመለሱ ነው ብለዋል።
እነዚህ አራት የሕግ ታራሚዎች ከዚህ ቀደም በተለያዩ ወንጀሎች ጥፋተኛ ተብለው በወላይታ ሶዶ ማረሚያ ቤት የእስር ጊዜያቸውን እያሳለፉ ሳለ ወደ ማረሚያ ቤቱ የእጅ ቦምብ በድብቅ በማስገባት ፖሊስ ላይ ወርውረው ለማምለጥ ሙከራ አድርገው ነበር ብለዋል።
አራቱ የሕግ ታራሚዎች በዚህ ወንጀል ክስ ቀርቦባቸው በወላይታ ሶዶ ማረሚያ ቤት የሚገኙ ታራሚዎች ስለመሰከሩባቸው ለመስካሪ ታራሚዎች ደኅንነት ሲባል ወደ ሃላባ እንዲዘዋወሩ መደረጉን ጨምረው አስረድተዋል።
“ይህ ክስ ሲመሰረትባቸው የመሰከሩት ታራሚዎች በወላይ ሶዶ ስለነበሩ ታራሚዎች ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ተብሎ እነዚህ ታራሚዎች ወደ ሌሎች ማረሚያ ቤቶች ተዘዋውረዋል” ብለዋል የደቡብ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የሚዲያ ክፍል ኃላፊ።
አራቱ ታራሚዎች ታዲያ ቀደም ሲል ከእስር ለማምለጥ ባደረጉት ሙከራ በቀረበባቸው ክስ የፍርድ ቤት ውሏቸውን ጨርሰው ሲመለሱ መሆኑን ተናግረዋል።
የፖሊስ አባላት ይን ላይ ሚጥሚጣ በመበተን ለማምለጥ ሲሞክሩ የተገደለው የሕግ ታራሚመ፣ ከዚህ ቀደም በተመሳሳይ መንገድ በሃላባ ማረሚያ ቤት በእስር ላይ ሳለ የእጅ ቦምብ በመወርወር ከእስር ቤት አምልጦ ዳግም የታሰረ መሆኑን ምክትል ሳጅን ታጁ አስታውሰዋል።
“የሞተው እስረኛ በሃላባ ማረሚያ ተቋም ቦምብ ወርውሮ ካመለጠ በኋላ በከምባታ ጠንባሮ፣ በሃዲያ እና በሃላባ ዞን ፖሊሶች ጠንካራ ክትትል ተይዞ መለሶ የታሰረ ነበር።”
ካመለጡት ታራሚዎች መካከል አንዱ የ20 ዓመት ፍርደኛ፣ ሌላኛው ደግሞ የጊዜ ቀጠሮ እስረኛ ነው መሆኑንም ገልጸዋል።
ምክትል ኮማንደሩ እሰረኞቹ ለማምለጥ ሲሞክሩ በማረሚያ ቤት የፖሊስ አባላት ላይ ያደረሱትን የጉዳት መጠን ተጠይቀው ሲመልሱ፤ “ፖሊሶቹን ተናንቀዋቸው ነው የሄዱት። ይሄ ነው የሚባል ጉዳት በፖሊሶቹ ላይ አልደረሰባቸውም” ብለዋል።
ምክትል ኮማንደሩ አንደኛው እስረኛ በምን ሁኔታ እንደተገደለ፣ ሌላኛው ደግሞ እንዴት እንደቆሰለ ዝርዝር መረጃ ከመስጠት ተቆጥበዋል።
ይሁን እንጂ ቆስሎ የተያዘው እስረኛ ወደ ሆስፒታል ተወስዶ የሕክምና ክትትል እየተደረገለት ይገኛል ብለዋል።
ምክትል ኮማንደር ታጁ ያመለጡትን እስረኞች መልሶ ለመያዝ ፎቶግራፋቸው እንደሚበትኑ ገልጸው፤ “እነዚህ እስረኞች እጅግ አደገኛ ጸባይ ያላቸው ስለሆኑ፣ ሕብረተቡ በያለበት ለፖሊስ ጥቆማ ይስጥ” ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።